By Abe Tockichaw
አንድ
ያው እንደሚታወቀው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፍቅር ከወደቅሁኝ ቆይቻለሁ። ስለዚህ ነጋ ጠባ ኢቲቪን ብጠቅስብዎ አየሰልቹ። ዛሬም “ቸር ያሳደርከኝ ቸር አውለኝ፣ ከተናግሮ አናጋሪ አገናኘኝ” ብዬ ፀሎት ካደረስኩ በኋላ መጀመሪያ
ያገኘሁትት የኢቲቪ ዜና አንባቢን ነበር። ባትሰማኝም “ደህና አደርሽ እግዚአብሄር ይመስገን” ብዬ ተቀበልኳት።
እርሷም ዜናዋን ቀጠለች።
“የፍትህ ሳምንት በኢትዮጵያ ሊከበር መሆኑ ተገለጠ…” አለችኝ። እውነትሽን ነው? ፍትህ …ፍትህ… ፍትህ የቱ…?
ብላት ግዜ “አቶ ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጡት ከሆነ የፍትህ ስርአቱ በሀገራችን እየተሻሻለ መጥቷል።” ስትል
ጨመረችልኝ። እሰይ ከተናግሮ አናጋሪ አገናኘኝ ብዬው አይደል እንዲህ ነው እንጂ ጌታዬ ተመስገን ብዬ የፍትህ
ስርዓቱን በረከቶች እንዳመጣልኝ መቁጠር ጀመርኩ።
የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ልጅ “ፍትህ ውብሸት” ይባላል። አራት አመት ቢሞላው ነው። አባቱ “አሸባርከን” ተብሎ
ታስሯል። ውብሸት በታሰረበት ወቅት አቶ ዘላለም፣ ሂሩት ክፍሌ እና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙም አብረው ታስረዋል።
እናም በተሻሻለው የፍትህ ስርዓት መሰረት አስራ ምናምን አመት እስር እንዲሁም፤ የቦንድ መግዣ ከሰላሳ አምስት
እስከ ሃምሳ ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ታድያ በቅርቡ ምን ሰማሁ መሰላችሁ። ለነዚህ ወዳጆቻችን መፅሀፍ ወደ
ቃሊቲ ብትልኩላቸው፤ ከመግባቱ በፊት ለዚሁ ስራ የተመደበ ሰው “ሙልጭ አድርጎ” ያነበዋል። ከዛም በውስጡ ምንም ክፉ
ቃል አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ያሳልፍላቸዋል። እንዲህ ነው እንጂ የፍትህ ስርዓት መሻሻል ብለው ይከተሉኝ።
(እዚህ ላይ ርዮት አለሙ ጡቷ አካባቢ እየተሰማት ላለው ህመም ህክምና ጠይቃ “ፓራሲታሞል ይበቃሻል” ተብላ በህመም
ስትሰቃይ “አረ የፍትህ ያለ” እያለች እንደነበር ማንሳት እችል ነበር ግን ገና በቁጥር አንድ እንዲህ ያለ ሀዘን
አላሰማዎትም ብዬ ነው)
ሁለት
ወጣቱ ፖለቲከኛ ናትናኤል “አሸባሪ” ተብሎ ከታሰረ በኋላ በምርመራ ላይ የደረሰበትን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ነበር። ርቃኑን በማድረግ እጁን ወደላይ አስረው ቀዝቃዛ ውሃ በላዩ ላይ እየተቸለሰበት ለሶስት ቀናት ምግብ ተከልክሎ
መከራውን ሲያይ እንደከረመ። ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ምን አለው… “እንደው ከጀመርክ እናስጨርስህ ብለን
እንጂ እኛ ይሄንን ልንሰማ አልተሰየምንም” ብሎት እርፍ። ፍክንያቱም የፍትህ ስርዓቱ ተሻሽሏላ።
ሶስት
