Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, May 16, 2012

የህዝብ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መንታ መንገድ

By ተመስገን ደሳለኝ, www.fetehe.com
የመኢአድ ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ የመኢአድ ሊቀመንበር በሆኑት ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል በተከሰሱበት ክስ ሁለት አመት ከስድስት ወር ተፈርዶባቸው ከርቸሌ ገቡ፤ መኢአድ እንደአንባሻ ተከፋፈለ፤ የማይለያዩት ኃይሉ ሻውል እና ማሙሸት አማረ ተለያዩ።

አንድነት ፓርቲ ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ ይል የነበረውን ጥያቄ አንዱአለም አራጌ ይፈታ በሚል ቀየረው፤ ብርቱካንን በማስብ ይበራ የነበረውንም ሻማ አንዷአለምን በማሰብ ይበራ ዘንድ ወሰነ፤ ብርቱካን ሚደቅሳ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ልታጠና ዋሽንግተን ሄደች፣ ስዬ አብርሃ ለትምህርት ወደአሜሪካ ሄዱ፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጀርመናዊ ህፃናቶችን ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊያስተምሩ ጀርመን ገቡ፡፡ 

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ዘንድሮም ሊቀመንበር ናቸው፤ ዘንድሮም ምክትል ሊቀመናብርቶቻቸው አይታወቁም። ሳሳሁልህ ከበደ ስልጣን ያዙ፤ አየለ ጫሚሶ ተባረሩ፡፡ ኢዴፓ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የአፍሪካ የሌብራል ፓርቲ ስብሰባን ያለማካሄድ ነው በሚል ቁጭት የአፍሪካ ሌበራል ፓርቲ ስብሰባ አዲስ አበባ እንዲካሄድ አደረገ፤ ልደቱ አያሌው ከፓርላማ ሲባረሩ ትምህርት ቤት ገቡ…. ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል ‹‹አጀንዳ አልባው›› የተቃዋሚ ፓርቲ ሠፈር አክራሞት።

እነሆ ዘንድሮም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተያዘው የትግል ስልት ‹‹ኢህአዴግ አምባገነን ነው››፣ ‹‹ኢህአዴግ ምርጫ ያጭበረብራል››፣ ‹‹የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ አፋኝ ነው››፣ ‹‹ከኢህአዴግ አመራር በሙስና የተጨማለቀው ይበዛል››፣ ‹‹ሀገሪቱ በአውራ ፓርቲ መዳፍ ስር ወደቀቸ›› …ከሚል ማጋለጥ ያለፈ ሊሆን አለመቻሉንም እያየነው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተቃዋሚዎች ትግል የተገኝ ‹‹መረጃ›› ሳይሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጠንቅቆ የሚያውቀው ተራ ወሬ ነው፡፡ 

በእርግጥ በግሌ በሀገሬ ያሉ ሁሉም ተቃዋሚዎች ‹‹ከጥቆማ ያለፈ›› ትግል የማድረግ ወይ ወኔው የላቸውም፤ ወይ ብርታቱ የላቸውም ብሎ ለመደምደም ይቸግረኛል። በተለይ ደግም የተሻለ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ የሚችሉትን አራቱን ፓርቲዎች እዚህ ውስጥ መደመሩ ለተቀማጭ ሰማይ… ይሆንብኛል፡፡ (አንድነት፣ መኢአድ፣ አረና እና ኦፌደንን ማለቴ ነው) ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ እንዳናጨበጭብላቸው የምርጫ ቦርድን የምዝገባ ሰርተፍኬት ታቅፎ ከመቀመጥ የዘለለ ስራ ሲሰሩ አይታዩም፡፡
በነገራችን ላይ ደጋግሜ እንደፃፍኩት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን የተቃውሞውን ጎራ ለመምራት ወደ አደባባይ የወጡት ፖለቲከኞች በዛጎላቸው ከተሸሸጉት ‹‹ሌሎች ኢትዮጵያውያን›› የበለጠ ‹‹አክብሮት›› ይገባቸዋል። (ይሁንና ግን ሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ማለት ምን ማለት ይሆን? እዚህ ውስጥ የሚመደቡትስ እነማን ይሆኑ? ከኢትዮጵያ ሌላ ትርፍ አገር ያላቸው ናቸው ወይስ የስርአቱ ምንደኞች?) ብቻ ከዚህ ባለፈ ክንብንባቸውን ገልጠው ፊታቸውን ያስመቱ ፖለቲከኞቻችን ለእስከአሁኑ አበርክቶታቸው ዋጋ ሊያገኙ ይገባል።

