በተመስገን ደሳለኝ፡ (የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ)
ተመስገን ደሳለኝ
ተመስገን ደሳለኝ
አቤት! እንደምን ያለ ጉዞ ነው? አድካሚ፣ ፈታኝ፣ አስፈሪ፣ አደናቃፊ… ብቻ ዙሪያው በአደጋ የተሞላ ነው። ልክ እንደ ጦር ሜዳ። በእርግጥ ጦር ሜዳን በፊልም እና በቴሌቪዥን ካልሆነ ገፅ-ለገፅ አይቼ አላውቅም። ሆኖም በጣም አስፈሪ እና ከሞት ጋር ‹‹አኩኩሉ›› የመጫወት ያህል እንደሆነ ለማወቅ አይቸግረኝም።
ለዚህምነው በጦር ሜዳ ‹‹ሞት እርካሽ ነው››ሲባልግነት እንዳይመስልህ የምልህ።ምንአልባት ከጎኑ ከሻጠው ኮዳ ውሃ ያስጎነጨህ ጓደኛህ ኮዳውን ከመመለስህ በፊት ሞቶ ወይም ሊሞት ሲያጣጥር ልታገኘው ትችላለህ። ለምን? በቃ! በጦር ሜዳ ሞት ከአይነ እርግብግቢት የፈጠነ ነዋ።የጦር ሜዳን መከራ ይበልጥ የሚያበዛው ደግሞ ላለ መሞት የሚደረገው ግብግብህ ከጠላት ጋር ብቻ አለመሆኑ ነው። ከወገንም በኩል የሚነሳ የሞት መልዕክ አለና።
ለዚህምነው በጦር ሜዳ ‹‹ሞት እርካሽ ነው››ሲባልግነት እንዳይመስልህ የምልህ።ምንአልባት ከጎኑ ከሻጠው ኮዳ ውሃ ያስጎነጨህ ጓደኛህ ኮዳውን ከመመለስህ በፊት ሞቶ ወይም ሊሞት ሲያጣጥር ልታገኘው ትችላለህ። ለምን? በቃ! በጦር ሜዳ ሞት ከአይነ እርግብግቢት የፈጠነ ነዋ።የጦር ሜዳን መከራ ይበልጥ የሚያበዛው ደግሞ ላለ መሞት የሚደረገው ግብግብህ ከጠላት ጋር ብቻ አለመሆኑ ነው። ከወገንም በኩል የሚነሳ የሞት መልዕክ አለና።
እናም ድንገት ወደ ውጊያ ከመግባትህ በፊት የተጠመደ ፈንጅ ታከሽፍ ዘንድ አለቃህ ይመርጥሃል። (ወዳጄ ‹‹ይመርጥሃል›› ስልህ ለሹመት እንዳይመስልህ፣ በፈንጂ ላይ ተረማምደህ ስጋና አጥንትህ ተበጣጥሶ ለሌሎች ወታደሮች መንገድ ትጠርግ ዘንድ ነው-የመረጠህ) አየህ! በጦር ሜዳ ሞት የቅርብ ጓደኛህ ብቻ ሳይሆን ጥላህም ነው። ጥላ ደግሞ ስትሄድ ይሄዳል፣ ስትቆም ይቆማል። ሞትም እንዲያ ቅርብ ነው። ዛሬ የምተርክልህ የጉዞ ገድልም ከዚህ በማይተናነስ መልኩ በአደጋ የተሞላ ነው ስልህ እመነኝ አላጋነንኩትም። በፈንጅ የታጠረ ነው። ይህን ከጦር ሜዳው ፈንጅ ወረዳ የሚለየው እንደ ጦር ሜዳ ፈንጅ መቀበሩን የምታውቀው ጓደኛህ ተንከባሎበት ሲበጣጠስ አለማየትህ ብቻ ነው።
እዚህ በግልፅ በመንግስት ሚዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ‹‹አሁን ቀዩን መስመር አልፈሃል››፣ ‹‹11ኛው ሰዓት ላይ ደርሰሀል››… ይሉሀልና። ያን ጊዜም ሁለት ስሜቶች ይፈጠሩብሃል ‹‹መራድ›› ወይም ‹‹በጽናት መቆም››፡፡ ግና የምትጓዘው ለሀገርና ለህዝብ እስከሆነ ድረስ ለምን ትርዳለህ? ጥያቄው ይህ ነው፣ መልሱም በእጅህ ነው። ፍትህ ስትመሰረት ምንም አልነበረም። በመስራቾቿ እጅ ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን ከምንም በላይ አንድ ነገር ነበረን። አላማ የሚባል፡፡ ያ አላማ መኖሩ ነው፣ የፍትህን ጅማሮዋን ብቻ ሳይሆን መጨረሻውንም አውቀን እንድንግባ ያደረገን። እናም ስንጀምር መድረሻችንን እናውቀዋለን። መንገዳችንም በመሰናክል ናዳ የተሞላ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን፡፡
