ኢሳት
ዜና:-
በጋሞጎፋ ዞን በመለኮዛ ወረዳ በለሀ ከተማ ከአራት ቀናት በፊት በተነሳው ረብሻ ልዩ የፌደራል ፖሊስ እና
የመከላከያ አባላት ህዝቡ ላይ በከፈቱት ተኩስ ቁጥሩ በትክክል ለማወቅ ያልተቻለ በርካታ ሰዎች ሙትና ቁስለኛ
ሆነዋል። አንዳንድ የአካባቢው ምንጮች የሟቾችን ቁጥር 10 ሲያደርሱት ሌሎች ደግሞ ወደ 5 ዝቅ ያደርጉታል።
በተመሳሳይም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁስለኞች ሆነዋል፣ ድብደባ የደረሰባቸው እና ለእስር የተዳረጉትም ቁጥራቸው
እጅግ በርካታ ነው ተብሎአል።
ግጭቱ የተነሳው ከአከላለል፣ ከማዳበሪያና ከወረዳ ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ
መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል። በጎፋ ዞን የሚኖሩት የመሎ ብሄረሰብ አባላት በጎፋ ዞን ውስጥ መጠቃለላችን ተገቢ
አይደለም የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ለማወቅ ተችሎአል። እጅግ የሚያሳዝነው ወታደሮቹ ነዋሪዎችን ከገደሉ በሁዋላ ህዝቡ
አስከሬን እንዳይወሰድ መከልከላቸው ነው ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለኢሳት
ገልጠዋል።
ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ወታደሮች ከተማዋን መውረራቸው
ታውቋል። ጉዳዩን በማስመልከት የደቡብ ክልል ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁን እንጅ
የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ተወካይ ግጭት የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ግጭቱ መከሰቱን ውጥረቱ አሁንም መኖሩን
አረጋግጠውልናል። አቶ ዳንኤል እንዳሉት በደቡብ ክልል ከአከላል ጋር በተያያዘ የሚታየው ግጭት የቆና እና እየቀጠለ
ሊሄድ የሚችል ነገር ነው ይላሉ.
No comments:
Post a Comment