Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, April 21, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩነቱን አቻችሎ በወያኔ ጠባብ አገዛዝ ላይ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቀረበ


ኢሳት ዜና:-
እራሱን ህጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሲኖዶስ፤ በሚል የሚጠራው ቅዱስ ሲኖዶስ “ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩነቱን አቻችሎና አስወግዶ  አገር እያጠፋ ባለው የወያነ ጠባብ አገዛዝ ላይ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቀረበ።

መቀመጫውን በአሜሪካ ኦክላንድ ያደረገው ሲኖዶሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ የጥንቱ የግብጽ አገዛዝ በእስራኤል ልጆች ላይ ሲያደርግባቸው የነበረውን አሰቃቂ ግፍ በማስታወስ፤ያኔ በባርነት ታግተው የነበሩት እስራኤላውያን ህይወታቸው  በምን ደረጃ ላይ እንደነበር ሊያመለክተን የሚችል ነገር ካለ፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የመከራ ህይወት ብቻ ነው ብሏል።

“ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟትና አይታው የማታውቀው ህልውናዋን የማጥፋት እንቅስቃሴ በዘረኛ መርሆ በሚገዛት ወያነ፤ እጅግ በሚገርም ፍጥነት እየተካሄደባት ይገኛል” ያለው የሲኖዶሱ መግለጫ፤አጥፊና ጨካኝ መንግስት ቢሆን እንኳ ፤እንዲህ እንደ ወያነ-  እየረገጠ የሚያስተዳድረውን ህዝብ ይህን ያህል የመሬት ኪራይ የሚያስከፍል አገዛዝ በዓለም ላይ ተፈልጎ አይገኝም”ብሏል።

“በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵየን የሚገዛው ቡድን የአምልኮ ቦታዎችን- እግዚአብሔር የሚመለክባቸው ሳይሆን፤ካድሬዎች የሚመለመሉባቸው አድርጓል፤ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸውን ገዳማትና ቤተ-መቅደሶች በሙሉ ደፍሯል፤አዋርዷል። ለዓለም ሰላም ለመለመን በጸሎት የሚተጉ የባህታውያንን መጠጊያ ዋሻዎች በቡልዶዘር እየደመሰሰ፤መጠለያ ዛፎቹን በእሳት እያቃጠለ፣የቅዱሳን አባቶችን አጽም ከመቃብር እያወጣ፣በረሀብና በግፍ አገዛዝ የተንገፈገፈው ህዝብ በአምላኩ ፊት እንኳ ተስፋ እንዳይኖረው ተስፋ የሆኑትን ገዳማቱን በለመደው”ልማት”በሚል የቅጥፈት ቅስቀሳው-እያወደመ፦ ተመልሰው ወደማያንሰራሩበት የጥፋት አዘቅት ውስጥ እየከተታቸው ይገኛል” ብሏል- ሲኖዶሱ።

እንደ ሲኖዶሱ መግለጫ  አገዛዙ ገዳማቱን ወደማፈራረስ እርምጃ የተሸጋገረው፤ የገዳማቱ እንዳለ መቀጠል  እየተከተለ ላለው ዘር ላይ የተመሰረተ ጸያፍ ፖለቲካ እንቅፋት ስለሆኑበት ነው።
“ምክንያቱም…” ይላል መግለጫው ሲቀጥል “….ምክንያቱም ገዳማቱ የዘር ክፍፍልን አያውቁም። የቋንቋ ልዩነትን እንደ ዘር ወስደው ሰውን ከሰው አይለዩም።ሰውን ከሰው አያበላልጡም”ይላል።
“ገዳማቱ የአገሪቱ አንድነትና የመንፈሳዊ ብልጽግና ማዕከል ብቻ ሳይሆኑ፤ የትምህርት ማዕከልም ጭምር ነበሩ” ያለው ህጋዊው ሲኖዶስ፤ የገዳማቱ መኖር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥንካሬና ህልውና ለኢትዮጵያም አንድነትና መሰረት እንደሆነ፤ የወያነ ዘረኛ ቡድን ጠንቅቆ ያውቀዋል”ብላል።

