በተመስገን ደሳለኝ
ብርዱ የጥቅምት ነው፤ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚያንቀጠቅጥ ኃይለኛ ቅዝቃዜ፡፡ አዲስ አበባ ገና ከእንቅልፏ በመንቃት ላይ ነች፡፡ ለስራ የቸኮሉ መንገደኞች ትራንስፖርት ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ይካለባሉ፡፡ ማክሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ብስራተ ገብርኤል አደባባይ ‹‹መገናኛ ራዲዮ›› በያዙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡
የትራፊክ ፖሊሶቹ ስራ የበዛባቸው ይመስላሉ፡፡ 12 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ሲል በሁለት የሞተር ብስክሌት በተፈናጠጡ የትራፊክ ፖሊሶች ፊት አውራሪነት አንዲት ሳይረን የተገጠመላት የፖሊስ ታርጋ የለጠፈች መኪና የ‹‹መንገድ ልቀቁልኝ›› ጩኸቷን እያንባረቀች አቋርጣ በማለፍ ወደ ሳር ቤት አቅጣጫ ከነፈች፡፡ ሶስት ‹‹ቪኤት›› መኪና ሰለሱ፡፡