By Solidarity Movement for new Ethiopia
“ውሰዱኝ፣ ገዳዮቹ ያሉበት ቦታ አድርሱኝ፣ እኔንም እንደ ልጆቼ ይግደሉኝ፣ ብቻዬን ቀርቼ እንዴት እኖራለሁ? አልችልም። ልጆቼ፣ ልጆቼ . . . ውሰዱኝና ይግደሉኝ። እንደ ልጆቼ ልሙት. . .” ብዙም አልቆዩም ተዝለፍልፈው ወደቁ። ሊያነሱዋቸው ቢሞክሩ መቆም አልቻሉም። ህይወታቸው አለፈ። እኚህ ሶስት ልጆቻቸው በተከታታይ
በህወሃት/ኢህአዴግ ሠራዊት የተገደሉባቸው አባት ሚያዚያ 25 ቀን 2004 ሞታቸውን ሲመኙ ከርመው ተሰናበቱ።
እንዲህ
ያለው አሰቃቂ ሃዘን በአገራችን በየአቅጣጫው እየተሰማ ነው።በዋልድባ፣ በተለያዩ ገዳማትና የማመለኪያ አውዶች የህዝበክርስቲያኑን እምነት እየተፈታተኑት ነው። ሙስሊም የኢትዮጵያ ልጆች እምነታቸውን በነፃነት እንዳያራምዱ
ተደርገዋል። “ተለጣፊ” እምነት ሲቋቋምባቸው “ለምን” ብለው በመጠየቃቸው ምላሹ ጥይት ሆኗል። በኦጋዴን፣ በመተማ፣
በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች፣ በደቡብ የአገራችን ክፍል፣ በአፋር፣ በመሃል ኢትዮጵያና በተለያዩ ቦታዎች እየተፈፀመ
ያለው የቀደመው የድንጋይ ዘመን ዓይነት ግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው።
“ብሶት” አሉ አንድ ወቅቱ ያሳሰባቸው ፣ “ብሶት የትግራይን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይወልዳል። እንኳን ሰው ከብትም ሲብስበት ያመራል። ብሶት እንስሳንም ይወልዳል። መሄጃ ያጡ፣ መቀመጫ የተከለከሉ፣ እምነታቸው የተነካባቸው፣ ስጋቸው የተገደለባቸው፣ የራባቸው፣ የባሰባቸው. . . አንዱን ሞት ይመርጣሉ. . .” በማለት በመላው አገሪቱና በተከታታይ በአኙዋኮች ላይ እየተፈፀመ ያለውን የመረረ ግፍ ይገልፃሉ።
አስተያየቱ
የተሰነዘረው ሚያዚያ 24 ቀን 2004 ዓ ም ጋምቤላ አቦቦ ወረዳ ፖኪዶ ቀበሌ በጠራራ ፀሃይ ንፁሃን በጥይት
ተደብድበው መገደላቸውን ተከትሎ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በተላከ መልእክት ነው። የህወሃት/ኢህአዴግን
አገዛዝ አረመኔነት የሚያሳየው መልዕክት “. . . እየጨረሱን ነው፤ ብቀላው ተጀምሯል፤ ድረሱልን. . .”
ሲል አገር ወዳዶችን፣ ዓለም አቀፍ ለጋሽ መንግስታትን ይማጸናል። ተማጽኖው ለትግራይ ወንድም፣ እህት፣ እናት፣
አባት. . . ህዝብና ወገኖችም ጭምር ነው። ድርጊቱ በትግራይ ህዝብ ስም እየተፈፀመ በመሆኑ ነው።
በተጠቀሰው
ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ገደማ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ፖኪዶ መንደር ይሄዳሉ። አንድ መሳሪያ የያዘ
ሰው ከፊት ለፊታቸው ሲያገኙ ያለ አንዳች ጥያቄ ተኩሰው እንደገደሉት የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። ሟች በክልሉ
አስተዳደር አካባቢውን እንዲቆጣጠር የተመደበ የፖሊስ አባል ሲሆን፣ ወንድሙ ምስራቅ ኢትዮጵያ በግዳጅ ላይ የሚገኝ
የመከላከያ ወታደር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የጋራ ንቅናቄያችን በደረሰው መረጃ ወንድሙ በባልደረቦቹ የመከላከያ
ሰራዊት አባላት የተገደለበት ወጣት ለቀብር ለመድረስ ከጅጅጋ ጋምቤላ መጥቷል። ምን ብሎ ይሆን? እሱ የለበሰውን መለያ የለበሱ፣ አገርንና ህዝብን ከጠላት ለመጠበቅ የማሉ ወታደሮች ወንድሙን ገደሉበት። ያውም ምንም በደል የሌለበትን!!
