ኢሳት ዜና:-” ነሀሴ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የወቅቱ የኢትዮጵያ አስተዳደር የፍትህ ጋዜጣን ማገዱ፤ በኢትዮጵያ ጭል ጭል ሲል የነበረው የፕሬስ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ መዳፈኑን የሚያመለክት ነው” ሰል ኢነጋማ ገለጸ።
በስደት
የሚገኘው የ ኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር፦“በፍትህ ጋዜጣና በአዘጋጁ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ፤
በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት መብት ጨርሶ መጥፋቱን የሚያረጋግጥ ክስተት ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ፍትህ
ጋዜጣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ብቸኛ የነፃ ፕሬስ አማራጭ በመሆን፤ የህዝብን የማወቅ መብት ተግባራዊ
ለማድረግ የተጣለባትን ተጽ እኖና አፈና ተቋቁማ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን አውስቷል።
ሃምሌ 12 ቀን
2004 ዓ.ም ከአንባብያን እጅ መድረስ የነበረባት የፍትህ ጋዜጣ እትም ግን፣ ለሕትመት ብዙ ሺህ ብሮች
ከተከፈለ በኋላ፣ ከአቶ መለስ ጤና ጋር ተያይዞ ባጠናቀረችው ዘገባ ምክንያት መታገዷን አስታውሷል።
“ከዚህም
በተጨማሪም ፤የዚህ መንግስት መቀለጃ በሆነው ፍርድ ቤት የታተመው 30 ሺህ ጋዜጣ እንዲቃጠል ተፈርዶበታል”ያለው
ኢነጋማ፤በዚህ በኩል ፍትህ ጋዜጣ፣ በአገራችን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እሳት እንድትለበለብ የተፈረደባት የመጀመሪያዋ
ጋዜጣ ናት”ብሏል።
ይህ ሁሉ ሆኖ የፍትህ ሚኒስትር ባለስልጣናት ጋዜጣው በነፃነት ስራውን መቀጠል
እንደሚችል በአንደበታቸው ቢገልጹም፣ አገዛዙ ግን በማተሚያ ቤቶች ላይ በፈጠረው ስውር ጫና ምክንያት ደፍሮ ጋዜጣዋን
የሚያትም ድርጅት ባለመገኘቱ በተዘዋዋሪና በይፋ ፍትህ ጋዜጣ በመንግስት ታግዳለች-ብላል ኢነጋማ።
ገዥው ፓርቲ ድህረ ምርጫ 97ን ተከትሎ በምርጫው ለደረሰበት ሽንፈት በግልፅ ተጠያቂ ያደረገው የነፃ ፕሬስ ጋዜጦችን እና የሙያ ማህበራትን እንደነበር ያስታወሰው ኢነጋማ፤ እንደዛሬዋ ፍትህ ሁሉ በርካታ ጋዜጠኞች ታስረውና ጋዜጦችም እገዳ ተደርጎባቸው ከገበያ ውጪ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ከነዚህ
መካከል ነፃነት፣ ኢትኦጵ፣ አባይ፣ ሳተናው ምኒልክ፣ አስኳል፣ ጦማር፣ አዲስ ዜና፣ ጦቢያና ልሳነ -ሕዝብ በግንባር
ቀደምትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያወሳው ማህበሩ፤ በተለይ ኢትኦጵ ጋዜጣ የ130 ሺህ የህትመት ትዕዛዝ ሰጥቶ
በመታተም ላይ እንዳለ በደህንነቶች ጣልቃ ገብነት በተሰጠ ትዕዛዝ ህትመቱ እንዲቋረጥና የታተሙትም ጋዜጦች
እንዲወረሱ መደረጉን አትቷል።
የታሰሩት ጋዜጠኞች ከተለቀቁ በኋላ በሁለተኛው የነፃ ፕሬስ ምዕራፍ ብቅ ካሉት ጥቂት ጋዜጦች “ፍትሕ” በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ ኢነጋማ ጠቁሟል።
የአዲስ
ነገር እና የአውራምባ ታይምስ አዘጋጆችና ጋዜጠኞች በየጊዜው በደረሰባቸው ጫና አገር ጥለው በመሰደድ ጋዜጦቹ ሲዘጉ
የስርዓቱ አራማጆች፦ “ውጭ ለመውጣት በመፈለጋቸው ነው” ማለታቸውን ያወሳው ኢነጋማ፤ ይሁንና እንዲያ ከተባሉት
አንዳንዶቹ -በተሰደዱበት ተጨማሪ ክስና የቅጣት ውሳኔ አልቀረላቸውም”ብሏል።
“ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን፣
ርዕዮት አለሙንና እስክንድር ነጋን “አሸባሪዎች” ብሎ ክስ የመሰረተው የወቅቱ አስተዳደር የፍትህ ጋዜጣን ማገዱ፤
በኢትዮጵያ ጭል ጭል ሲል የነበረው የፕሬስ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ መዳፈኑን የሚያመለክት፤ ብሎም አምባገነኑ ስርዓት
በግልፅ መንግስት ያልፈለገውን መፃፍና ማሳተም እንደማይቻል ያረጋገጠበትና የአፈናው ደረጃ እየጨመረ መሄዱን
ያሳየበት ነው”ብሏል – በስደት ያለው ኢነጋማ።
“በአገራችን የፕሬስ ነፃነት እንዲረጋገጥ እና የዜጎች
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ህጋዊ መብት እንዲከበር መታገል ፤የጋዜጠኞች ተልዕኮ ብቻ እንዳልሆነ ሁሉም ይገነዘበናል
ብለን እናምናለን” ያለው ኢነጋማ፤ ስለዚህም ለእውነት ተቆርቋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፦ ፍትህ ጋዜጣን
አግደው እና ዋና አዘጋጁ ተመስገን ደሳለኝ ባልቀረበበት ችሎት ተሰይመው- ክስ በመመስረት፣ በፍትህ ስም ፖለቲካዊ
እርምጃ ለመውሰድ እየተሰናዱ ያሉትን ዳኞች በመቃወም እና ህዝባቸውን በቅንነት ስላገለገሉ በ“ሽብርተኛነት”
ተወንጅለው መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ከሚገኙት የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ጎን በመቆም፤ አጋርነታችሁን እንድታሳዩ
እንጠይቃለን!” በማለት ህዛባዊ ጥሪ አቅርቧል።
No comments:
Post a Comment