 በዚህ በኩል ችግር የለም፡፡ ችግር የሚኖረው ያ የአክብሮት ዋጋ በየአመቱ እየተመነዘረ ‹‹መሪ›› በሚል ስም ዛሬም በስልጣናችን እንደተቀመጥን መቀጠል አለብን ሲሉ ነው። ይሄ ወደድናቸውም ጠላናቸውም ትልቅ ችግር ፈጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት አጣብቂኝ ከጥቆማና ከአጋላጭ ባለፈ ‹‹አንቂና አደራጅ›› መሪ የሚፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነውና።

እናም ማህተም እና የምርጫ ቦርድ ፈቃድ ያላቸው ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን ‹‹የተሻሉ›› ሊባሉ የሚችሉት አራቱ ድርጅቶችም ቢሆኑ ለኑባሪያቸው (ህልውናቸው) መገለጫ ሊሆን የሚችል ስራ ሲሰሩ ማየት እንፈልጋለን። ከዚህ ውጭ ቀጣዩ ውድድር ወይም ፉክክር እንደቀድሞው ሁሉ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎች ብቻ የመሆን እድሉ ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ ነው።

 ምክንያቱ ደግሞ በርካታ ‹‹ተቀጣጣይ ነገሮች›› በህዝብ እና በመንግስት መካከል የከረረ ፍጥጫን እየፈጠሩ በመሆኑ ነው። ይህንን ሁኔታ በግልፅ አማርኛ ስንነጋገርበት ‹‹ዙሩ እየከረረ ነው›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን ጊዜም ነው የአደባባይ ሰው ወይም መሪ ድርጅት ከወዴት ነህ? ብለን እንድንጠይቅ የምንገደደው፡፡ አሁን ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹ከሞላ ጎደል…›› ተብለው እንኳ ሊመረጡ የሚችሉ አይደሉም።

 እንደዋዛ ‹‹ኢህአዴግን ማውረድ ቀላል ነው›› ሲሉ ልትሰሟቸው ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ያንን ‹‹ቀላል›› መንገድ አያሳዩዋችሁም ወይም አያውቁትም። እናም ይህንን ‹‹ዋዛ ፈዛዛ›› ለማስወገድ ቀድመን መነጋገር አለብን። ለምሳሌ ረጅም የትግል ልምድ አላቸው የሚባሉትን የፕ/ር በየነ ጴጥሮስን እና የዶ/ር መረራ ጉዲናን ድርጅቶች ብናይ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች መንደር ከክበበው ገዳ የበለጠ ኮሜዲያን የበዛበት ሆኖ እናገኘዋለን።

በእርግጥ በየነም ሆኑ መረራ ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቁ›› እየተባለ ለንፅፅር በሚቀርብበት ሀገር በተቃውሞ ጎራ መገኘታቸው በራሱ ዋጋ ሊያሰጣቸው እንደሚገባ ከላይ ተስማምተናል። ሆኖም ያ ዋጋ ግን ዛሬም ድረስ ሊጨበጥ እና ሊዳሰስ የማይችል ፓርቲ ይዘው ‹‹መድረክ›› በሚባል የተበሳሳ ዣንጥላ ተጠልለው ‹‹ወከልነው›› በሚሉት ህዝብ ላይ እየቀለዱ እንዲጓዙ የሚያስችላቸው መሆን የለበትም።