መጓዛችን አይቀሬ እንደሆነም እናውቃለን፡፡ከቶም ምንም ነገር ከመድረሻችን ሊመልሰን እንደ ማይችል እናውቃለን፡፡እስርም፣ ሞትም፣ ጫናም..፡፡ ለነገሩ እነዚህ ሁሉ ከሀገር እና ህዝብ በታች ናቸው። እናም እልሀለሁ ጉዳዩ የሀገር እስከሆነ ድረስ፣ተጠቃሚው ህዝብህ መከራውም ስለ ምትውዳት ሀገር እስከሆነ ድረስ የመረጥከውን መንገድ ይዘህ መጓዝ እንጂ የምትከፍለው ዋጋ ሊያሳስብህ አይገባም። በእርግጥ የፍትህ ፈተና ይህ ብቻ አይደለም፣ከዚህም ይሻገራል።ነባር የፍትህ አንባቢዎች እንደሚያስታውሱት ፍትህ ቀኗን ጠብቃ ለንባብ የማትበቃበት ጊዜ ነበር። ለአራት ሳምንት ያህል ያልታተመችበት ጊዜ ሁሉ አለ። በቂ የገንዘብ አቅም አልነበራትምና። በአናቱም ያች ሚጢጢዋ የፍትህ ቢሮ ከአንዴም ሁለቴ ተዘርፋለች። የሁለተኛው ዝርፊያ ለፖሊስ ቢመለክትም እስከዛሬም ድረስ ዘራፊዎቹን አየን ያለ የለም።
ሌላው ፈተና ደግሞ ከቤተሰብህ እና ከወዳጆችህ የሚመጣው ጫና ነው። ሆኖም እንዲህ አይነቱን ፈተና በቀላሉ ማለፍ ትችላለህ። ‹‹ይቅርብህ፣ ተው…›› ለሚሉህእናትና አባትህ አሊያም ሌሎች የቤተሰብ አባላት ‹‹ከሀገር አትበልጡም›› ብለህ በመመለስ ማለቴ ነው። ይህም አልገባቸው ካለ እንዲህ ስትል ዘምርላቸው፡- እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል ሀገር የሞተ እንደው ወዴት ይደረሳል… አዎን! ወዴትም አይደ እንዲሁም እንዲህ ብለህ አትፃፍ፣ መንግስት ሀይለኛ ነው፣ ፖለቲካ ኮረንቲ ነው፣ ገለመሌ ለሚሉ ወዳጅ ዘመድ ደግሞ ከህገ-መንግስቱ ውስጥ ሀሳብን ያለገደብ መግለፅ እንደምትችል የሚፈቅደውን አንቀፅ ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብላቸው። ከፍ አድርገህ… የሆነ ሆኖ ነገ ድፍን አራት አመት የሚሞላት ፍትህ እዚህ የደረሰችው በ‹‹መራድ›› እና በ‹‹መጽናት›› ወጀብ ከወዲህ ወዲያ እየተላጋች ነው። በእርግጥ እንዲህ ያለው አድካሚ እና ፈታኝ ጉዞ ነገም ይጠብቃታል።
አደጋውን አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ ከቀን ወደ ቀን የመሰናክሉ አይነት መጨመሩና መደደሩ ነው። ማን ነበር ህዝቡን ከረጅም ጉዞ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረሰው? ሙሴ ይሆን? የለም የለም የሙሴ ጉዞ ለእኛ አርዕያ አይሆነንም፡ ፡ ሙሴ የታገለው ‹‹ህዝቤን ልቀቅ›› ብሎሃል እያለ ነውና፡፡ የእኛ እንዲህ የሚል መዕልክት አስተላለፊ ‹‹ኃይለኛ›› የለውም፡፡ ያለው ይህ የኔ ትውልድ (እኔና አንተ) ነው፡፡ እናም እኛው ራሳችን ነን ‹‹በቃን! ልቀቁን›› እያልን ያለነው