Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, May 13, 2012

በውፍረት ምክንያት አውሮፕላን ላይ እንዳትሳፈር የተከለከለችው ወይዘሮ ክስ መሰረተች

 By Ethiopian Reporter: አሰናጅ፡- ምሕረት ሞገስ  እና ሔኖከ ያሬድ
ሦስት መቶ ፓውንድ የምትመዝነው ሚስስ ኬንሊ ቲግማን የሉዚያና ነዋሪ ስትሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት በዳላሳ ከተማ በታዋቂው የሳውዝዌስት አየር መንገድ ለመሳፈር በሄደችበት ወቅት እጅግ በጣም ወፍራም በመሆኗ በአውሮፕላን ላይ መሳፈር እንደማትችል ተነግሯታል፡፡ በዚህም የተነሳ የ32 ዓመቷ አሜሪካዊት ወይዘሮ በአየር መንገዱ ላይ ክስ መስርታለች፡፡
አፍሪካዊ ጸሎት
አቤቱ ጌታ ሆይ፣
እንደ ምግብ እህል መከራም በቁና፣ ተሰፍሮ ቢታደልለዚህ አርበሰፊ፣ ዓለም የሚበቃ
ጦርነት.
ድህነት…
የተትረፈረፈ፣ ሰው ሠራሽ ሰቆቃ
ከሚታጨድባት
ጥቁር ሴት ወይዘሮ፣ እናት ምድር በላይ
እንደ በካር ቅሪት
የሚብሰከሰከው፣ ይህ ነፍሰ ጡር ሰማይ…
የዘመናት ምጡን፣ ተገላግሎ እስከማይ…
እባክህ አምላኬ፣
ችጋር ሳይሰለቸኝ
ሕይወትን አክኬ
የምኖርበትን ዕድሜ እንዳትነሳኝ፣
አሜን ባንተው መጀን፣ እስከዚያው
ሞት ይርሳኝ፡፡
-    ሰሎሞን ሽፈራው “ተወራራሽ ሕልሞች” ብሎ ከመደበለው ግጥሞቹ የተገኘ (2004)
* * * * *
 ሰካራም ተክሎች
ተክሎች እንደ እንስሳት ሁሉ ውስጣዊ ሽብርና ጉዳት እንደሚደርስባቸውና በአንዳንድ ኃይለኛ አስካሪ ነገሮች ራሳቸውን መሳት እንደሚችሉ ጀግዲሽ ቻንድራ ቦስ የተባሉ ሕንዳዊ ዶ/ር ባደረጉት ጥናት አረጋግጠዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1858-1937 የኖሩት እኚሁ ሳይንቲስት ተክሎች እንደ እንስሳት ሳንባ፣ ጨጓራ፣ ጡንቻ ወዘተ. ባይኖራቸውም ይተነፍሳሉ፤ የተመገቡትን ይፈጫሉ፣ በርካታ ውስብስብ ሥራዎችን ያከናውናሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሌሎች እንስሳት ሁሉ በድካም ኃይል ተሸንፈው ይልፈሰፈሳሉ፤ የኤሌክትሪክ ሞገዶችን ያፈልቃሉ፡፡

ዶ/ር ቦስ ባደረጉት ጥናት የመጨረሻ ህልውናውን በማጣትና በመሞት ላይ የነበረ አንድ ተክል ኃይለኛ የኤሌክትሪክ ሞገድ መልቀቅ መቻሉን አረጋግጠዋል፣ በተጨማሪም ያለ ካርቦንዳዮክሳይድ ጋዝ ተክሎች መኖር እንደማይችሉ ሁሉ ከመጠን በላይ ሲሆንባቸው ደግሞ እንደሚገድላቸውና ኦክስጂን ሲሰጣቸው ግን ከነበሩበት የሞት አፋፍ ተመልሰው ሕያው እንደሚሆኑ በዚሁ ምርምራቸው ላይ ዘግበዋል፡፡ ከዚህ በማስከተልም አንዳንድ ተክሎች በእጅ ሲነኩ የተለምዶ ሥራቸው እንደሚደናቀፍ፣ እንደሚቋረጥና እንደሚደነግጡ ጠቅሰው በተለምዶ “ተች ሚ ኖት” በመባል የሚጠራው አትንኩኝ ተክልን በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡

በጣም አስደናቂ ሆኖ የተገኘውና ብዙ ተመራማሪዎችን በጥናቱ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረገው ደግሞ ዕፅዋትም እንደ ሰዎችና ሌሎች እንስሳት የስካር መንፈስ ማሳየታቸው ነው፡፡ አንዳንድ አስካሪ የሆኑ ናርኮቲኮች ለተክሎች በሚሰጥበት ወቅት ተክሎች ስካር ተጭኖዋቸው ዝልፍልፍ የማለትና ስካሩ ሲበርድላቸው ደግሞ ከሰመመን ነቅተው ተለምዶዋዊ ተግባራቸውን ለማከናወን መቻላቸው ነው፡፡
-    ፈቃዱ ሺፈታ፣ ምጥን፣ 2003 ዓ.ም.
* * * * *

የአርባ ቀን ዕድል
ሞት በታዘዘ ዕለት ጦር የባለቤቱን ጋሻ ቀዶ ይወጋል፤ እንዲሞት ያልተወሰነበትን ግን ልብሱን እንኳን አይቀድም፡፡ ምንም እንኳን ድርብርብ የብረት ልብስ ቢለብስም የሞት ቁጣ ሰይፉን መዝዞ የሚከተለው ሰው እርቃኑን ነው፡፡ ግን ዕድል የምትጠብቀውና ጊዜ የምትጠብቀውን እርቃኑን የቆመን ሰው የሥጋ መከትከቻ ቢላዋ እንኳን አይገድለውም፡፡ አንድም ጥበበኛ በራሱ ትግል ከሞት አላመለጠም፡፡ እንዲሁም የቆሸሸ ነገር በመብላቱ ምክንያት የሞተ የለም፡፡