 አሁንም ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ እነዚህ ሁለት ሊቀመንበሮች ‹‹ድርጅት›› ይሁኑ ‹‹ግለሰቦች›› ሊለዩ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ መለስ ዜናዊ ላይ ሲሆን የሚቃወሙትን የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት እነሱ ጋ ሲደርስ ‹‹ትክክል ነው›› ይሉናል። ለዚህም ነው አንድም ቀን ጠቅላላ ጉባኤ ሲያካሄዱም ሆነ የራሳቸውን አጀንዳ ቀርፀው ሲታገሉ ያላየናቸውን ፓርቲዎቻቸውን እንደፓርቲ ልንቀበል አይገባም የምለው። አመንም አላመንም በየነ ወይም መራራ የሚባል ግለሰብ ይኖራል እንጂ የሚመሩት ፓርቲ በህይወት የለም፡፡

ሌላው ቀርቶ የመረራ ጉዲና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ የሆነው ኦላና ሌሊሳ በአሸባሪነት ተጠርጥሮ ሲታሰር በህይወት ስለመኖሩ ከማህተም ባለፈ ማስረጃ ሊቀርብለት ያልቻለው የዶ/ር መረራ ኦህኮ በያዘው ማህተም እንኳ ተጠቅሞ አንዳች ያደረገው ነገር የለም፡፡ እልፍ አእላፋት የኦሮሞ ልጆች እንደበግ ከትምህርት ቤት እና ከእርሻ ቦታቸው እየታነቁ ሲታሰሩ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ›› ድምፁን ማሰማት ያልቻለው ለምን ይሆን? ዛሬ የወለጋ እና የባሌ እናቶች የደረሱ ልጆቻቸው እየታነቁባቸው ‹‹የፍትህ ያለህ?›› ሲሉ እያየን መራራን እንደፖለቲካ ታጋይ መውሰዱ ለታሪክ ስህተት እንደሚዳርግ አትጠራጠሩ፡፡

 የሀድያ ብላቴናዎች በ‹‹ችጋር›› ከቀዬአቸው መሰደድን በየነ ጴጥሮስ ከቁም ነገር እንደማይቆጥሩት ሁሉ፤ ኦሮሞ መሆን ብቻውን ‹‹አሸባሪ›› ማስባሉ ለመራራ ጉዲና ችግር አይደለም፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው ችግሩን እንደ አንድ የመቀስቀሻ (የመታገያ) ስልት ወስደው ሲጠቀሙበት እና ሲያውገዙት አለመታየታቸውም ጭምር ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ፓርቲው ከመህተም ውጭ ህይወት አልባ በመሆኑ ይመስለኛል።

…ከዚህ በኋላ ምን አልባት ራሳቸውን አጠናክረው ከ‹‹እስኮላር›› እና ‹‹ፌሎው-ሽፕ›› ማሳደድ እርቀው መውጣት ከቻሉ አንድነት፣ መኢአድ፣ አረና እና ኦፌዴን የተሻለ ተቀባይነት የሚያገኙበት እድል ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሰፋ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ከሚማልሉበት የውጭ ሀገር ትምህርት ዕድል ብቻ ሳይሆን እየተከተሉት ካለው የዘልማድ ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ››ነት መላቀቅ ከቻሉ ብቻ ነው። 

እዚህ ጋ አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት፡፡ እነዚህን ፓርቲዎችም ቢሆን የሰፋ እድል አላቸው ያልኩት በአመራሩ ጥንካሬ ተማምኜ አይደለም፡፡ ይልቁንም የዕድላቸው እጣ ፈንታ ገና ‹‹ያልተፋቀ›› የሆነው ጠንካራ የድርጅት ፍቅር ባለው አባሎቻቸው ብርቱነት ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ በዚህ ቀመር መሰረትም አንድነት እና መኢአድ ልዩነታቸውን አጥበው በጋራ መስራት ከቻሉ ሰፊ ሊባል የሚችል ዕድል አላቸው፡፡ 