ወይም የምንለው፡፡ ታዲያ ማን ይሆን ህዝቡን ከረጅም ጉዞ በኋላ ‹‹ከንአን›› ያደረሰው? የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መስራቾች ናቸው ብትል አልዋሸህም፡፡ ነገሩም እንዲህ ነው፡- ከዛሬ 80 አመት በፊት CCP የተባለው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ፣ ከወቅቱ የቻይና ገዢ ፓርቲ “Kuomintang” ጋር ለህግና ለስርዓት ያስቸገሩትን በመላ ቻይና የነበሩ የጦር አበጋዞችን በትብብር ድራሻቸውን ለማጥፋት ይስማማል።
በስምምነታቸው መሰረትም በየአጥቢያቸው ትናንሽ ንጉስ ሆነው አልገዛም ያሉትን የጦር አበጋዞች ከግራና ቀኝ አጥቅተው ያጠፋሉ። ከዚህም በኋላ ኮሚኒታግ ቃሉን አጥፎ የተቆጣ ፊቱን ወደ CCP ያዞራል። ይህን ግዜ የመንግስት ሀይል ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ የገባቸው ማኦ ዜዱንግ እና ጓደኞቹ ከከተማ ወደ ገጠር ሸሹ። ዛሬ በቻይናዊያን እንደገድል የሚነገርለትን Long march (ረዥሙ ጉዞን) በዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ነው CCP የተጓዘው። የጉዞውም እርቀት 11 ሺ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ከዚህ በኋላም CCP ራሱን አጠናከረ። የጥንካሬያቸው ምንጭ ደግሞ ለአንድ አመት ያህል በፈጀው ጉዟአቸው የሚበሉት አጥተው መርዛማ ቅጠል እየበሉ ሳይቀር መጓዛቸው ብቻ ሳይሆን ከጉዞው በኋላ ያደረጉት ስር ነቀል ተሀድሶ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው CCP በድል እየገሰገሰ በሽንፈት ለቆት ወደሄደው ከተማ የተመለሰው። እነሆ ያ ፓርቲ ዛሬም በስልጣን ላይ አለ። ምን አልባት፣ ምንአልባት ግን በዛ አስቸጋሪ ጉዞ ቢበገር ኖሮ፣ ዛሬ CCPን እንኳ እኔና አንተ ምሳሌ ልናደርጋቸው ቀርቶ ቻይናውያንም አያውቁትም ነበር። ይህ ነው አይበገሬነት።
ሌላም በፈተና ከተሞላ ጉዞ በኋላ ታሪክ የሰራ ድርጅት አለ፤ ህወሓት። ህወሓት ለ17 አመት ያህል ተጉዟል። ያውም በመሳሪያ፣ በሰው ሀይል እና በስልጠና በእጅጉ ከሚበልጠው ከቀድሞ መንግስት ወታደሮች ጋር እየተዋጋ። እናም ብዙ የገደለ ሞትን ያሸንፋል እንዲሉ ህወሓትም ከዚህ ሁሉ ጉዞ በኋላ የመንግስቱን መንበር ያዘ። ነገር ግን የህወሓት ጉዞ እንደ CCP የተሳካነው ማለት አንችልም። ምክንያቱ ደግሞ ከህወሓት መስራቾች አብዛኞዎቹ ዛሬም በሌላ ረጅም፣ አሰልቺ እና ፈታኝ ጉዞ ላይ መሆናቸው ነው። አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘራዕፅዮን፣ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አወአሎም ወልዱ፣አረጋሽ አዳነ፣ አስገደ ገብረሥላሴ፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ…ህወሓትን መስርተው የ17 አመቱን ጉዞ የመሩ ናቸው። ሆኖም ዛሬም በሌላ ጉዞ ላይ ይገኛሉ። ህወሓትን ይዘን የተጓዝነው ጉዞ የስህተት ጉዞ ነው በሚል ማለቴ ነው።
