ኢሳት ዜና:-
ከጋምቤላ በምስል ተደግፎ ለኢሳት የተላከው ዘገባ እንዳመለከተው ባለፈው ቅዳሜ በአበቦ ወረዳ
በሳውዲ ስታርና በሳውዲ ስታር ሰብ ኮንትራክተር በሆነው CRBC ኩባንያ ሰራተኞች ላይ ቅዳሜ እለት በተፈጸመው ጥቃት
የሞቱት ዛሬ በአንድ የመከላከያ ሰራዊት ሄሊኮፕተር እና በአንድ አውሮፕላን ተጭነው ወደ አዲስ አበባ ተሸኝተዋል።
ድርጊቱ
የተፈጸመው ሰራተኞቹ ከአሌሮ ግድብ የሚወጣውን ውሀ ለሩዝ እርሻው ለማቅረብ የቧንቧ መስመር ዘርግተው እንደጨረሱ
ወደ ሰርቪሳቸው በመመለስ ላይ እያሉ ነው። አንድ የአይን እማኝ ለኢሳት እንደገለጠው ሰራተኞቹ ወደ ሰርቪሳቸው
እየተመለሱ በነበረበት ጊዜ የሳውዲ ስታር ጠባቂ የሆኑት የአካባቢው ተወላጆች በሞባይል ስልክ መልእክቶችን ተለዋውጠው
ተኩስ ከፍተዋል። በተኩሱም አንድ ፓኪስታናዊ ጨምሮ 5 ሰዎች ሲገደሉ፣ 4 ፓኪስታናዊያንና 5 ኢትዮጵያውያን
ቆስለዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት የሳውዲ ስታር ዘበኞች ናቸው ያለው ይህ ግለሰብ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት
ከአካባቢው ራቅ ብለው በመገኘታቸው ጥቃቱን ለማስቆም እንዳልቻሉ ተናግሯል። ይሁን እንጅ በአቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመራው
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በመህጻረ ቃሉ አኢጋን ዛሬ ባወጣው ዘገባ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ናቸው
ብሎአል። መንግስትም ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች መሆናቸውን አምኗል።
ሽፍታ በሚል ስያሜ የሚጠሩት ታጣቂዎች
ንብረትነቱ የሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ የሖነውን የሳውዲ ስታር እርሻ ሁለገብ ካምፕ ያለአንዳች ችግር ዘልቀው
ከገቡ በሁዋላ የኮማንዶ ስልት በተሞላበት ቅልጥፍና እና ፍጥነት በመከፋፈል የእርሻውን ስራ ማከናወኛ ቢሮ፣ የዋና
ዋና ስራተኞች መኖሪያ ካፍቴሪያና የተመረጡ ቦታዎችን በመቆጣጠር ተግባራቸውን አከናውነዋል ሲል ኢጋን ዘግቧል።
ታጣቂዎቹ አራት ከፍተኛ የእርሻ ኤክስፐርት የሆኑ የፓኪስታን ዜጎችን ገድለው ሶስቱን ማቁሰላቸውን እንዲሁም አራት ኢትዮጵያዊ ሰራተኞችና አንድ የአኝዋክ ተወላጅ የጥበቃ ፖሊስ መገደላቸውንና ስድስት የሚሆኑት መቁሰላቸውን ዘገባው ጨምሮ ያስረዳል።
የኢሳት ዘጋቢ በላከው ዘገባ እንደሚለው ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው ከሚጠረጠሩ 10 የአካባቢው ተወላጆች መካከል የተወሰኑት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው። በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት ሰራተኞች ገሚሶቹ ወደ መቱ ሆስፒታል ሲወሰዱ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል።
በዛሬው
እለት የሳውዲ ስታር እና የሚድሮክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ጋምቤላ ያቀኑ ሲሆን ፣ ሰራተኞች ከግቢያቸው
እንዳይወጡ፣ ስራም እንዲያቆሙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። በአካባቢው ያለ ማንኛውም እንቅስቃሴም እንዲቆም ተደርጓል። በጋምቤላ
ቀደም ሲል በተካሄደ ተመሳሳይ ድንገተኛ ጥቃት ሰው መገደሉና ሳውዲ ስታር” ተብሎ የሚጠራው የ አል አሙዲ እርሻ
ድርጅት ገንዘብ ያዥ የነበረ ግለሰብ ክፉኛ ቆስሎ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መወሰዱ ይታወሳል።
እንዲሁም ሌላ በሰፊ መሬት ላይ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት ድንገት በታጣቂዎች ተገድሎ አስከሬኑ ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት ወደ መቀሌ ከተማ እንደተወሰደ ኢሳት መዘገቡ አይዘነጋም። ከዚህም ባሻገር የደህንነት ሀላፊ የነበሩትን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱባቸው ተኩስ ህይወታቸውን ማጣታቸው በተደጋጋሚ ሢዘገብ ቆይቷል።
ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 19 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ከቅርብ
ጊዜ ወዲህ በጋምቤላ እየተባባሰ ለመጣው እና የመንግስት ራስ ምታት እስከ መሆን ለደረሰው ለዚህ ተደጋጋሚ ጥቃት
ዋነኛ ምክንያቱ ፤ መንግስት የ አካባቢውን ተወላጆች ከይዞታቸውና ከቀያቸው እያፈናቀለ መሬታቸውን በውዳቂ ዋጋ
ለውጪ ባለሀብቶችና ለራሱ ካድሬዎች መስጠቱ ያስከተለው ቁጣ እንደሆነ ይነገራል።
መንግስት ታጣቂዎቹን ለማደንና ለባለሀብቶቹ ዋስትና ለመስጠት የከተማዋን ዙሪያ በሜካናይዝድ ጦር ማስጠበቅ ከጀመረ ቢሰነብትም፤ እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት ሊቆጣጠረው አልቻለም። በተለይ
መንግሰት ፦’የተሟላ ጥበቃ እያደረግኩ ነው”በሚልበት በአሁኑ ጊዜ የተፈመው ጥቃት፤ በአካባቢው በእርሻ ሥራ ላይ
የተሰማሩትን ቀሪ ባለሀብቶች ስለ ቀጣዩ ቆይታቸው ደጋግመው እንዲያስቡ ፤ በአካባቢው እንደ አዲስ ለመሰማራት
አስበው የነበሩ ሌሎች ባለሀብቶችንም እግራቸውን እንዲሰበስቡ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
__________________________________________________________________________________________________________
No comments:
Post a Comment