ምንአልባት ይህ የሚቸግራቸው ከሆነም ከሁለቱ የትኛው ልቆ ይወጣል? የሚለው አጨቃጫቂ ቢሆንም ሁለቱም ከሰሩ ከገቡበት ቅርቃር ሊወጡ የሚችሉባቸው ሽርፍራፊ ዕድሎች አላቸው፤ ከነአሰልቺና ማለቂያ የሌለው ችግሮቻቸው ማለቴ ነው፡፡ የአረናና የኦፌዴን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ፓርቲዎች ብሄር ተኮር ከመሆናቸው አኳያ የሚነፃፀሩት በወከሉት ብሄር ውስጥ ባላቸው ተቀባይነት ነው፡፡ 

እናም ንፅፅሩ ኦሮሚያ ውስጥ ኦፌዴንን ከኦህዴድ፤ በትግራይ መሬት ላይ ደግሞ አረናን ከህወሓት ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በሚዛን የሚቀመጠው የኦሮሚያ እና የትግራይ ህዝብ ነፃ የመወዳደሪያ መድረክ ከተመቻቸለት ለየትኛው ድርጅት የተሻለ ድጋፍ ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ መቼም ለ21 አመታት ያህል ግብር ከመሰብሰብ እና ማዳበሪያ ከመቸርቸር የዘለለ ፋይዳ ለሌላቸው ኦህዴድ እና ህወሓት ነው የሚል ቀልደኛ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

ከዚህ ባሻገር በሀገራችን ፖለቲካ ላይ በየአመቱ እንደአዶ-ከበሬ የሚከሰት አንድ አደገኛ ተመላላሽ ችግር አለ። የአንጃ ፖለቲካ የሚባል። ይህ አይነቱ አደጋ ነው የፓርቲውን ውስጠ ሚስጥር የጉሊት ሽንኩርት የሚያደርገው፡ ፡ ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ ባሉ ተቃዋሚዎች ውስጥ የአንጃ ፖለቲካ የሚከሰተው በሶስት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው መናፍቅነት / ጥርጣሬ/ ሲከሰት ነው። በዚህ ጉዳይ ደግሞ ‹‹አንጋፋ›› ፖለቲከኞቻችን የተካኑ ናቸው። ልክ መለስ ‹‹በሲኒ ውስጥ ማዕበል የሚፈጥሩ›› የሚሏቸው አይነት፤ ‹‹እከሌ ወያኔ ነው›› ይሉና ጠርጥረው ያሰጠረጥራሉ፤ ፈርጀው ያስፈርጃሉ። 

ይህንን ተከትሎም በአንጃዎች መናጥ የፓርቲው ዕጣ ፈንታ ይሆናል። ይህን ጊዜም ትላልቆቹ ፖለቲከኞች ሽሚያ ይገባሉ፤ ሽሚያው ግን ፓርቲውን ከአንጃ ወጀብ ለመታደግ አይደለም፤ ትከሻው ለ‹‹ሎሌነት›› የተመቻቸውን ለማፈስ እንጂ፡፡ሁለተኛው ችግር የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊነት ነው። በዚህ ተቃዋሚዎች የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ከኢህአዴግ አይለዩም። ክፉ አቻዎች ናቸው። በመኢአድ ውስጥ የኢንጅነር ኃይሉ ሻወልን ሃሳብ መቃወም ዛሬ መኢድ ያለበት ደረጃ ያደርሳል። 

መሰነጣጠቅ ማለቴ ነው። አመራሩን መገምገም ወይም የአደባባይ ስህተቱን መተቸት ‹‹መናፈቅ›› ያስብላል፡፡ እናም በሁሉም ፓርቲዎች ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ‹‹ውስጠ-ዲሞክራሲ›› የሚባል ነገር እምጥ ይግባ ስምጥ አይታወቅም፡፡ በዚህም የተነሳ ለገዥው ፓርቲ ሲሆን ‹‹ለልዑላኑ እውነት መናገር አንገት ያስቀነጥሳል›› ማኪያቬሊያዊ አስተምህሮት በተቃዋሚዎች ሰፈር ሲደርስ እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን ‹‹አመራሩን መተቸት መናፍቅነት ነው››፤ መናፍቁ ደግሞ የራሱን አማኝ ያሰባስብና አንጃ ይፈጥራል፡፡