እንደምራቂ ደግሞ የህወሓት የአማርኛ ተናጋሪ ክንፍ የሆነውን ብአዴንንም ብታየው ከላይ የነበረው አመራር አሁንም በአዲስ ጉዞ ላይ ነው። በእርግጥ የብአዴን ሰዎች እየተጓዙ ነው ስልህ የታምራት ላይኔንም ጉዞ ከዚህ እንዳታያይዘው፡፡ የእርሳቸው ለፅድቅ ነውና፡፡ መሰረቱም ምድራዊ ሳይሆን ሠማያዊ ነው፡፡ ምንጩም ፖለቲካ አይደለም፤ የእስር ቤት ‹‹ራዕይ›› እንጂ፡፡ ፍትህ ስትመሰረት ረጅምና የፈተና ጉዞ እንደሚጠብቃት መስራቾቿ ያውቁ እንደነበር ተነጋግረናል፡፡ አውቀውም ነው የገቡበት ብዬሀለሁ፡፡ ሆኖም ፍትህ እንዲህ ሄዳ ሄዳ ብቻ የመሆን ዕዳ ላይ ትወድቃለች የሚል እሳቤ ግን አልነበራቸውም። የሆነው ግን እንዲያ ነው። የተለያዩ የሚታዩና የማይታዩ አደጋዎችን ተቋቁማ፣ አንዳንዴም እየተቸነከረች፣ አንዳንዴም እየተሸራረፈች ዳገቱን ለመጨረስ ግብ ግብ ተያይዛለች። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ወቅት በዚህችው ፍትህ ላይ በፃፉት ፅሁፍ ‹‹ዳገት ላይ ሰው ጠፋ›› ብለው ነበር። ፕሮፍ ልክ ናቸው።
ዛሬ ሀገሬ ዳገቱን ጨርሶ ከገደሉ ስቦ የሚያወጣትን አላገኘችም። ምክንያቱ ደግሞ በብዙ የሚጠበቀው አንዳንዴም ገና ከታች፣ አንዳንዴም ከዳገቱ ወገብ እየቀረ ጣሯም መከራዋም ትውልድ ተሻጋሪ እየሆነ ነው፡፡ …እንዴት ያማል መሰለህ ትውልድ ተሻጋሪ መከራ? የእኔና የአንት ትውልድ ባለፉት ተከታታይ ትውልዶች ያልተከፈለ ዕዳ ተሸክሟል። የሸክማችን ግዝፈት መነሾም ይኸው ይመስለኛል። እንደቅርስ መከራን ማውረስ …የፍትህም ጉዞ ቢሆን ዳገቱን ለመውጣት በትግል ላይ ነው። በእርግጥ መከራው እና ድካሙ በአይነትም ሆነ በአሰቃቂነት የሚጨምረው ወደፊት በተጓዝክ ቁጥር ነው። ዳገቱን ለመጨረስ በተጓዝክ ቁጥር አደጋውም እየበዛ ይሄዳል። የታዘዘውም ያልታዘዘውም የአቅሙን መሰናክል ይፈጥርብሃል። በየቀኑ መቸንከር፣ በየቀኑም ከችንካር ወርዶ ወደፊት፣ ወደፊት፣ ወደፊት… እንዴት ፈታኝ መሰለህ? እንዴት ብርክ ፈጣሪ መሰለህ? እናም የፍትህ (የነፃ ፕሬስ) ጉዞ እንዲህ እንደዋዛ ‹‹ውሾቹ ይጮኻሉ፣ ግመሉ ጉዞውን ቀጥሎአል›› ብለህ የምታልፈው እንዳይመስልህ።
እውነታው ተቃራኒው ነውና፡፡ የሚናከስ እንጂ የሚጮህ ነገር አትሰማም። ስለዚህም ድንገት ልትነከስ ትችላለህ። ድንገትም ጉዞህ በአደጋ ይከበባል። ያኔም አማራጭ ከፊት ይቀመጣል። ‹‹ውጣ አትበለው ግን እንዲወጣ አድርገው›› የሚለው ለዘመናት ያገለገለው ቀመርም በስራ ላይ ይውላል። እመነኝ ይህን ቀመር ከተቀበልክ ተሸውደሀል። ከወጣ ወጣህ ነውና። ማን ነበር ‹‹ሀገሩ የሌለ የትም የለ›› ያለው? ተስፋዬ ገ/አብ ይሆን? ለነገሩ ስዬ አብርሃም ‹‹መሬትህን አትልቀቅ›› ሲሉ የጻፉ መስለኛል፡፡ በእርግጥ ፍትህ በአራት አመት