Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, May 13, 2012

መድረክ ባለፈው ወር 259 ሰዎች በሻዕቢያ መታፈናቸውን ገለጸ

 By Ethiopian Reporter
ባለፈው ሚያዝያ ወር ውስጥ በሰሜን ትግራይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሻዕቢያ ባካሄደው ጥቃት 259 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን መድረክ አስታወቀ፡፡ መንግሥት ለውጪ ዜጐች እንጂ ለአገሩ ዜጐች ደንታ የሌለው መሆኑን ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 የሻዕቢያ መንግሥት የአገሪቱን ድንበር በመጣስ በሰሜን ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በሚኖሩ ወገኖች ላይ በየጊዜው በርካታ ጥቃቶችን በማድረስ ዜጐችን ሲገድል፣ አፍኖ ሲወስድና ንብረት ሲዘርፍ እንደሚስተዋል የገለጸው መድረክ፣ በቅርቡም ሚያዝያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሁመራ አካባቢ 43 ሰዎች፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢድሪስ ከሚባለው ሥፍራ 158 ሰዎች፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. በኢድሪስ ቀበሌ ኦርሶቢት ከተባለ ሥፍራ 58 ሰዎች በድምሩ 259 ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን አስታውቋል፡፡ ከአፈና ለማምለጥና ላለመያዝ በነበረው ግርግር ተኩስ ተከፍቶ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱንና አንድ ሰው ደግሞ ሕይወቱ ማለፉንም አክሎ ገልጿል፡፡

‹‹እነዚህን በቅርብ ቀን የተፈጸሙትን አፈናዎች ለአብነት ያህል ጠቀስን እንጂ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከአዲ ኢሮብ ታፍነው የተወሰድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጐቻችን እስካሁን የት እንደደረሱ አይታወቅም፡፡ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ባለመከታተሉ እነዚህ ዜጐች ያለበት ሁኔታ አይታወቅም፤›› ይላል የመድረክ መግለጫ፡፡

አውሮፓውያን ቱሪስቶች ከአፋር አካባቢ በተገደሉበትና በታፈኑበት ወቅት መንግሥት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የተፈጠረውን ክስተት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያራግብ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ፣ ‹‹በመቶዎች የሚቆሩ ዜጎቹ ታፍነው መንግሥት ምንም ነገር አለማለቱ ዜጐቹን ከጥቃት ለመከላከልና ደኅንነታቸውን ለማስከበር ደንታ የሌለው መሆኑን ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡

መድረክ እንደሚለው በቅርቡ በጋምቤላ በደፈጣ ኃይሎች የተገደሉ ዜጐች፣ በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ጥቃት፣ በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰቱ ግድያዎችና ሌሎችም ሁኔታዎች ሲጤኑ የኢሕአዴግ መንግሥት የዜጐችን ደኅንነትና ሕይወት እንዲያስጠብቅ የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በሚኖሩ ዜጐች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ አሳስቦት ተገቢ ዕርምጃ መውሰድ ቀርቶ ሁኔታውን በሚዲያ እንኳን ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አያሳውቅም፡፡ ከስንትና ስንት አፈናና ግድያ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዋዛ አንድ መቶ ሰዎች ታፍነው እንደተወሰዱ የተናገሩት ከቅርብ ሳምንታት በፊት ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ ነገር ግን ለእነዚህ ሰዎች ምን እየተደረገ ነገር እንዳለ ለመግለጽ አልሞከሩም፤›› ያለው መድረክ፣ ከአሁኑ በፊት እንደታየው መንግሥት መግለጫ የሚያወጣው የውጭ ዜጐች ሲታፈኑና ሲገደሉ እንጂ በራሱ ዜጐች ላይ ጥቃት ሲደርስ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

በቅርብ ጊዜ የተከሰተ አሳዛኝ ድርጊት ነው ተብሎ በመድረክ የተገለጸው ሌላው ጉዳይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ፣ ጊዳና አቤንቱ በተባሉት ወረዳዎች በጉምዝና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የተከሰተው የዜጐች እርስ በእርስ እልቂት ነው፡፡ መድረክ የደረሰውን መረጃ መሠረት በማድረግ እንደገለጸው፣ ከአንድ ወር በፊት በደረሰው በዚህ ግጭት ከኦሮሞ በኩል 27 ዜጐች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከሟቾቹ መካከልም ዘጠኙ በስም ተለይተው ታውቀዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ በገደብ አሳሳ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ዕርምጃ ከአራት በላይ ዜጐች ተገድለው ከ20 ሴቶች በላይ የመቁሰልና በመቶዎች የሚቆጠሩ የመታሰር ችግር የገጠማቸው መሆኑን በመግለጫው የጠቆመው መድረክ፣ መንግሥት የአገሪቱን ዜጐች ደኅንነትና ሕይወት መጠበቅ ሲገባው በጠራራ ፀሐይ ዜጐች ሲገደሉና ሲታፈሱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ያለመፈለጉ ተስፋ አስቆራጭ ክስተት እንደሆነበት ገልጿል፡፡

‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሁሉ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በመገንዘብ በሕዝቦች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች የሚሞቱ ሰዎች ሁኔታ በገለልተኛ ኃይል እንዲጣራ፣ በኤርትራ መንግሥት በኃይል ታፍነው የተወሰዱ ዜጐቻችን ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥቶ መንግሥት እንዲንቀሳቀስ የበኩላቸውን ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ እናስተላልፋለን፤›› በማለት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው መድረክ ጠይቋል፡፡

No comments:

Post a Comment