ሶስተኛው Personality Cult (የተክል ስብዕና አምልኮ) ለመፍጠር የሚደረገው እሽቅድምድም ነው ለአንጃ መፈጠር በር ከፋቻ የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ በትግሉ ዘመን በህወሓት ውስጥ ግለሰብን ማምለክም ሆነ ለመመለክ ራስን ማመቻቸት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነበር፡ ፡ ከ1993ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሮ በግልባጩ መለስ ዜናዊን ያለማምለክ በሞት ባያስቀጣም ከፓርቲ ጥቅማ ጥቅም በእጅጉ ያርቃል ተባለ- ባልተፃፈው የህወሓት ህግ፡ ፡ ይህንንም ተከትሎ አንጃ ተፈጠረ፡፡

 እናም በህወሓት ውስጥ ‹‹ውድብ /ድርጅት ወስናለች›› ተረት የሆነውን ያህል በተቃዋሚዎችም ‹‹ቅድሚያ ለፓርቲው ውሳኔ›› የሚለው መርህ ተረት ሆኖአል። ለዚህ ትልቁ ማሳያ በየነ ጴጥሮስ እና መረራ ጉዲና ናቸው። ለምሳሌ የመረራ ጉዲና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ገብሩ ገ/ማርያም በማንኛውም መልኩ ከመራራ የሚያንስ አቅም የላቸውም። እንዲያውም በአንዳንድ ነገሮች፣ ሀሳብን አፍታቶ በማብራራት እና በመሳሰሉት የተሻሉ ናቸው። ነገር ግን ላለፉት አስራ ስድስት አመታት ከመረራ ውጭ ማንም ሊቀመንበር ሆኖ አያውቅም፡፡ 

ምንአልባትም በቀጣዩ አስራ ስድስት አመታትም ኦህኮ በዚህ መልኩ የሚቆይ ከሆነ እመኑኝ መረራንም በሊቀመንበር ወንበር ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በየትኛውም ሚዲያም ሆነ መድረክ ም/ል ሊቀመንበራቸውን ገብሩ ገብረማሪያም ኦህኮን ወክለው ሲናገሩ አናያቸውም። ይህ የሆነው በመለኮታዊ ስልጣን አይደለም፤ መረራ የመሰረቱት ፓርቲ የራሳቸውን ተክለ ስብዕና ብቻ ይዞ ይገነባ ዘንድ ስላመቻቹት እንጂ። እናም ልክ ኢህአዴግ ሲነሳ መለስ ዜናዊ፤ ህወሓት ሲነሳ መለስ ዜናዊ እንደሆነው ሁሉ ኦህኮም ሲነሳ ከፊት መራራ ጉዲና ናቸው፡፡

 በየነ ጴጥሮስም ‹‹ጽዋ›› እየተጠጣ የሚዘከርለት መላዕክ ይመስል በፓርቲያቸው ውስጥ ራሳቸውን ‹‹አምላክ›› አድረገዋል፤ ያውም የማይከሰስ፣ የማይወቀስ። በዚህም ተደጋጋሚ ጊዜ በአንጃ ተከፋፍለው ከጦር መሳሪያ ፍልሚያ መለስ ባሉ ፍልሚያዎች ሲፋለሙ ማየቱ አዲስ አይደለም፡፡
ከዚህም አልፈው በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በመድረክ በኩል የሚተሳሰሩትን የአንድነት ም/ሊቀመንበር /በዚህ ወቅት ሊቀመንበሩን ወክለው እየሰሩ ነው/ ግርማ ሰይፉ ፓርላማ በመግባታቸው ደጋግመው ወርፈዋቸዋል። 