ጉዞዋ በቂ ሊባል የሚችል ስራ ባትሰራም፣ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ሂደት የአቅሟን ያህል አስተዋፆ ማድረጓ ሊካድ የሚችል አይደለም። ከተባዳዩ አንፃር ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ለተበደሉ፣ እና ፍትህን ለተነፈጉ ድምፃቸው ሆናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ህዝባዊ ችግሮችን፣ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ግራና ቀኝ ፈትሻ አደባባይ አውላለች፡፡ ይህ ሲሆን መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ እንዳይመስልህ፡፡
ለነገሩ አንተ እዚችው ኢትዮጵያ ስላለህ ከአደጋ የፀዳ መንገድ ያለ ሊመስልህ እንደማይችል አውቃለሁ፡፡ እንዲያውም ይህ ሁኔታ የሚመሳሰለው ከኢህአዴግ ጉዞ ጋራ ነው፡፡ አዎ! ህወሓትን እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች እንደ መሰረቱት ታውቃለህ። ሞኛ ሞኙ ደርግም በቆረጡ ሰዎች (ሰባትም ሆኑ አስራ ሁለት) የታሪክ ሰሪ መንፈስ እንደሚሰፍንባቸው አላወቅምና እስከውድቀቱ ዋዜማ ድረስ ‹‹እፍኝ የማይሞሉ ወንበዴዎች…›› በሚል ፕሮፓጋንዳ ጉልበቱን ጨረሰ። (ይህ የእኔ ትንተና እንዳይመስልህ። ‹‹የትውልድ ሀላፊነትን የተቀበሉ ቆራጦች አዲስ ታሪክ ሰሪ መንፈስ ይጫናቸዋል›› የሚሉት ታሪክ አዋቂ ፈላስፎች ናቸውና።) እመነኝ የህወሓትም ብርታት ከዚህ እንጂ ከሱዳን ጠንቋይ የመጣ አይደለም። ማን ያውቃል የፍትህ ጉዞስ ነፃውን ፕሬስን የት እንደሚያደርሰው? እናም ያ ቀን ለቀጣዩ ትውልድ ሲል ያጥር ዘንድ እመኛለሁ፡፡ መመኘት ብቻም አይደለም እንዲህም እላለሁ አቤቱ ታሪክ ሰሪ መንፈስ ሆይ ወዴትነህ? የሆነ ሆኖ ከመጋረጃው ጀርባ ባለችው ኢትዮጵያ እና በኢቲቪ በምትመለከታት ኢትዮጵያ ብዙ ርቀት አለ።
የኢቲቪ ኢትዮጵያ በየአመቱ 11 በመቶ የምታድግ፣ ነፃ ፕሬስ እንደ አሸን የፈላባት፣ ብሔር ብሔረሰቦች በደስታ እና በተድላ ተፋቅረው ‹‹ያምቡሌ››ን የሚጨፍሩባት፣ ፍትህ ርትዕ የነገሰባት፣ እውነትን የሚያገለግል ጋዜጠኛ የሚከበርባት፣ የስራ እድል የተትረፈረፈባት… ወዘተተርፈ ነች። እንዳልኩህ ይች ኢትዮጵያ የኢቲቪ እንጂ እኔና አንተ የምናውቃት፣ ኢህአዴግ የሚያስተዳድራት አይደለችም። እኔና አንተ የምናውቃት፣ ከነገ-ዛሬ… እያልን የምንሰጋባት፣ ዜጐቿ ‹‹ውጡ ይህ ሀገራችሁ አይደለም›› የሚባሉባት፣ ጋዜጠኞች አሸባሪ እየተባሉ እንደ በግ ተጎትተው የሚታሰሩባት ወይም ሀገር ለቀው የሚሰደዱባት፣ ህፃናት በረሃብ እንደቅጠል የሚረግፉበት፣ ስራ እጥ የነገሰበት፣ የፍትህ ስርዓቱ ለመንግስት ጠባቂ መልዕክ የሆነበት፣ ካድሬ ያሸውን የሚያደርግባት፣ የመደራጀትና የመሰለፍ መብት የተነፈገባት፣ ሰብዓዊ መብት የሚጣስባት፣ አቤት! የሚባልበት ዳኛ የሌለባት፣… ኢትዮጵያን ነው የምናውቃት።