ተኩስ
የሰሙ የመንደሩ ታጣቂ ሚሊሻዎች መሳሪያ በመያዝ ወደ ስፍራው ሲያመሩ አሁንም ያለ አንዳች ንግግር የመከላለያ
ሰራዊት አባላት ተኩስ ከፍተው ሁለት አቆሰሉ። ሁለት ገደሉ። ተኩስ የሰሙ የፖኪዶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት
ተማሪዎችና መምህራን ከክፍላቸው ወጡ። ይህን ጊዜ የህወሃት ሰራዊት አባላት መሳሪያቸውን ወደ ትምህርት ቤቱ አቅጣጫ
በማዞር ከየአቅጣጫው ተኮሱ፡፡ አንድ መምህርና አንድ ተማሪ የጥይት ራት ሆኑ። ሌላ የ19 ዓመት ወጣት ወደ ህወሃት
ሰራዊት ዋና ካምፕ የተወሰደ ሲሆን በደረሰበት ከባድ ድብደባ ህይወቱ ሳያልፍ እንዳልቀረ ተነግሯል።በተፈጠረው
ያልተጠበቀ ጥቃት የተደናገጡ ተማሪዎች ወደ ጫካ ፈረጠጡ።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት በሚሸሹት ተማሪዎችና
ያካባቢው ተወላጆች ላይ የተኩስ እሩምታ ይወርድ ስለነበር በትክክል የሟችና የቆሰሉትን ቁጥር መለየት አልተቻለም። ከጥቂት
ቀናት በፊት አስር ሺህ ሄክታር መሬት በወሰደው የሳዑዲ ስታር ሜካናይዝድ የሩዝ እርሻ ሰራተኞች ላይ የደረሰውን
ጥቃት ተከትሎ የአካባቢው ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው የጅምላ እስር መባባሱን ከተለያ አቅጣጫዎች መረጃዎች
እየደረሱን ነው። እስር ቤት ያሉት ንፁሃን በየቀኑ ይደበደባሉ፤ ይሰቃያሉ። ምን ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈ ለጊዜው
ዝርዝር ማቅረብ ባንችልም የሞቱ አሉ።
የተቀሩትም ህይወት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው። “ድፍን የአኙዋክ ብሄረሰብ አባላት በሽፍትነት ተፈርጀናል፣ ችግሩ አሳሳቢ ነው። በቀሉ ተጀምሯል። አሁን እየተካሄደ ያለው ግድያ በ1996 ከተካሄደው ጭፍጨፋ የሚተናነስ አይደለም። አገርና ህዝብ ከጠላት ለመጠበቅ የማለ ሠራዊት የራሱን ህዝብ እንዲጨርስ ታዟል። እንዲህ ያለ ተግባር የጠላት ሠራዊት እንኳን አያከናውንም” የሚል አስተያየት የሰጡን የጋምቤላ ነዋሪ “ፍረዱት ሲሉ” ጎክ ወረዳ ጋሪ ቀበሌ በአንድ ቤተሰብ ላይ የደረሰውን ጉዳት ተናግረዋል።
አዛውንቱ አባት በአገራቸው ባህል መሰረት ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ሳለ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ የመከላከያ አባላት ድንገት ወደ እነርሱ ዘንድ ይመጣሉ። “ለሽፍቶች ቀለብ የምትሰጠው አንተ ነህ” በማለት ሙሉ ቤተሰባቸውንና አዛውንቱን ይረሽናሉ። የቤተሰቡ ታሪክም በዛው ይደመደማል። እንዲህ ያለው አሰቃቂ ተግባር የሚፈፀመው አቶ መለስ በሚመሩት ህወሃትና በትግራይ ህዝብ ስም ነው።
እዚሁ መንደር ከሁለት ሳምንት በፊት ማር ለመቁረጥ ጫካ የሄደ አንድ ግለሰብ ሲመለስ የህወሃት/ኢህአዴግ ሠራዊት አባላት ያገኙታል “ለሽፍቶች ምግብ አድርሰህ ነው”
