Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, April 17, 2012

የግድብ ስራው ተቋረጠ አሉ!

 By abetokichaw

ቆይ ቆይ አይደናገጡ! መጀመሪያ የቱ ግድብ? ብለው ይጠይቁ እንጂ፤ “ወይኔ ቦንዴ? ወይኔ ደሞዜ” ብለው ሀዘን አይግባዎ! መንግስታችን አባይን ለመገደብ ከማሰቡም በፊት በትጋት ሲገድብ የነበረው ድረ ገፆችን፣ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎችን እንደነበረ የታወቀ ነው። እንደውም አንዳንድ አሽሟጠጮች እንደሚሉት ከሆነ መንግስት ያለ ምንም ዕቅድ አባይን ልገድብ ብሎ የተነሳው፤  ድረ ገፅ እና ራዲዮ ጣቢያ በመገደብ  ያዳበረውን ልምድ በመተማመን ነው ይሉታል።

ትላንት ዘላለም የተባለ የልብ ወዳጃችን በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ “ስጋትን ስለመግለፅ” ብሎ እንደለጠፈልን ከስቅለተ አርብ ጀምሮ ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ተገድበው የነበሩ ድረ ገፆች በሙሉ ተከፍተዋል። እኔም ይህንኑ ዜና እንዲያረጋግጥልኝ በጠየቅሁት ግዜ በመሃላ አረጋግጦልኛል። አሁን በቅርቡ ይቺን የኔዋን ምስኪን ብሎግ ጨምሮ ሎሎችም ብሎጎች ለሳምንት ያህል ወደ ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ ታግተው ሰንብተው ነበር። የዛኔም መንግስት የግድብ ስራውን እያጧጧፈ እንደሆነ ግንዛቤ ወስደናል። (“ግንዛቤ ወስደናል” አሪፍ የካድሬ ንግግር ናት ብዙ ግዜ በገንዘብ ከሚደረጉ ስብሰባዎች በኋላ የስብሰባው ተሳታፊዎች “ገንዘብ አግኝተናል” አይሉም ግንዛቤ አግኝተናል ነው የሚሉት።)

እውነትም ታድያ ከብሎጎቹ ቀጥሎ አብዝተው ዴሞክራሲን የሚሰብኩ የፌስ ቡክ ታጋዮችም ጭምር የግድቡ ሰለባ ሆነው ነበር። እኛም በያለንበት “ጨምሯል ግድብ ጨምሯል” እያልን ስናንጎራጉር ሰንብተናል። አሁን ግን ይኸው ከስቅለተ አርብ ያነሳ ቢያንስ እስከ ሰኞ አመሻሹ ድረስ ከዚህ በፊት ታግደው የነበሩ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩ ድረ ገፆች እንደ ምንጬ አባባል “ፏ” ብለው ይታዩ ነበር። እንዴት ነው ነገሩ መንግስት ተቀየረ ወይስ ዌብሳይቶችን ሲገድብ የነበረው ሰውዬ ደህና አይደለም? ወይስ መንግስት ተፀፀተ?  እነዚህን ጥያቄዎች እርሱ ባለቤቱ ይመልሳቸው።

ነገሩ ግን በዚሁ ካዘለቀው በጣም ጥሩ ጅምር ነው። እግረ መንግድ ታድያ እነ እስክንድር ነጋ ውብሸት ታዬ እና ርዮት አለሙን የመሳሰሉ ጋዜጠኞች የተገደቡበት የቃሊቲ ግድብም ቢፈርስ፤ እንዲሁም ብቸኛዋን ፍትህ ጋዜጣ እየደረሰባት ያለው “ሰፋጣ” ቢቆምላት መንግስትን “የዴሞክራሲ አርበኛ” ብለን እንሸልመው ነበር!

ከዚህ በፊት ያልኩትን አሁንም እደግመዋለሁ። የመናገር እና የመፃፍ መብት መገደብ የኤሌክትሪክ ሀይል አያመነጭም እናም በጅምሩ “መንግስቴ በርታ በርታ…” ብዬ ላዜምለት እወዳለሁ። ወዳጄ እንግዲህ አሁን ጎግልዎ ላይ ያሻዎን ድረ ገፅ ታይፕ አድርገው ያሻዎን መረጃ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው። ታድያ ዛሬም ሊገደብ ስለሚችል ቀልጠፍ ቀልጠፍ ይበሉና በኢቲቪ የሚመጡ ህመሞችን ያስታግሱ!

No comments:

Post a Comment