የፍትህ ጉዞንም በእሾህ የተከበበ ያደረገው ይህ ነው። ለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን ‹‹ጉዞአችን ቀራኒዮ›› ድረስ ነው ያልነው። በእርግጥ ላለመሰናከል መበርታት እንደአለብን ብናውቅም ቀራኒዮ ከዚህ ምን ያህል እንደሚርቅ ግን ማናችንም አናውቅም፤ ዛሬ ምሽት እንድረስ ወይም ነገ አሊያም የሚቀጥለው አመት የሚያውቀው ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው። ምንም አይነት እርምጃ የመውሰድ ምርጫው በገዥው ፓርቲ እጅ ነው። አዎን! ውሳኔው በእጁ ነው። ወይ ፍትህን አጥፍቶ የሚመጣውን በፀጋ መቀበል፤ አሊያም የፍትህን ጎምዛዛ ሂስ ውጦ መታረም። ከዚህ በተጨማሪም ፍትህን መዝጋት አሊያም እንድትዘጋ በስውር መዳፍ መደፍጠጥ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ላይ የመጨረሻውን ሚስማር መምታት ነው፡፡ ሚስማር ደግሞ የሚፈነቅለው ነገር ሊኖር እንደሚችል ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ እስከዛው ድረስ ግን እኛ እንፅፋለን። የምንፅፈው የሀገሪቱ ህገ-መንግስት መፃፍ ትችላላችሁ ሲል መብታችንን ስላረጋገጠልን ነው። እምንከተለውም ሆነ እምንቀበለው ህገ-መንግስቱን ብቻ እንጂ የአምባገነን ባለስልጣናትን ተግሳፅ አይደለም።
አንተም ይህን ልታደርግ ይገባሃል። ሀሳብህን ያለገደብ መግለፅ ትችላለህ ተብለሀልና ይህንኑ መተግበር አለብህ። ያን ጊዜም ነው ነፃነትህ በእጅህ የምትሆነው። ያንጊዜም ነው ሀገር እና ህዝብን ምታገለግለወ። አዎን ፍትህም የምታገለግለው ሀገርንና ህዝብን እንጂ መንግስትን ወይም ተቀናቃኞቹን ባለመሆኑ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ከመስመራችን አንድ ኢንች አንወጣም። ትላንት ጎዞአችን ቀራኒዮ ድረስ ነው ብዬሀለሁ፡፡ ዛሬም እደግመዋለው ‹‹ቀራኒዮ…ድረስ ነው›› የሆነ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ ላይ ከከፍተኛ ባለስልጣኖች ጀምሮ እስከ ተራው ካድሬ ድረስ በሚቆጠሩ አምባገነኖች የተሰነዘሩ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን፣ እንዲሁም ለቁጥር አዳጋች የሆኑ የሀሰት ክሶችን ብዘረዝር ቢያንስ ለታሪክ ይጠቅም ነበር። ሆኖም እንኳን አንድ አምድ፣ ሙሉ ጋዜጣውም አይበቃምና እናልፈዋለን፡፡ ነገር ግን እዚህች ጋ ስደርስ አንድ ነገር ትዝ ስላለኝ ላጫውትህ።
