አቤ ቶኪቻው
ይህንን ጨዋታ ስፅፍ ፋሲል ደሞዜ የተባለ አቀንቃኝ “አለ ነገር…” እያለ የሚያንጎራጉረውን ሙዚቃ እየሰማሁ
ነው! ልብ አድርጉልኝ ይህ ስጋት ነው እንጂ ቅስቀሳ አይደለም! ምክር ነው እንጂ ቁጣም አይደለም! አክብራቹሁ
ብሎጋችንን የምትዘጉ ሰዎች ምክራችንንም ስሙ…! አስቲ ሰሞኑን የሰማኋቸውን አጫጭር ዜናዎች ልንገራችሁ።
አንድ
በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ “መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን” ያሉ ሙስሊሞች ከመንግስት ታጣቂ ሃይሎች በተከፈተባቸው ተኩስ አምስት ሰዎች ተገደለው በርካቶች ቆስለዋል። መንግስትም “አስር ፖሊሶቼ ተጎድተውብኛል
ብሏል።” ይህ እንግዲህ የመርካቶው አንዋር መስጊድ እንቅስቃሴ አካል ነው። ይህንን መንግስት በሰላም እንዲፈታ
ሁላችንም መክረናል ለምነናል ሰሚ ግን አላገኘንም እናም፤ መርካቶ አለ ነገር አትሉልኝም!
ሁለት
ጋምቤላ ከመሬታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰቡ አካላት በሼኩ እና በፓኪስታኖቹ የሩዝ አምራቾች ላይ እያሰሙ ያሉት
ተቃውሞ ከእለት እለት እየተባባሰ፤ ወደ ተቀናጀ ጥቃት ተለውጦ አሁን በቅርቡ በሩዝ እርሻው ላይ ሲሰሩ የነበሩ የውጪ
ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን ላይ እስከ ሞት የደረሰ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። ይህንንም አቤት እያሉ ሲጮሁ የነበሩ ብዙ
ናቸው ግን ማን ይስማ…? በዚህም የተነሳ ጋምቤላ አለ ነገር! ያስብላል።
ሶስት
የዋልድባ ገዳምን ህልውና በሚፈታተን መልኩ የስኳር ምርት ሊያመርት መንግስት ደፋ ቀና እያለ ነው። የገዳሙ
ሰዎችም “ተዉ ስለ እግዚአብሄር ብላችሁ አትንኩን” ብለው ቢለምኑ ቢማፀኑ የሚሰማ አላገኙም። መንግስት ነብሴ
በቴሌቪዥኑ “ዋልድባ ሳይነኩት ጮኸ” አይነት ይዘት ያለው ዘገባ አሰራ! ቄሱም ዲያቆኑም መከረ ዘከረ “መንግስት ሆይ
እባክህን ነገርህን በልኩ አድርገው!” አሉ።
ነገር ግን አልሰማም። ልክ በአሁኑ ሰዓት የጎንደር ህዝብ ነብስ ወከፍ
መሳሪያውን ይዞ በአስፈሪ ሁኔታ ወደ ዋልድባ ገዳም እየተመመ እንደሆነ ሰማን… ጎንደር አለ ነገር ማለት ይሄኔ
ነው! “ሶስት በአንድ” ይሄ እነ “ማዘር ቤት” የመሳሰሉ ምግብ ቤቶች ገብተን ምግብ የምናዝበት ቋንቋ ነው። ብዙ
ግዜ እንደዚህ የምናዘው ለአራት ሆነን ነበር። አሁን ግን መንግስታችን ብቻውን ሆኖ ሶስት በአንድ አዟል። ደሞ ሌሎች
ተከታዮችም አያጣም…!
ታድያልዎ ምን አስጨነቀኝ መሰልዎ… መንግስት ምን ያህል ቢርበው ነው ሶስት በአንድ ያዘዘው? የሚለው ጥያቄ ያሳስበኛል። በአዲስ መስመር እንደተለመደው መንግስቴን እመክራለሁ… አረ ተዉ ግድ የላችሁም…! አንድ ግዜ ሰዉ ምን እያለ እንደሆነ ቆም ብላችሁ አዳምጡ! እየተጠየቁ ያሉት እጅግ
በጣም ቀላል ቀላል ጥያቄዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ከከበደን የምንከፍለው ዋጋ ይወደድብናል!
እባካችሁ!!! ሶስት ለአንድ አያልቅም ትዕዛዝም ልክ አለው! ተዉ!
No comments:
Post a Comment