በምርጫ 97 ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ፦”የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን ፦”የነፍጠኞች ዋሻ” ብለው መዝለፋቸው አይዘነጋም። “የገዳማቱ ህልውና መጠበቅ ገዥው ቡድን ሊያጠፋት ቆርጦ በተነሳባት ኢትዮጵያ ላይ እየፈፀመ ላለው የማጥፋት ተግባር ትልቅ መሰናክል እንደሚሆንበት ይረዳል’ያለው ሲኖዶሱ፤ “ለዚህም ነው አንዴ በልማት ስም፤ ሌላ ጊዜ በእሳት ስም ገዳማቱን እያጠፋ ያለው”ብሏል። ሲኖዶሱ መግለጫውን ለማውጣት የተገደደውም፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዋልድባ ገዳምን ለማጥፋት እየተፈጸመ ያለውን ሴራ ለማሳወቅ እንደሆነ ጠቁሟል።

“በመናኙ በአባ ሳሙኤል ዘዋልድ በ 13ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የተቆረቆረው የዋልድባ ገዳም  ፤በአሁኑ ጊዜ ስልጣን ላይ፤ ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ ይሁኝታ በተፈናጠጠው ቡድን  ከመደፈሩ በስተቀር፤በቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎችና ነገስታት ይቅርና  በጠላትም ያልተደፈረ ታላቅ የአገሪቱ መንፈሳዊ እሴት ሆኖ የኖረ ገዳም ነው” ሲል ሲኖዶሱ አትቷል። ሲኖዶሱ አያይዞም፤የአሁኑ መንግስት  በገዳማት ላይ እየፈጸመ  ካለው ጥፋት በመነሳት ፤”የኢትዮጵያ፦ የመጥፊያዋ -መደምደሚያ ጅማሬ ፤እየተደገሰ ነው” ብሎ እንደሚያምን ስጋቱን ገልጿል።

በስደት ላይ የሚገኘው  ይህ ሲኖዶስ የህወሀትን አጥፊነት ቀደም ብሎ ስላወቀው ጥፋቱን እያጋለጠ ስህተቱን በማያሻማ መንገድ ሲያወጣ ሀያ ዓመታት ማስቆጠሩንም አውስቷል። ሲኖዶሱ በመቀጠልም፦”ቤተ-ክርስቲያንን ከፖለቲካ ጋር ምን ያገናኘዋል?ብለው ለሚጠይቁ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጩኸት ግልጽ የሆነ ይመስለናል።የወያነ ጠባብ የገዥ  ቡድን አጥፊነት የመጨረሻው ጣራ ላይ ደርሷል።በአሁኑ ጊዜ አጥፊነቱን አልተረዳሁም የሚል ያለ አይመስለንም።

የወያነ ጠባብ ቡድን እስካለ ድረስ፤ኢትዮጵያ የምትባል አገር በስምም፣በአካልም በመልክዓ-ምድር ላይ ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ካለ፤ አንድም እሱ የዋህ ነው፤አለያም የጠባቡን ገዥ ቡድን ዓላማ የሚጋራ ነው።”ብሏል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል የሚፈልጉ ሁሉ፤ የቤተክርስቲያንን ጥሪ በመቀበል አገራቸውን እንዲታደጉ  በማሣሰብ  የትብብር ትግል ጥያቄውን በስድስት ነጥቦች በመዘርዘር አቅርቧል-ሲኖዶሱ።

በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ፀሀፊ በብጹዕ አቡነ መልከ-ጼዴቅ ፊርማ ይፋ የሆነው  ይህ መግለጫ፦“በፖለቲካ፣በሀይማኖትና በልዩ ልዩ ችግር የሀሳብ ልዩነት እያደረጋችሁ የምትጣሉ ሁሉ፤ጠባችሁ ስለ አገር ከሆነ፤ አገር የለችም።ስለ ሥልጣን ከሆነም፤ የሚመርጥ ህዝብ -የሚተዳደር አገር ስለሌለ፤ህዝብ ከማለቁ፤ሀገርም ጨርሶ ከመጥፋቱ በፊት በአንድ ልብና በአንድ ሀሳብ መክራችሁ በዚህ የአገር አጥፊ ቡድን ላይ በመነሳት ኢትዮጵያን እንድታድኑ በቤተ-ክርስቲያን ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብሏል።

No comments:

Post a Comment