በዚሁ ዓመት በወርሃ ታህሳስ ለአንድ ሳምንት ያህል በፍትህ አዘጋጆች ላይ የደህንነት አባላት ነን ያሉ ሰዎች 24 ሰዓት ሙሉ እየተከታተሉ ያስጨንቁ ነበር። ሁኔታውም ከቀን ወደ ቀን እየከረረ እና እየበረታ ሲሄድ ሁሉም አዘጋጆች አሲምባ ገቡ። አሲምባ ግን የት ነው? ትርጓሜውስ ምን ማለት ይሆን? መቼም በያ ትውልድ ዘመን በነበሩ ወጣቶች ልብ ውስጥ ኢህአፓ የሚባል ፓርቲ ነግሶ እንደነበረ ታስታውሰዋለህ። ደህና! ኢህአፓም ሰራዊቱን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ኢሮብ የሚባል ቦታ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ እንዲሰፍሩ አደረገ። ያ ተራራም አሲምባ ይባላል። ትርጓሜውም ‹‹ቀዩ ተራራ›› ማለት ነው። እናም አሲምባ ለብዙ ወጣቶች ከሞት የማምለጫ ምሽግ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በእርግጥም እድል ቀንቶአቸው በርካታ የደርግ ኬላዎችን አልፈው አሲምባ መድረስ የቻሉ ወጣቶች ከሞት ተርፈዋል። አሲምባ ማለት በያ ትውልድ ይህ ነው። ወደ ፍትህ አሲምባ ደግሞ እንምጣ።
ከላይ እንዳልኩህ በነዛ ሰባት የመከራ ቀናት፣ ክትትሉና ጫናው አደገኛ በመሆኑ ሁለቱ የጋዜጣው አዘጋጆች ‹‹በጋራ ለቆምንለት የፕሬስ ነፃነት፣ በጋራ ዋጋ እንከፍልለታለን›› አሉና በብቸኝነት ኖርበት የነበረችውን አንድ ክፍል ቤት ተዳበሉ። ከዚህ በኋላም ክትትሉና ማስፈራሪያው በጋራ ሆነ፤ የእኛም እንቅስቃሴ ተገደበ፣ እንደጋዜጠኛ ከወዲህ ወዲያ ተሯሩጦ መስራት የማይሞከር ሆነ፡፡ ሎአችንም ከቤት ወደቢሮ፤ከቢሮ ወደቤት ሆነ፡፡ይህን ሁኔታ ቅርብ ሆነው የተከታተሉ ወዳጆቻችንም ያችን በጋራ የሙጢኝ ያልናትን የኔን ቤት ‹‹አሲምባ›› ሲሉ የበረሃ ስም ሰጧት። እነሆም በግልፅ የነበረው የደህንነት ከበባው ቢነሳም (ምንአልባት በስውር ሆኖ ሊሆን ይችላል) አሲምባ ግን ዛሬም የአዘጋጆቹ መኖሪያ ቤት መሆኗን ቀጥላለች፡፡ በእርግጥ አሲምባን መኖሪያ ቤት ከማለት ‹‹ምሽግ›› ማለቱ የሚቀል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአሲምባ ህይወት ጉራማይሌ ነው።
ከምቾት የተፋታ፣ ከደስታ የተጋባ ነውና፡፡ በምግብ በኩል በአሲምባ አብስሎ ለመብላት የሚያስችልምንም አይነት ቁስ ስለሌለ ብዙውን ጊዜ ለእራት የሚሆነው ሙዝ በዳቦ ሲሆን፣ እንዳንዴም ጫናው ሲበረታ እንደተራቡ ማደር ይከተላል። (አሳዳጆቻችን ግን የሚያሳድዱን እራት በልተው ይሆን ወይም ሳይበሉ የሚያውቀው የመደባቸው አካል ብቻ ነው) ይህም ሆኖ በአሲምባ በጊዜ የሚተኛ የለም፡፡ ቶሎ ከተተኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ ነው፡፡ አሊያም እስከ ንጋት 11 ሰዓት ይመሻል። ይህ ግን አሰልቺ አንዳይመስልህ። እንዲያውም በጣም ጣፋጭ ነው፡፡እንዴትስ ጣፋጭ አይሆን? በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዱላ ቀረሽ ክርክር እና ውይይት እየተደረገ የሚቆይ ምሽት? እናም በአሲምባ ሲነጋ መንጋቱን የምታውቀው ከጎዳናው ላይ በሚሰማው የታክሲ ረዳቶች ተሳፋሪዎቻቸውን በሚጣሩበት ድምፅ ነው። (ስለአሲምባ ሌላ ጊዜ በስፋት እናወጋለን፡፡ አሁን ኑሮአቸውን በአሲም ባደረጉ አዘጋጆች ስለምትዘጋጀው የ‹‹ፍትህ›› ገዳለ ገደል ጉዞን ቅኝት ወደመደምደሙ እንመለስ፡፡) አዎ! እጃችሁን ከፍትህ አንሱ ፍትህን ማሸነፍም ሆነ መጨፍለቅ አይቻልምና። በነገራችን ላይ ፍትህ ስል አዘጋጆቹን እንዳይመስላችሁ፣ መንፈሱን ነው።