በቅርቡ አንድ የመድረክ አመራር እንደነገሩኝ በዚህ ጉዳይ ላይ የስራ አስፈፃሚ አባላት ተሰብስበው እየተወያዩ ሳለ መራራ ጉዲና ‹‹ድንጋይ እየተወራወርን ነው›› ሲሉ የመወራረፉን የእድገት ደረጃ በገደምዳሜ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ መቼም የሽግግር ወቅቱን ጨምሮ ለአራት ክፍለ ጊዜ / Term/ በፓርላማው ቋሚ ተሰላፊ የነበሩት በየነ ጴጥሮስ ‹‹ፓርላማ መግባትን›› ሲቃወሙ መስማት የተቃውሞ ስብስብ መሪዎች የሞራል ደረጃችው የት እንዳለ ያሳያል፡፡ በዚህ መልኩም በእንዲህ አይነት ፖለቲከኞች የምንሻገረው ወንዝ ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰብ ደመናን የመጨበጥ፣ ጉምን የመዝገን ያህል ይሆንብናል። 

ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ሳለ በመሀሉ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሮ ጎራ ለማለት ሞከርኩ። ፕሮግራማቸውን በደምሳሳው ለመቃኘት። ነገር ግን የአብዛኞቹ ቢሮ ዝግ ነው። እናም ሁለተኛ አማራጭን ተጠቀምኩ። ኢንተርኔትን፡፡ በመረራ ጉዲና የሚመራውን የኦህኮ ፕሮግራም አገኘሁና በእጅጉ ተገረምኩ። ያስገረመኝ ምን መሰላችሁ? ከሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከፍተኛ የሆነውን ኦሮሞን የሚወክለው ኦህኮ ፕሮግራሙ በአምስት ገፅ የሚጠናቀቅ መሆኑ ነው። 

እንዴት ነው ነገሩ? ምን አልባት ‹‹ኢየሱስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ነው በዚህ አለም የኖረው›› የሚል የመፀሀፍ ቃል ሰምተው ይሆን እንዲህ በአምስት ነጠላ ወረቀት የተዘጋጀ ፕሮግራም የቀረፁት? ብቻ እንጃ፡ ፡ (እንደማሳሰቢያ፡- በበየነ ጴጥሮስ እና በመረራ ጉዲና ላይ ያተኮርኩት በአሁኑ ወቅት በተቃውሞ ጎራ ያለውን ፖለቲካ በመምራት ከሁሉም የበለጠ የትግል ዕድሜ ስላስቆጠሩ ነው፡፡ በተጨማሪም የሁለቱ ሰዎች የፖለቲካ አዙሪት ሌሎችንም ይወክላል በሚል ነው)
የመውጫ በር አለ?

የወንድ በር ሳይሆን የመውጫ በር ለፈለገ አለ፡፡ በተለይ ለአንድነት፣ ለመኢአድ፣ ለኦፌዴን እና ለአረና። ለምሳሌ የፀረ መጅሊስ እንቅስቃሴ፣ የመምህራን ጥያቄ፣ የጉራፈርዳ መፈናቀል፤ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሳንሱር፣ የኑሮ ውድነት፣ በልማት ስም ኢፍትሃዊ መፈናቀል… ሌላም ሌላም ጥያቄዎችን በማጎን ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።

 ከእንዲህ አይነት ህዝባዊ አጀንዳዎች ጎን ከመቆም ባሻገርም ሌሎች ድርጅታዊ ጥንካሬን የመፍጠሪያ ስልቶችን መንደፍ እና አድፋጭ ምሁራኖችን ወደ አደባባይ ማምጣትም ሌላው የመጠናከሪያ መንገድ ነው። activist (ተሟጋቾችን) መመልመል እና ማብቃት፤ ከዛም ሀገራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት በአለም አቀፍ መድረኮች ሳይቀር ለመሟገት የሚችሉበትን መደላድል ማመቻቸትም እንዲሁ ለድርጅት ጥንካሬ የጎላ ጠቀሜታ አለው።

