By ፍኖተ ነጻነት-ቁ.37
የአዲስ አበባ መግቢያ ኬላዎች በፌዴራል እንዲጠበቅ ተደረገ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዲስ አበባ ዙሪያ ዞን ሥር የምትገኘው የቡራዩ ከተማ ሁለቱ ከንቲባዎች ከሌሎች 17 የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በሙስና ተጠርጥረው ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት “የከተማው ከንቲባ አቶ ቸርነት ጉርሜሳና የቀድሞ ከተማው ከንቲባ አቶ ኃይሉ ደቻሳ ከሌሎች 23 የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለሥልጣናት “በካሽ ልምጣ ወይስ በክላሽ” እያሉ መሬት የዘረፉበት አካባቢ እየተባለ የሚቀለድበት ቡራዩ ከተማ ባለሥልጣናት ተለያየ ሰው ስም በተደጋጋሚ ቦታ ወስደው በመሸጥ በመለወጥ ከፍተኛ ሙስና ሲከናወንበት ከነበሩት ከተማዎች ውስጥ ቡራዩ አንዷ መሆኗ ይነገራል፡፡ በዚሁ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ 25 የአካባቢው ባለሥልጣናት መታሰራቸው ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና ከመላው አገሪቱ ወደ አዲስ አበባ መግቢያ የሆኑት አምስቱ ኬላዎች ከኦሮሚያ ፖሊስ ተነጥቆ ለፌዴራል ፖሊስ መሰጠቱን የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ገለፁ፡፡ ምንጮች እንደሚሉት “ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም የምታገኝበት መንገድ ወደፊት በህግ ይወሰናል የሚል ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ቢኖርም ጉዳዩ እስከአሁን ድርስ እልባት ባለማግኘቱ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ያለበትን የቀረጥ ታሪፍና የግብር ገቢ ማግኘት አልቻለችም፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ በኦሮሚያ ፖሊስ ይጠበቅ የነበረው ኬላ ተነጥቆ ለፌዴራል ፖሊስ መስጠቱ ቅሬታ ቀስቅሷል” ሲሉ ምንጮች ያብራራሉ፡፡ የዜና ምንጮቻችን እንደሚሉት “ኬላዎቹ ያሉት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፡፡ አዲስ አበባም ቢሆን ኦሮሚያ ናት፡፡ ከኬላዎች የሚገኘው ገቢ የኦሮሚያ መሆን አለበት፡፡ ፌዴራል መንግስት በቀጥታ ኦሮሚያ ውስጥ ገብቶ የክልሉን መንግስት ጥቅም በሚነካ መልክ ጣልቃ መግባቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ቅሬታ ማስነሳቱ አይቀርም” በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
No comments:
Post a Comment