በማለት ይገሉትና አስከሬኑን ጫካ ውስጥ ይጥሉታል። ሰዎች ያገኙት በጠረኑ አማካይነት እንደሆነ የሚገልፁት
እማኞች “ይህንን አስነዋሪና ዘግናኝ ተግባር የሚፈጽሙት የአገር የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው” በማለት የግፉ
መጠን ከልክ ማለፍ ይናገራሉ። ከሶስት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ አንድ ሰው ተገሏል በማለት በምሬት ይገልፃሉ።
ማክሰኞ
ሚያዚያ 24 ቀን የፐርቦንጎ መንደር ነዋሪ የሆነ በመካከለኛ እድሜ የሚገኝ አንድ ወጣት ከመንደሩ ወጥቶ በዝግታ
ርምጃ ሲያዘግም በጥይት ተገድሏል። በሁሉም ዘንድ አሁን ያለው ፍርሃቻ ያለ አንዳች ጥያቄ በጥይት መገደል፣ መታሰር፣
መገረፍ፣ ሽፍቶችን አጋልጡ በሚል ማሰቃየት በጋምቤላ የዕለት ተለት ተግባር መሆኑ ነው።
ይህ ሁሉ ግፍና
በደል እየተፈጸመ ነው የአኙዋክ ብሄረሰብ አባል የሆኑት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞት ኦባንግ ወገኖቻቸው የሆኑትንና
በጅምላ “ሽፍታ” ተብለው የሚጨፈጨፉትን የአኙዋክ ብሄር አባላትን በመሰብሰብ “ሽፍቶችን አውግዙ” በሚል ሽፍቶች
እንዲያወግዙ የክልሉ አስተዳደር ባዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ነዋሪው እንዲገኝ ማሳሰቢያ የሰጡት። ተሰብሳቢዎቹን እጅግ
እንዳበሳጨ የተነገረለት ስብሰባ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ሽፍታ የሚባሉትን “ፀረ መንግስት፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ
ኢንቨስትመንት” በማለት እንዲያወግዙና በሳዑዲ ስታር የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች ላይ የተፈፀመውን ግድያ
እንዲቃወሙ፣ ይህንን ካላደረጉ የሽፍቶች ደጋፊ ለመሆናቸው እንደማረጋገጫ ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ አቶ ኦሞት
ያስጠነቀቁበት ነበር።
ያሰባሰብነው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ኦሞት ይህንን ቢሉም ሚያዚያ 25/ 2004
ዓም በማስፈራሪያና በአኙዋክነታቸው ብቻ በጅምላ “ሽፍታ” ተብለው የተፈረጁት የብሄሩ አባላት ሰልፍ መሄዳቸው ቀርቶ
ባብዛኛው ቀብር ላይ ነበሩ። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ ካድሬዎችና
በግዳጅ ሰልፍ እንዲወጡ የታዘዙ የመንግሥት ሰራተኞች ታይተዋል።
ለትግራይ ተወላጆች፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
በመላው አገራችን እየተፈፀመ ላለውና ቀደም ሲል ለተፈፀሙት ኢሰብዓዊ የብቀላ ተግባር ከአቶ መለስ ጀምሮ ራሱን
“በነጻአውጪ ግምባር” ስም ሰይሞ ኢትዮጵያን እየገዛ ያለውን ህወሃት/ኢህአዴግን፣ እንዲሁም በተዋረድ እስከታች ድረስ
ትዕዛዝ ፈጻሚ የሆኑትን ሁሉ በቀጥታ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም የጋራ ንቅናቄያችን