የመናገር፣ የመተቸት፣ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መንፈስን ማንም አይገድበውም። ማንም። የፍትህን መንፈስ (ይህን መንፈስ) ማሸነፍ ደርግን የማሸነፍ ያህል ቀላል አይደለም። ይህ ማስፈራሪያ አይደለም። ህዝብ አይሸነፍም ማለት እንጂ። መቼም ይሁን መቼ፣ የትም ይሁን የት ህዝብ ተሸንፎ አያውቅም። እናም ፍትህን አጥፍቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻ ይኑር ማለት ትውልድን ከማጥፋት ወንጀል በምንም ሊለይ አይችልም። ሊያንስምም አይችልም። ስለዚህም በአገሪቱ ህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዳለን ሁሉ፣ የምንሰብከውም በህገ-መንግስቱ በተረጋገጠው መብታችን ብቻ እንደሆነ እና ይህንን መብትም ሌሎችም እንዲጠቀሙበት የማበረታት ሙሉ መብት እንዳለን አውቃችሁ ልታከብሩልን ይገባል። …የሆነ ሆኖ የፍትህ ቤተሰቦች እየከፈሉ ያለው ዋጋ ለሀገር መከፈል ካለበት አንፃር ከአየነው በጣም ጥቂቱን ነው። ምክንያቱም ለዚህች ሀገር በርካቶች የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለው አልፈዋልና።
በጎዳና ላይ በጥይት ያለቁት ወንድም እና እህቶቻችን ዛሬ እኛ እያቀነቀንን ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ነው። ከታሪካችን እንደተረዳነውም ካልን እልፍ አላፍት መስዋዕቶች ‹‹ሀገሬን…›› ሲሉ አልፈዋል። ለዳር ድንበር መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን ከፍለዋል። ለዚህም ይመስለኛል አሉላ አባነጋን የመሳሰሉ የሀገር አንድነት አቀንቃኝ ጠላቶቻችን ተሸንፈው ከሀገራችን ሲወጡ ‹የረገጣችሁት አፈር ላይ የወንድሞቻችን ደም ፈሶአልና ከጫማችሁ አራግፉ›› ሲሉ ያስገደዱት። ወዳጄ! ይህን እየፃፍኩልህ ሳለ ፍትህን የከበባት አደጋ ከመቼውም ጊዜ የከፋ ሆኗል።
ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እስከ አይጋ ፎረሙና አዲስ ዘመን የተሰኙ ‹‹ሎሌ›› ሚዲያዎች ከእነ ጭፍሮቻቸው የማሸማቀቅ፣ የመወንጀል፣ የማስፈራራት፣ የማስጨነቅ ዘመቻቸውን በተለያየ ግንባር ከፍተውብናል። እነዚህ ሚዲዎች ዛሬ እየፈጠሩ የሚለጥፉብንን የሀሰት ውንጀላዎች ነገ ደግሞ ማስረጃ አጠናከርንበት ሊሉ እንደሚችሉ ማንም ያውቃል። በፍትህ በኩል ግን ዛሬም እንደቀድሞ ለስደት የተዘጋጀ እግር እና አጎብዳጅ አንገት እንደሌለ ከሳሾቻችን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
No comments:
Post a Comment