Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 29, 2012

የብሔራዊ ባንክና የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኃላፊዎች እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተወሰነባቸው

 By ሪፓርተር
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ወርቅ ነው” በማለት ቁርጥራጭ ብረቶችን ላቀረቡ ግለሰቦች ከፍተኛ ክፍያ መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸውና ለክፍያው መፈጸም ምክንያት ሆነዋል የተባሉ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሥልጣን ከፍተኛ ጂኦሎጂስትና ነጋዴዎች ከሦስት እስከ 12 ዓመታት እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ሚያዝያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ውሳኔ ተላለፈባቸው፡፡

ውሳኔውን የሰጠው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በየካቲት ወር 2000 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የመሠረተውን “በግብረ አበርነት ተፈጽሟል” ያለውን የሙስና ወንጀል ሲመረምር የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15 ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ላይ የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበ በኋላ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሠረት፣ ተከሶሾቹ የሰዎችና የሰነድ መከላከያ ማስረጃዎችን ያቀረቡ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት የወንጀል ድርጊት መሠረት ሚያዝያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም. በግለሰቦቹና በአንድ ኩባንያ ላይ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ሰይፈ ደስታ፣ የከረንሲ ማኔጅመንት መምርያ ኃላፊ አቶ ዋሱ አደም፣ የኢሹ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ተክለሃና ዘለቀ፤ ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ደግሞ ዋና ጂኦሎጂስት አቶ አመንቴ አብርሃ፣ የላብራቶሪ ክፍል ኃላፊ አቶ ያሲን ይማምና የላብራቶሪ ባለሙያ አቶ በላቸው በሬሳ እያንዳንዳቸው ስድስት ዓመታት እስርና ሁለት ሺሕ ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩትና “ወርቅ ነው” በማለት በተለያዩ መንገዶች ቁርጥራጭ ብረቶች (ባሌስትራ) በማቅረብ በባንኩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተወሰነባቸው፣ አቶ ሙደሲር መሐመድና አቶ ባህርዲን ኑርሴቦ እያንዳንዳቸው 12 ዓመታት እስርና ሰባት ሺሕ ብር፣ አቶ ሱልጣን መሐመድ ስድስት ዓመታት እስርና አምስት ሺሕ ብር፣ አቶ ሐሽም አማን ስምንት ዓመታት እስራትና 34 ሺሕ ብር፣ አቶ ካፍ መሐመድ ሰባት ዓመታት እስራትና ሦስት ሺሕ ብር፣ አቶ አብዱ ሽኩር መሐመድ ሦስት ዓመታት ከሰባት ወራት እስራት፣ አቶ መኸዲን ጀማል ሰባት ዓመታት እስራትና 30 ሺሕ ብር፣ እንዲሁም አቶ አምሳሉ አሰፋ ሦስት ዓመታት ከ11 ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ ሶፋም ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 84 ሺሕ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

ሚያዝያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15 ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው በወንጀል መዝገብ ቁጥር 66211 ክስ የተመሠረተባቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ቅብ ለሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ለኪሳራ መዳረጉን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡  

No comments:

Post a Comment