በመላው አገራችን ፍትህን ሰቅለው ህዝብ ላይ በጅምላና በነጠላ ጭፍጨፋ የሚያካሂዱትን ህወሃት/ኢህአዴግ መሪዎችና
አረመኔነት የተሞላበትን ግፍ ዋና አስፈፃሚ የሆኑትን የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን ያስታውቃል።
የጋራ ንቅናቄያችን በሌላም በኩል
ይህ ሥርዓት ቆሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብ ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል። አገር ቤት ያላችሁ ጭቁን የትግራይ
ተወላጆች በስማችሁ ወገኖቻችሁ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና ግድያ በፊት ለፊት እንድትቃወሙ ከየአቅጣጫው ጥሪ
እየቀረበላችሁ ነውና ለወገን አጋርነታችሁን ግለፁ። ህወሃትና አመራሮቹ በስማችሁ ህዝብ እየጨረሱ ነውና አስቁሙ።
በስማችን ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመውን የጅምላና የተናጠል ጭፍጨፋ ተቃወሙ። ህዝባዊነታችሁን አሳዩ። አገራችን
እየገባችበት ካለው የበቀል ስሜትና ከጅምላ ጥላቻ እንርቅ ዘንድ ትብብራችሁን አሳዩ።
በውጪ የምትገኙ የህወሃት ደጋፊ የትግራይ ሰዎች፤ በጭፍን ለህወሃት የምታደርጉትን ድጋፍ ቆም ብላችሁ መርምሩ። በመላው አገሪቱ እየተፈፀመ ያለውን ኢሰብዓዊ ግድያ፣ እስር፣ ግርፋት፣… ተቃወሙ። ለወገናችሁ
ያላችሁን ሰብዓዊነት የተሞላው ድጋፍ አሳዩ፡፡ “የኣጋዚ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ”፣
“የትግራይ ሴቶች ማኅበር ስብሰባ”፣ “የሕዳሴ ግድብ ስብሰባ”፣ “ትራንስፎርሜሽንና ዕድገት” . . . እያላችሁ
በምትገናኙባቸው ጊዜያት ሁሉ በየቀኑ መከራውን ስለሚያየው ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ ልታስቡ
ይገባል የሚል ጠንካራ አቋም በድፍን አገራችንና በውጪ አገር ባሉ ወንድሞቻችሁ እየተሰነዘረ ነውና የወገኖቻችሁን ጥሪ
ታደምጡ ዘንድ እንጠይቃለን።
አገር ማለት ህንጻ፣ መንገድ፣ ት/ቤት፣ ግድብ፣ ወዘተ ሳይሆን ሕዝብ ነው። ሰብዓዊነት ነው!! ከኋላው
መሣሪያ ተደግኖበት ወደ ገደል አፋፍ የሚገፋ ሕዝብ ሞት የማይቀርለት ሲሆንበት ከሁለቱ አንዱን ለመምረጥ ይገደዳል።
ከሁለት አንዱን የመምረጡ ጉዳይ ደግሞ “ብሶትን” መውለድ ማለት ይሆናል፡፡ ብሶት የወለደውን ደግሞ “ሽፍታ፣
ወንበዴ፣ አሸባሪ፣ አክራሪ፣ አተራማሽ፣ ፀረ ልማት፣” ቢሉት መፍትሔ አይሆንም፡፡ በመፈረጅ ሰላም የወረደበት አገርም
ሆነ ዘመንና የታሪክ ተሞክሮም የለም። በየትኛውም ዘመን እስካፍንጫቸው ነፍጥ ታጥቀው ህዝባቸውን ሲፈጁ የኖሩ ብሶት
የወለዳቸው ሲነሱ የሚሆነው የሚታወቅ ነውና ለሰብዓዊነት ክብር በመስጠት ብሶትን ለመቅደም የምንተገባት ጊዜ ላይ
እንዳለን መረዳት አግባብ ነው እንላለን።
