By Ethiopian reporter
ከሦስት ሳምንታት በፊት በበርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በአያቷ ስትደበደብ የታየችው ሕፃን በድጋሚ ስትደበደብ
ተገኘች፡፡ በወቅቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ወ/ሮ ሐሊማት መሐመድ በተባሉት አያቷ ስትደበደብ የምትታየው ሕፃን፣ በድጋሚ
ትናንትና ወሎ ሰፈር አካባቢ በወንድ አያቷ ተደብድባ ፖሊስ ጣቢያ መሄዷ ታውቋል፡፡
አያቷ ወሎ ሠፈር ካለው ዳንዲቦሩ ትምህርት ቤት ጀርባ በሚገኘው ሐምሌ 19 ሕፃናት መዋያ የጥበቃ ሠራተኛ ሲሆኑ፣
ትናንትና ከሰዓት በኋላ የሕፃናት መዋያው በር ላይ ሲደበድቧት ተገኝተዋል፡፡
አቶ ኃይለ ሚካኤል ጌታቸው የተባለ ቧንቧ ሠራተኛ ግለሰቡ ከሕፃናት መዋያው አንጠልጥለዋት ሲወጡ አይቷል፡፡ አቶ ኃይለ ሚካኤል እንዳለው፣ ‹‹ሕፃኗ በመጀመርያ የሕፃናት መዋያው በር ላይ ነበረች፡፡ ከዚያም ተመልሳ ገብታለች፡፡ በመቅጽበትም ግለሰቡ በዱላ እየደበደቧት አንጥልጥለው አወጧት፤›› በማለት በድርጊቱ የተደናገጠው አቶ ኃይለ ሚካኤል፣ ሕፃኗ ምንም ብታጠፋ ልጅ በመሆኗ ከመደብደብ ይልቅ ቢመክሯት እንደሚሻል ለግለሰቡ ቢገልጽላቸውም፣ ‹‹ልጄ ናት ምን አገባህ፤›› እንዳሉት ተናግሯል፡፡ በነገሩ የተበሳጨው አቶ ኃይለ ሚካኤል ከግለሰቡ ዱላውን እንደተቀበላቸውና በወቅቱ ሕፃኗ መሬት ላይ ስትንፈራገጥ እንደነበር ገልጿል፡፡
ከዚያም አቶ ኃይለ ሚካኤል ከሌላ መንገደኛ ጋር ተባብሮ ደብዳቢ ግለሰቡን ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እያመሩ ሳለ፣ መንገደኛው ሕፃኗን ከዚህ በፊት በቪዲዮ እንዳያት ለደብዳቢው ሲገልጽላቸው፣ ልጅቷ እሷ መሆኗንና በጣም እንዳስቸገረቻቸው መግለጻቸውን አቶ ኃይለ ሚካኤል አስታውቋል፡፡ መንገደኛው ደብዳቢውን ግለሰብ ቄራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዳቸው ሲሆን፣ ቃላቸውን ሰጥተው በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ቃላቸውን የተቀበለው ፖሊስ እንዳስረዳው፣ ልጅቷ ከአያቷ ጋር ለመጫወት የሕፃናት መዋያው የሄደች ሲሆን፣ በትምህርት ቤት ውስጥ የነበረውን ስብሰባ ረብሻለች በሚል እንዳስወጧት ግለሰቡ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረው እንደሆነ ገልጾ፣ በልጅቷ ላይ ምንም የሚታይ ጉዳት እንደሌለ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡
በሕፃኗ ላይ በመጀመርያ በተፈጸመው ድብደባ ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት ወ/ሮ ሐሊማት መሐመድና ወጣት ሜሮን አስናቀ ባለፈው ሐሙስ መፈታታቸው ታውቋል፡፡ ሕፃኗ አሁን ወደደበደቧት አያቷ ዘንድ የሄደችው የሚያሳድጓት ወ/ሮ ሐሊማት መሐመድ በመታሰራቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕፃኗ ትምህርቷን ማቋረጧን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንድትሰጠን ወጣት ሜሮንን ብናነጋግራትም፣ በፖሊስ የተያዘ ነገር ስለሆነ ምንም መናገር እንደማትፈልግ ገልጻለች፡፡
No comments:
Post a Comment