ኢሳት ዜና:-
በሺዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች ወደ ዋልድባ ተመሙ፣ ሁለት ነጮች ተገድለዋል ሌሎች ሰራተኞች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል የገዳሙ
አባቶች ለሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች ባቀረቡት ጥሪ መሰረት እስከ 200 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኙ የሰሜን ጎንደር
ነዋሪዎች ወደ አካባቢው መትመማቸውን ተከትሎ ሁለት ነጮች መሞታቸውን፣ ሌሎች ሰራተኞች ደግሞ እኛ ከህዝብ ጋር
አንጣላም በማለት አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።
የሟቾቹ እና አካባቢውን ለቀው የወጡት ነጮች ምእርባዊያን ይሁኑ
የቻይና ዜጎች አልታወቀም። ከ5ሺ ያላነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች በዋልድባ ተገኝተው ተቃውሞ እያሰሙ ሲሆን፣
የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላትም እርምጃ ለመውሰድ ፈርተዋል። ሁኔታው እጅግ አስፈሪ ነው፣ መንግስትና ህዝቡ
ተፋጠዋል፣ የአካባቢው ወጣቶችም ወደ አካባቢው ለመጓዝ እየተመካከሩ ነው ሲል አንድ ጉዳዩን በቅርብ ሆኖ የሚከታተል
ሰው ለኢሳት ገልጧል።
“ሰራተኞቹ እኛ ለህዝብ ልማት ይውላል ተብሎ ነው የመጣነው፣ እናንተማ ካልፈለጋችሁት እኛ እዚህ ምን እናደርጋለን?” በማለት አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ስራው ሙሉ በሙሉ ቆሟል። መንግስት
ስራው ተቋርጧል በማለት ለአካባቢው ነዋሪዎች ቢናገርም፣ ህዝቡ ግን ሚጢቆ በሚባል ቦታ ላይ የተተከሉት ሁለቱ
የኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮች ካልተነሱ ስራው መቋረጡን ከልብ አምነን ለመቀበል አንችልም የሚል መልስ ሰጥቷል።
የአካባቢው ህዝብ አሁንም ጄኔሬተሮቹ እስኪነሱ ድረስ በትእግስት በአካባቢው ተገኝቶ እየጠበቀ ነው። ህዝቡ በስንቅ እጦት እንዳይቸገር እርስ በርሱ እየተተካካ እንደሚጠብቅ ለማወቅ ተችሎአል። የገዳሙ አባቶች ” ከሀይማኖት ወዲያ ምን አለ፣ ለሀይማኖት መሞት ጽድቅ ነው።” በማለት ሰሞኑን ህዝቡን እየዞሩ ሲያስተምሩ ነበር። መንግስት የተወሰኑ መነኮሳትን አፍኖ መውሰዱም ታውቋል።
አሁን
በሚታየው ስሜት የዋልድባ የስኳር ግንባታ ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል አንድ የአካባቢው ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።
የህዝቡ ቁጣ ከመጠን እያለፈ ነው ያሉት እኝህ ሰው ፣ መንግስት ከህዝቡ ጋር እልህ ውስጥ የሚጋባ ከሆነ ከፍተኛ
ጉዳት ሊደርስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የመንግስት ባለስልጣናት በግንባታው ዙሪያ የሀይማኖት አባቶች ስምምነታቸውን ሰጥተዋል ቢሉም፣ ህዝቡ ግን የሚቀበለው አልሆነም።
No comments:
Post a Comment