EMF news: የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አይታወቅም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይዘውት
የነበረውን የጠቅላይ ጦር አዝዥነትን ሚና በማን ኃላፊነት ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ግልጽ አልነበረም።
ይህንን ክፍተት
ለመሙላት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቀጥሎ የጦር አዛዥነቱን ሚና ጄነራል ሳሞራ የኑስ ተክቶ ይሰራል፤ ተብሎ ግምት ሲሰጥ
ቢቆይም…አሁን ግን ሳሞራ የኑስም በድንገተኛ ህመም ስራቸውን ያቆሙ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ይልቁንም በትላንትናው
ምሽት ህመማቸው ስለጠና፤ ለህክምና ወደውጭ አገር ለቀው ወጥተዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰራዊት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ሆኖ፤ አመራሩን ሌ/ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሌ/ጄ
ታደሰ ወረደ በመስጠት ላይ ናቸው። ከጄነራል ሳሞራ የኑስ ድንገተኛ ህመም በኋላ ሌ/ጄኔራል ፀዓረ በተለይ የትግራው /
የህወሃት ጄነራሎች ጋር ስብሰባ ማድረጉንና ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ ሆኖ፤ በተለይ በኮሎኔል ደረጃ የሚገኙ የብአዴን
ጦር መኮንኖችንን በቅርብ እንዲከታተሉ መመሪያ ተሰጥቷል። በዚህም መሰረት በተለይ የቀድሞ የኢህዴን ታጋይ የነበሩ
እና አሁን በብአዴን ውስጥ በጦር አመራር ላይ የሚገኙ መኮንኖች ላይ የስራ ዝውውር እየተደረገ ሲሆን፤ ሌሎች
መኮንኖች ደግሞ በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ ግምገማ እየተደረገባቸው ነው።
ተያይዞ የደረሰን ዘገባ እንደሚገልጸው፤ በአሁኑ የህወሃት ጄነራሎች እና ከፍተኛ መኮንኖች የራሳቸው የጦር መረብ
በመዘርጋት የሬዲዮ ግንኙነታቸው ጭምር በትግርኛ ብቻ ሆኗል። ይህ የጦር አዛዦች በትግርኛ የሬዲዮ መልዕክት መለዋወጥ
ከቀድሞም የተለመደ እና የሚሰራበት ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን በሁሉም መስመር ላይ የሚገኙ የሬዲዮ መስመር
ተቀባዮች ጭምር በትግርኛ መመሪያ እየተለዋወጡ መሆናቸውን በመከላከያ የሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል። ይህም የአገሪቱ
ብሄራዊ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ ሳለ፤ ሚስጥራዊ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ ሲባል የሬድዮ ግንኙነቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማለት
በሚያስደፍር ሁኔታ በትግርኛ መደረጉ በሌሎች የጦር አዛዦች ዘንድ ቅሬታን እየፈጠረ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከሳሞራ የኑስ ቀጥሎ የሌፍተናንት ጄነራልነት ማዕረግ ያላቸው ሶስት ሰዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱ የህወሃት የጦር አዛዦች ሌ ሌ/ጄነራል ፀዓረ መኮንን እና ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ ናቸው። 3ኛው ሰው ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ሲሆኑ፤ ሳሞራ የኑስ በህመም ከመውደቃቸው ሶስት ወራት በፊት፤ ከጦር ሃላፊነት ስልጣናቸው እንዲነሱ ስላደረጓቸው አሁንም ድረስ በጦሩ ውስጥ የጎላ ሚና እንደሌላቸው ነው – የተገለጸው።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት፤ የፍትህ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ጠቅላይ ሚንስትሩን መተካት
የሚያስችል አዲስ ህግ እያወጣ ቢሆንም፤ አዲስ የሚሾመው ጠቅላይ ሚንስትር የጦር ኃይሉን የመምራት ስልጣኑ በግልጽ
ካልተካተተ ለህወሃት ጄነራሎች ትዕዛዝ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በዘረኝነት መስመር ክልል ውስጥ
የሚሰሩት ከፍተኛ የጦር አዛዦች በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ፤ ከሌላ ብሄር የሚሾም ጠቅላይ ሚንስትር እንደአገሪቱ ፕሬዘዳንት ከስም ያለፈ ስልጣን ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ እየሆነ ነው።
የነሌ/ጄነራል ፀዓረ መኮንን እና ሌ/ጄ ታደሰ ወረደን አምባገነናዊነት በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፤ ከአራት
አመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የጸረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቋመ። የዚህ ኮሚቴ ሃላፊ የብአዴን ታጋይ የነበረችው ወ/ሮ
እነወይ ገብረመድህን ስትሆን፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ነበር የተሾመችው። ስራዋን እንደጀመረች ከፍተኛ
ባለስልጣናት ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ መመሪያ አወጣች።
ይህ መመሪያ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር በዋናነት
“ንብረታችንን አናስመዘግብም” ብለው ያስቸገሩት እነዚሁ የህወሃት ጄነራሎች እና አዜብ መስፍን ናቸው። አሁንም ድረስ
አላስመዘገቡም። እንግዲህ እንዲህ ያሉ እምቢ ባዮች ናቸው እነሌ/ጄነራል ፀዓረ መኮንን፣ ታደሰ ወረደ እና ሌሎችም
የህወሃት ጄነራሎች። እናም “ምን አይነት ህግ፤ እንዴት ያለ ጠቅላይ ሚንስትር እነዚህን ሰዎች ሊያዛቸው ይችል
ይሆን?” የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ ይቆያል።
ማስታወሻ - ሳሞራ የኑስ እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1947 ዓ.ም. አክሱም፣
ትግራይ ተወለደ። በአባቱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን፤ እናቱ ኤትራዊ ናት። ሳሞራ የትግል ስሙ ሲሆን፤ ትክክለኛ ስሙ መሃመድ
የኑስ ነው። ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ኦፕሬሽኑን የመራው ሳሞራ የኑስ ነበር።
No comments:
Post a Comment