አንድ ጊዜ ይህን ታሪክ ሰምቼ ነበር፡፡ አንድ ድሃ ገንዘብ ወድቆ ጠፋበትና ቢፈልግ ቢፈልግ ገንዘቡን ሊያገኘው ስላልቻለ በመጨረሻ በድካም ተስፋ ቆርጦና ታክቶት ጥሎት እንደሄደ አንድ ሌላ ሰው ሳይለፋ ሳይደክም ከፊቱ ላይ ወድቆ አገኘው፡፡ መልካምና መጥፎ ዕድል ገና ከማሕፀን ውስጥ እያለን ለእኛ የሚፃፉ ናቸው፡፡

ብልፅግና የፈጣሪ ቡራኬ ነው እንጂ በጉልበት የሚገኘ አይደለም፡፡ ፀጋውን የሰማዩ ጌታ ካልሰጠ በጀግንነት ኃይልና በብልጠት ሊማረክ አይችልም፡፡ ጉንዳን በትንሽነቷ ምክንያት መከራ አይደርስባትም፤
-    ባይለይኝ ጣሰው (ትርጉም)፤ የሰዓዲ ጥበቦች ገላስታንና ቡስታን፣ 2004 ዓ.ም.

* * * * *

ራስን ማሳመን
ብዙ ሰዎች ሌሎችን ለመሳብ ይጥራሉ እንጂ ራሳቸውን ለራሳቸው ለመሳብ ጥረት አያደርጉም፡፡ ሌሎች ናቸው የሚጎትቷቸው፡፡ ሌሎች እንደፈለጉ የሚወስዱዎት ነዎ ወይስ ሕሊናዎ የሚወስድዎ? ሌሎችን ነው በብዛት የሚያዳምጡት ወይስ ሕሊናዎን? በሌሎች ነው የሚሳቡት ወይስ በራስዎ ማንነት?

ማጠርዎ፣ መቅጠንዎ፣ መወፈርዎ፣መርዘምዎ… የአካልዎ ምንነት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ አይደሉም፡፡ የእኛ ዋጋ ያለው አእምሯችን ውስጥ የተቀመጠው እኛ ለእኛ ያለን ታማኝነትና እኛ ለእኛ የምንሰጠው ዋጋ ነው፡፡ እኛ ለራሳችን ዋጋ ስንሰጠው ራሳችንን እንስበዋለን፡፡ በጣም ብዙዎች ግን ለራሳቸው ያላቸውን ዋጋ ዝቅ ስለሚያደርጉ ለውጫዊ ነገር ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡

- ዶ/ር ወሮታው በዛብህ፣ በኢንተርፕረነርሽፕ መበልፀግ፣ 2003 ዓ.ም.
* * * * *

ከበር

እባብ ለ14 ሺሕ ቤቶች ኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ሆነ
ከኃይለኛ ዝናብ ለመሸሽ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያ ውስጥ የገባ እባብ በኦክላማ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ለሚገኙ 14 ሺሕ ቤቶች ኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ሆነ፡፡

የአካባቢውን የጋዝና የኤሌክትሪክ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው በወቅቱ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ለተፈጠረው ምስቅልቅል ምክንያቱን ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡

በኋላ ግን በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎቹ ላይ ይሳብ የነበረው እባብ ከመስመሩ ጨርሶ ሲወጣ ምክንያቱ እሱው መሆኑ ታወቋል፡፡ ኤሌክትሪኩ ሊቋረጥ የቻለው እባቡ በመስመሮቹ ላይ በሚሳብበት ጊዜ የአደጋ ጊዜ መቆጣጠርያው በመመለሱ ነበር፡፡

* * * * *
ጓደኛዎትን ከአደጋ ለመታደግ እስከምን ድረስ ይሔዳሉ?
ጓደኛዎ ወይም ቤተብዎ አሲድ ተበጥብጦ በተቀመጠበት ገንዳ ውስጥ ቢወድቅ ምን ያደርጋሉ? ዘለው የገባበት ገንዳ በመግባት ሊያወጡት ይሞክራሉ?

በኒው ጀርሲ የተፈጸመው ግን እንዲህ ነው፡፡ ጓደኛሞቹ የብረት ትቦ ከሚሠራ ድርጅት ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ የተሠራው ብረት የሚታጠብበት የናይትሪክ አሲድ ገንዳም በአካባቢያቸው ነበር፡፡ በሥራ ላይ የነበረው የ44 ዓመቱ ዴቪስ በድንገት የአሲድ ገንዳው ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህን የተመለከተው የ51 ዓመቱ የሥራ ባልደረባው ሮብ ኒኮላስ የአሲድ ገንዳው ውስጥ ዘሎ በመግባት ሙሉ ለሙሉ የተዘፈቀ ጓደኛውን ከውጭ ሆነው ከተባበሩት ሦስት ሠራተኞች ጋር በመሆን አውጥቶታል፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ዴቪስ በሕክምና ላይ ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት በአስጊ ሁኔታ ላይ ሲገኝ ኪኮላስ ደገሞ በአሲድ የተቃጠሉ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ሕክምና እየተደረገለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment