Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 15, 2012

በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩት እነ አንዱዓለም አራጌ ለፍርድ ተቀጠሩ

 By Reporter
                                  
 

የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና ሌሎች ማስረጃዎችን አቅርበው ጨረሱ

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ ከመሠረተባቸው 24 ተጠርጣሪዎች መካከል ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው በመከታተል ላይ ያሉት አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ፣ ስምንት ተጠርጣሪዎች ሚያዝያ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አሰምተው በመጨረሳቸው ለፍርድ ተቀጠሩ፡፡ የሰዎች መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው ከጨረሱ በኋላ፣ የኦዲዮና የቪዲዮ መከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ለማሰማት ለሚያዝያ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. የተቀጠሩት ተጠርጣሪዎች አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባካሄዳቸው ስብሰባዎች ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች የሚመለከት ማስረጃ እንደሚያቀርቡና ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ያደረጓቸው ንግግሮች የሰሜን አፍሪካ አገሮች ያደረጉትን አመፅ የሚያራምዱ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ ለሰላም የቆሙ መሆናቸውን የሚያስረዱ መሆናቸውን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በጭብጥነት አስይዘዋል፡፡

እንዲሁም ክንፈሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የግንቦት 7 ድርጅት አራማጆች መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረበውን ማስረጃ የሚያስተባብል መሆኑንም በጭብጥነት አስመዝግበዋል፡፡

የቀረበው የኦዲዮና የቪዲዮ ማስረጃ አቶ አንዱዓለም አራጌ ያደረጉት ባለስምንት ነጥብ ንግግርን የሚገልጽ ሲሆን፣ “በዓረቡ ዓለም የተጀመረው አብዮት መነሻውና ኢትዮጵያ ከዚህ ምን ትማራለች? ምን እናድርግ?” በማለት ሁለቱን የሚያነፃፅር ነው፡፡ በዓረብ አገር ያሉ ዜጎች ግፍና ጭቆናው ስላስመረራቸው ለአመፅ መውጣታቸውን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያም ከዚያ ያነሰ ነገር አለመኖሩን የሚያስረዳ ነው፡፡

በዓረቡ አገር ፌስቡክ ትልቅ ሚና መጫወቱን የሚተነትነው የአቶ አንዱዓለም ንግግር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ነገር ግን ጭቆናውና ግፉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለትግል እንደሚያነሳሳው፣ ሞትን መድፈር ፍርኃትን መቅበር ማለት መሆኑንና ሁሉንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ያብራራል፡፡

የዓረቡን ዓለም ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረጉ እንደሚከብድ፣ ነገር ግን የሥነ ልቦና ዝግጅት እንደሚያስፈልግ፣ መታገልና መደራጀት አስፈላጊ መሆኑን በንግግራቸው አስተላልፈዋል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባደረገው ንግግር የተቀጣጠለን ዲሞክራሲ ፖሊስና ሠራዊት እንደማያስቆሙት በመጠቆም፣ በዚህም ምክንያት በአፍሪካ ሦስት አገሮች ሦስት መሪዎች በግዳጅ ከሥልጣናቸው መወገዳቸውን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያም ከአፍሪካ አገሮች እንደማታንስ አብራርቷል፡፡

ማስረጃው 2004 ዓ.ም. ወደ ለውጥ የሚገባበት ወቅት መሆን እንዳለበት በመግለጽ ላይ እያለ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች “ይበቃናል” በማለት ሲያስቆሙ፣ ዓቃቤ ሕግ ሙሉውን ቃል እንዲያሰሙ ቢቃወምም፣ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ “የማትፈልጉት ላይ ስትደርሱ ማስቆም ትችላላችሁ” ብሎ ብይን ስለሰጠበት ተቃውሞው ተቀባይነት ባለማግኘቱ መደመጡ ቆሟል፡፡

አቶ አንዱዓለምና ጋዜጠኛ እስክንድር ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ከተሰብሳቢዎቹ የተሰጠው አስተያየት የታየና የተሰማ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ፣ “2004 ርቆብናል፤ ከእንግዲህ እየፈራን አንናገርም፤” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡

መስከረም 21 ቀን 2004 ዓ.ም. መኢዴፓ ጠርቶት ስለነበረው አገራዊ ሰላማዊ ሠልፍ በሚመለከት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በፍላሽ ይዘውት የመጡት ኦዲዮና ቪዲዮ ማስረጃ ሲከፈት ሌላ ሆኖ በመገኘቱ፣ ፍርድ ቤቱ ስህተቱ የእነሱ መሆኑን በመግለጽ ማስረጃን በሚመለከት መጠናቀቁን አስታውቆ፣ ሁለቱም ወገኖች (ዓቃቤ ሕግና ተጠርጣሪዎቹ) የክርክር ማቆሚያ ንግግር ከቀጠሮ በፊት እንዲያቀርቡ አዟል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሌላው የተመለከተው ጉዳይ አቶ አንዱዓለም አራጌ በማረሚያ ቤት ውስጥ በአንድ ፍርደኛ በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ማረሚያ ቤቱ በደብዳቢው ላይ “አመክሮ መከልከልና ቤተሰቡ እንዳይጠይቀው አድርጌያለሁ” ያለውን በማረጋገጥ፣ አቶ አንዱዓለም የፈለጉትን ሕክምና እንዲያገኙ በማዘዝ፣ በመዝገቡ ላይ ፍርድ ለመስጠት ለግንቦት 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment