Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, August 18, 2012

ብአዴን እየታመሰ ነው

ኢሳት ዜና:- ነሀሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የብአዴን አባል የሆኑ ታማኝ የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት ሰሞኑን የብአዴን የኮር አባላት ለሁለተኛ ጊዜ በአቶ በረከት መሪነት በባህርዳር ከተማ ስብሰባ አድርገዋል።

የአማራ ክልል የወጣቶች ፕሬዚዳንት የሆነው ወጣት ዘመነ ካሴ ከአገር መውጣቱና ለኢሳት  ቃለምልልስ መስጠቱ፣  በክልሉ የተነሳው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ከአቶ መለስ ዜናዊ የጤንነት ሁኔታ ጋር ተደማምሮ በብአዴን የኮር አባላት ላይ ከፍተኛ ፍርሀት እና አለመረጋጋት መፍጠሩ የስብሰባው ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ነበሩ።


የብአዴን ዋና ዋና አመራሮች በተገኙበት የኮር አባላቱ ያሳለፍነውን ጉዞ እንገምግም፣ ለወደፊቱም የማስተካከያ እርምጃ እንውሰድ የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል። የወጣት ዘመነ ካሴ ከአገር መውጣት ብአዴን በወጣቱ ዙሪያ በቂ ስራ አለመስራቱን፣ የክልሉ ወጣት ልብ ከድርጅቱ ጋር ሳይሆን ከጸረ ሰላም ሀይሎች ጋር መሆኑን ያመለካተ በመሆኑ ድርጅቱ፣ የወጣቱን ልብ መልሶ ለመያዝ መንቀሳቀስ እንዳለበት አባላቱ መተማመን ላይ ደርሰዋል። በዚህም መሰረት በተለያዩ መንገዶች ከድርጅቱ የተባረሩና አኩርፈው የተቀመጡ ወጣቶችን፣ አመራሮችንና ደጋፊዎችን ” ስህተቱ የእኛ ነበር፣ ወደ ስራ እንመልሳችሁዋለን” በሚል ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ፣ ከወጣት ዘመነ ካሴ ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩት ሁሉ በደህንነቶች ክትትል እንዲደረግባቸው ተወስኖአል።

እንዲሁም ወጣት ዘመነ ለኢሳት የሰጠውን ቃለምልልስ የሚያፈርስ የማስተባበያ ቅድመ ስራዎች በክልሉ ወጣቶች እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከፍተኛ መደነጋገር በታየበት በዚህ ስብሰባ፣ አብዛኛው አባሎች በተናጠል ወጣቱ የተናገረውን በማድነቅ የሙገሳ ቃላትን ሲሰነዝሩ ተስምተዋል፣ ይሁን እንጅ ባለስልጣኖቹ ወደ አዳራሹ ገብተው ስብሰባውን መምራት ሲጀምሩ፣ አባላቱ የወጣት ዘመነ ቃለምልልስ የክልሉን ወጣቶች አሸፍቷልና አንድ እርምጃ መወሰድ አለበት በማለት መናገር መጀመራቸውን ነው ስብሰባውን የተከታተለው ምንጫችን የገለጠው።

“ደርግን የሚያክል ሀይል ደምስሶ የመጣው ብአዴን ከውጭ ሆነው 24 ሰአት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በሚነዙት ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ሀይሎች ሊፈራረስ አይችልም” ፣ በማለት የተናገሩት አቶ በረከት፣ አባላቱ ከውጭ በሚተላለፉ  ዘገባዎች እየተደናገሩ ድርጅቱን እንዳያዳክሙት ተረጋግተው ስራቸውን እንዲሰሩ አሳስበዋል። አቶ በረከት የውሸት ፋብሪካ በማለት የጠሩት ኢሳት፣ በድርጅቱና በህገመንግስቱ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ መክፈቱን ለኮር አባሎቻቸው ተናግረው፣ አባላቱ ከኢሳት በሚለቀቀው ፕሮፓጋንዳ ሳይደናበሩ  ስራቸውን በጽናት መስራት እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበዋል።

ከወጣት ዘመነ ቃለምልልስ በተጨማሪ የሙስሊሞች ተከታታይ ተቃውሞ በኮር አባላቱ ላይ ፍርሀትን ፈጥሮአል። ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓም በሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ የድርጅቱ አባላትና ካድሬዎች ልዩ  ስልጠና እንዲወስዱ የድርጅቱ አመራሮች የወሰኑትን ለኮር አባሉ የገለጡ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት የኮር አባላት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ማን እንደሚመረጥ ልዩ ስልጠና ተሰጥተአቸዋል።

ምንም እንኳ አቶ በረከት ወደ ባህርዳር በመመላለስ የብአዴን የኮር አባላትን የማረጋጋቱን ስራ ያለመታከት ቢሰሩም፣ ድርጅቱ ግን አሁንም በቀውስ ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

No comments:

Post a Comment