ከዛሬ 29 ዓመት በፊት የተቋቋመው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በየዓመቱ በሚያካሂደው ፌስቲቫል በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ መድረክ ነበር:: ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያካሂደው ፌስቲቫል የኢትዮጵያን ባህልና ቅርስ ከማስተዋወቅ አልፎ ለኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ማኅበረሰብ አመቺ ከባቢዎችን በመፍጠር ረገድ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል::
የድርጅቱ ተልዕኮ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማጠናከር፣ የቢዝነስ ማኅበረሰቡን መደገፍ፣ ለወጣቶች የስኮላርሺፕ ዕድል መስጠት ሲሆን፣ ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸምም የእግር ኳስ ውድድሮችን፣ ሌሎች የስፖርት ክንውኖችንና የባህል ዝግጅቶችን ያካሂዳል:: የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከብሔር ወገንተኝነት የፀዳ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያስተናግድና የሚያሳትፍ ድርጅት ነበር::