አቶ አንዷለም አራጌ በቃሊቲ መታሰሪያ ቤት ታስሮ የከሳሾቹን ፍርድ እየተጠባበቀ ይገኛል። በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ፍረደኛ ሰው ፍርዱን ከሚጠባበቅ ሰው ጋር አይቀላቀልም። ለእነ አንዷለም አራጌ ሲሆን ግን የፍትህ ስርዓቱ ይሻሻላል። በዚህም መሰረት በአደገኛ ወንጀል አደገኛ ፍርድ
የተፈረደበት አደገኛ ሰው እነ አንዷለምን ተቀላቀላቸው። ከተቀላቀለም በኋላ አደገኛ በሆነ መልኩ አቶ አንዷለምን
ደበደው። የፍርድ ቤቱ ምላሽ ምን እንደሆነ አልሰማንም! “የፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ውጤት ነው” መባሉ ግን አይቀርም።
አራት
ዜና አንባቢቱ እንደነገረችኝ ከሆነ የፍትህ ስርዓቱ ተሻሽሏል። ብለው የተናገሩት የፌደራል ፖሊሱ አቶ ወርቅነህ
ገበየሁ ናቸው። እኒህን ሰው በምን መሰላችሁ የማስታውሳቸው…? ያኔ ገና መንግስት፤ “ሽብርተኝነት ሽብርተኝነት”
መጫወት ከመጀመሩ በፊት እስክንድር ነጋን ቢሯቸው ድረስ በፖሊሶች አሳግተው ወሰደውት ነበር። ልብ አድርጉልኝ ፖሊሶቹ
መጥሪያ ወረቀት እንኳ አልያዙም። እንኳንስ ወረቀት ለመጥሪያ የሚሆን ፉጨትም አላፏጩለትም። እስክንድር ሀገር ሰላም
ብሎ ቁጭ ካለበት ኢንተርኔት ካፌ መጡ አንጠልጥለው ሜክሲኮ አደባባይ ከሚገኘው አቶ ወርቅነህ ቢሮ ወሰዱት። ታድያ
እርሳቸው ምን ቢሉት ጥሩ ነው…?
“በዘጠና ሰባቱ ምርጫ የደሀ ልጅ ተገድሏል። አሁን ግን የደሀ ልጅ አይገደልም። አንድ ነገር ኮሽ ቢል መጀመሪያ
ርምጃ የሚወሰደው አንተ ላይ ነው። እርምጃው እስር እንዳይመስልህ እንደፋሀለን” አላሉትም መሰላችሁ! አይገረሙ ይሄ
የፍትህ ስርአቱ መሻሻል መገለጫ ነው። እንግዲህ ሰሞኑ የፍትህ ሳምንት በኢትዮጵያ የሚከበርበት ሰሞን ነው። ልብ አድርጉ የሚቀበርበት አይደለም ቀብሩ
ትንሽ ቆይቷል። እናም መልካም የፍትህ ሳምንት ልመኝልዎት። እንዲህ ነው እንጂ ስላቅ አይሉኝም!
በመጨረሻም
ትላንት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስለ ኑሮ ውድነቱ በአንዲት ወይዘሮ የፓርላማ አባል የተጠየቁ ግዜ “የዋጋ ግሽበቱን
ከሚያባባብሱት ነገሮች መካከል የአለም ነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ከአንድ የተቀናቃኝ ፓርቲ አባል “የነዳጅ ድጎማ ለምን ቀረ?” ተብለው ሲጠየቁ “እኔ እስከማውቀው ድረስ ሰማንያ
አምስት በመቶ የሚሆነው ህዝብ በእግሩ ነው የሚሄደው። ነዳጅ የሚጠቀሙት ሀብታሞች ናቸው ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ
በገበያው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብዬ አላምንም። ስለማላምንም አልደጉምም” በማለት ተናግረው ነበር።
እኔ የምለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የስራ ማስታወቂያ ማውጣት ያለባቸው አይመስላችሁም? ምን አይነት በሉኝማ…
የስራ መደቡ መጠሪያ “አምና የተናገሩትን ዘንድሮ አስታዋሽ።” ልዩ ችሎታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ አቤት ውሸት
ብሎ የማይሳቀቅ!
No comments:
Post a Comment