በአናቱም ራሳቸውን ስልጣን ላይ እንዳለ ገዢ ፓርቲ በመውሰድ ለእያንዳንዱ ጉድልቶች የመፍትሄ ሀሳቦችን መሸጥ ፓርቲዎቹ ለመጠናከር ከሚችሉባቸው ስልቶች ዋነኛው ነው። በተለይም አማራጭ መንገዶችን ማሳየት ጠቀሜታው የላቀ ነው። ወጣቶችን ወደፊት ማምጣትም ሌላኛው ጠቃሚ ስልት ነው። በ‹‹ያ ትውልድ›› እና በ‹‹66ቱ ፖለቲካ›› የእኔን ትውልድ ‹‹አማልላለሁ›› ማለቱ ግን አስቸጋሪ ነው። እናም ፓርቲዎቹ የአመራር ቦታውን በወጣቶችም ጭምር ከአጠናከሩት ለተሻጋሪነቱ አስተማማኝ መንገድ ይፈጥርላቸዋል። 

በዚህ ደግሞ ቢያንስ በቀጣዩ አመት የሚደረገውን የአዲስ አበባ ምርጫን ‹‹እንደሰርቶ ማሳያ›› የሙከራ ፕሮግራም ወስደው ራሳቸውን ሊፈተሹ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ መልካም ምኞቴ ነው፡፡ ሆኖም ‹‹የፖለቲካ ምህዳር መጥበብን›› ብቻ በመግለጫ እየተቃወሙ፣ በሰላማዊ የትግል ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አማራጮችን ‹‹አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ›› እያለፉ፣ 150 ሰው ብቻ በተሰለፈበት ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹ብርቱካን ትፈታ›› ተብሎ የተጠየቀውን አይነት ጥያቄ ያህል እንኳ ‹‹አንዷአለም ይፈታ›› በሚል መድገም አቅቶአቸው እያየን ‹‹መጪው ጊዜ ለተቃዋሚዎች ጨለማ ነው›› ለማለት ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

 ከዚህ በተረፈ ህዝቡ ከፓርቲዎቹ ቀድሞ ወደአደባባይ በመውጣት፡- ‹‹ገለል ይሻልሃል ገለል ያለው መቶልሃል›› ያለ እንደሆነ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሊቢያ ወይም የሶሪያ ከመሆን አይመለስም። በሊቢያ እና በሶሪያ ህዝባዊ አመፅ በተቀሰቀሰ ጊዜ የተፈጠረው ነገር ምንድር ነው? ብሎ መጠየቁ የተሻለ ተሞክሮ እንዲኖር ያስችላል፡፡ ምንአልባትም እንዲህ የሚል መልስ ልናገኝ እንችላለንና፡፡ በእነዚህ ሀገራት ህዝባዊ ተቃውሞውን መስመር የሚያሲዝ ጠንካራ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ ህዝቡ በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ ከመንግስት ጋ መፋለሙ ሀገራቱ የመፈራረስ አደጋ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። 

በቱኒዚያ እና በግብፅ ግን የታየው የዚህ ተቃራኒ ነው። ምክንያቱም በሁለቱ አገራት የነበሩ ፓርቲዎች ምንም እንኳን በጠበበ ምህዳር እና በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ቢሆኑም ከአብዮቱ በፊት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ራሳቸውን ከማጠናከር ያልሰነፉ ስለነበር ተቃውሞ ሲቀሰቀስ ከፊት መስመር ለመገኘት አላዳገታቸውም። እናም የፈነዳውን ህዝባዊ ቁጣ ተከትሎ ሀገሬው አደባባይ መዋል ሲጀምር ፓርቲዎቹ በቀላሉ

‹‹አንበሳው ጋሜ አይዞህ ወንድሜ››ን እየዘፈኑ አብዮቱን ከመቀላቀል ያገዳቸው አልነበረም። ይህ ደግሞ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር አስችሎአል። (…በአነሰተኛና ጥቃቅን መደራጀትም ስራ ነው፣ ኮብል ስቶን ማንጠፍም ስራ ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋምም ‹‹ኢንተር ፕሩነር ነው›› /ስራ ፈጠራ ነው/ በሚል ስለተቋቋሙ ፓርቲዎች ሌላ ቀን እመለስበታለሁ)

No comments:

Post a Comment