ኢሳት
ዜና:-
ይህን ያስታወቁት የአፍሪካ የሲፒጄ አስተባባሪ የሆኑት ሙሀመድ ኬይታ በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ባወጡት ጽሁፍ
ነው። ሙሀመድ ኬይታ የአፍሪካ ነጻ ሚዲያ ችገሮች በሚል ርእስ ባወጡት ጽሁፍ ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ ፣
በነጻው ፕሬስ ላይ የሚደርሰው አፈናም በዚያው ልክ እያደገ ነው ብለዋል። በአፍሪካ ውስጥ የሚካሄደውን ልማት
የሚዘግቡ ጋዜጠኖች ፣ ስለ ሙስና፣ እና የውጭ አገር ባለሀብቶች ስለሚፈጽሙት አስነዋሪ ተግባር ሲዘግቡ ይዋከባሉ
የሚሉት ኬይታ፣ ምእራባዊያን በአፍሪካ ዲሞክራሲ ተስፋ በመቁረጣቸው የልማት እርዳታቸውን ድህነትን በመቅረፍና
በመረጋጋት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው ገልጠዋል።
ትናንት ይላሉ ኬይታ ትናንት ምእራባዊያን
የሩዋንዳውን ፖል ካጋሜና የኢትዮጵያውን መለስ ዜናዊ የፖለቲካና የማህበራዊ ታሀድሶ አራማጅ በማለት ያሞካሹዋቸው
ነበር፣ ዛሬ ደግሞ እነዚህን መሪዎች የኢኮኖሚ እድገት ያመጡና ሰላምና መረጋጋትን ያሰፈኑ በማለት ያደንቋቸዋል፤
ይሁን እንጅ እነዚህ መሪዎች የተባሉትን ውጤቶች ያስመዘገቡት በአገራቸው ውስጥ ያሉትን ብሄራዊ ተቋማትና ነጻውን
ፕሬስ በቁጥጥርራቸው ስር አድርገው መሆኑን ይዘነጉታል ብለዋል።
በአፍሪካ ውስጥ ሊመታየው የፕሬስ አፈና
በአንድ በኩል ቻይናን ተጠያቂ ያደረጉት ኬይታ ፣ ከሶስት አመታት በፊት ቻይና እና የአፍሪካ መንግስታት ሚዲያዎች
ሁሉ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንዲሰለፍና አዎንታዊ ነገሮች ብቻ እንዲዘገቡ መስማማታቸውን ገልጠዋል። ይህ እይነቱ
አቋም ከአፍሪካ አገሮች በደንብ የሚንጸባረቀው የምእራባዊያንን እርዳታ በገፍ በምታገኘው እና የቻይና ዋነኛ የንግድ
ሸሪክ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ያሉት ሞሀመድ ኬይታ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ እስር ቤቶች ልክ እንደ ቻይና እስር ቤቶች
ሁሉ የተሞሉት በጋዜጠኞችና በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ነው ሲሉ አክለዋል።
ጻሀፊው በኢትዮጵያ
ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ አየር እጅግ የሚረብሽ መሆኑን አውስተዋል። በ19 80ዎቹ የመንግስቱ ሀይለማርያም
አምባገነን መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ረሀብ ሲከሰት ለመደበቅ ቢሞክርም አለማቀፍ ጋዜጠኞች በስፍራው በመገኘት
እውነታውን በማጋለጣቸው እርዳታ ሊደርስ ቻለ፣ ከሶስት አስርት በሁዋላ ደግሞ ኢትዮጵያ አሁንም በማህበራዊ ቀውስ እና
በግጭት እየታመሰች ነው፣ ይሁን እንጅ ዛሬም ጋዜጠኞች ወደ እነዚህ ቦታዎች ገብተው እንዳይዘግቡ እገዳ
ተጥሎባቸዋል፤ ይህን ቢያደርጉ በመንግስት አሸባሪ ጋዜጠኞች ተብለው ለእስር ይዳረጋሉ ሲሉ አትተዋል።
የእርዳታ
ድርጅቶች በኢትዮጵያ አለውን እውነታ ለመግለጽ እንደተሳናቸው የገለጡት ኬይታ፣ የሲቪል ሶሳይቲው፣ ነጻው ፕሬስና
ተቃዋሚው በተዳከመበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የውጭ እርዳታ ለበጎ ምግባር መዋሉን እና አለመዋሉን ለማረጋገጥ
አይቻልም ያሉት ኬይታ፣ በሩዋንዳ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ መሆኑን ገልጠዋል።
የቻይና ኢንቨስትመንት
በአፍሪካ ምንም አይነት ነጻ የሚባል ጋዜጣ እንዳይኖር እያደረገ በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ
በአፍሪካ ውስጥ ተገኘ ስለሚባለው የኢኮኖሚ እድገት አሀዝ፣ ስለ ስራ አጥነት፣ የገንዘብ ግሽበት፣ ስለማህበራዊና
ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሚዛናዊና ገለልተኛ ሪፖርት የሚያቀረቡ የአፍሪካ ፕሬሶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋሉ የሚሉት
ኬይታ፣ ለአፍሪካ ፕሬስ እድገት የፖለቲካ እና ማህበራዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ ሲሉ ደምድመዋል። ሲፒጄ በኢትዮጵያ ያለውን የፕሬስ አፈና በተደጋጋሚ የሚያጋልጥ ድርጅት ነው።
No comments:
Post a Comment