ስለሆነም፤ ለዚህ ክቡር ጥሪ ቅድሚያ በመስጠት፣ የወደፊቱንም አጥብቃችሁ በማሰብ፣ ለሌሎች ጉዳዮች በምትሰባሰቡበት ጊዜያት ሁሉ የወገኖቻችሁን ጥሪ መመለስ የሚያስችላችሁን አቋም ያዙ። ይህንን መጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ ተጽዕኖ የምታደርጉበትን መንገድ መፈለግ ይገባችኋልና የከበረውን የወገኖቻችሁን ጥሪ አክብሩ።
በውል
ከላይ እንደገለፅነው የአቶ መለስ አገዛዝ “የዕድገትና የልማት” ሥራዎችን ሲሰራ በትግራይ ህዝብ ስም መሆኑ
እንደሚገልፅ ሁሉ፣ የወንጀል ተግባራቱንም የሚያከናውነው በእናንተው የትግራይ ተወላጆች ስም ነውና በማወቅም ይሁን
ባለማወቅ የመወያያ ርዕስ ከሆናችሁ ውሎ አድሯል። በዚሁ መሰረት ወንጀል የተፈጸመበትና “ብሶት የወለደው” ደግሞ
ዕርምጃ ሲወስድ የተጠናና የተነጣጠረ እንደሚሆን ለመገመት የሚያዳግት አይሆንምና ከፀፀት መጠበቅ የሚያስችል ርህራሄ
የተሞላበት ተግባር ለመፈጸም መጣደፍ የወቅቱ ጥያቄ መሆኑን የጋራ ንቅናቄያችን አጠንክሮ ያሳስባል።
በኢትዮጵያዊያን
ላይ እንደ ባዕድ ወረራ እየተከናወነ ያለው የከፋ ረገጣና ግድያ እያከናወኑ ያሉትን ክፍሎች በየትኛውም አግባብ
በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ሰፊ መሰረት በመጣል እየሰራ ያለው የጋራ ንቅናቄያችን ጋምቤላን ጨምሮ በየአቅጣጫው
የሚፈፀሙትን ወንጀሎችና፣ የወንጀሉ ተዋንያኖችን በመጪው ጊዜ፣ ከህዝብ ፍርድና ከህግ ሊደበቁ እንደማይችሉ አሁንም
ለማሳሰብ ይወዳል። የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በአምሳሉ ለሰራችሁና የራሳችሁን ህዝብ እየጨፈጨፋችሁ፣
እያሰራችሁ፣ እየደበደባችሁ፣ አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ ያላችሁ ሁሉ፣ የፈጠራችሁ ያ ህዝብ ከመፍረዱ በፊት፣ ይህንን
ስርዓት በማሽመድመድ ህዝባዊነታችሁን ለማንም ሳይሆን ለኅሊናችሁ አሳዩ።
የጋራ
ንቅናቄያችን የቆመለት መሰረቱ ከጎሳ ይልቅ ሰብአዊነትን ማስቀደም በመሆኑ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምናስተላልፈው
መልዕክት ቅድመ ማስጠንቀቂያው የሁላችንም አገር ኢትዮጵያን የሚታደጋት ነውና “ብሶት” የሚወልዳቸው በብሶታቸው
መጠን ከሁለት አንደኛውን መርጠው ሳይደፈርስ እንድንነቃ ነው። በ“ብሶት” ማዕበል እየተናወጠ ያለ ስርዐት የሙጢኝ
ብሎ ለህዝብና ለወገን ጥሪና ስቃይ ምላሽ አለመስጠት፣ ጆሮ ዳባ ማለት በደም ከመጨማለቅና ሃጢያትን ከማብዛት
አያድንምና ከአምባገነኖች ታሪክ እንማር። ቢያንስ ለልጅ ልጆቻችን ስንል!! ከሚያዚያ 21 እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2004ዓም ድረስ በጋምቤላ አካባቢ የተገደሉ
(ማሳሰቢያ፤ ይህ ዝርዝር በየጊዜው ከእስር ቤት እየተገደሉ ወደ ጫካ እየተጣሉና የደረሱበት ባለመታወቁ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀውን ሰዎች አይጨምርም)
No comments:
Post a Comment