Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, April 21, 2012

ሰሜን ሱዳን ደቡብ ሱዳንን የምትወጋ ከሆነ ዩጋንዳ ጣልቃ እንደምትገባ አስጠነቀቀች

ኢሳት ዜና:-
የዩጋንዳ ጦር አዛዥ የሆኑት አሮንዳ ኒያክሪማ እንዳሉት ሰሜን ሱዳን ደቡብ ሱዳንን ለመውረር ከከጀለች አገራቸው ዝም ብላ አትመለከትም። የጦር አዛዡ የአልበሽር መንግስት የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ  ሰራዊትን ይደግፋል የሚል ክስም አቅረበዋል። የኡጋንዳን መንግስት እየተፋለመ የሚገኘው የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ ፣ ቀደም ብሎ ከመሸገበት የማእከላዊ አፍሪካ ወጥቶ በሰሜን ሱዳን ድንበር አካባቢ ሰፍሮ እንደሚገኝ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

የመለስ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያደርገውን በረራ እንዲሰርዝ በማድረግ ለሰሜን ሱዳን መንግስት ግልጽ ወገናዊነት እንዳሳየ እየተነገረ ነው። የአልበሽር መንግስት ልዩ ልኡክ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር መገናኘታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። ሁለቱ አገሮች ወደ ሙሉ ጦርነት የሚገቡ ከሆነና ዩጋንዳ ደቡብ ሱዳንን በመደገፍ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ በአካባቢው ያለውን ፖለቲካ ያወሳስበዋል ተብሎ ተሰግቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያድርገውን በረራ ከዛሬ ጀምሮ ማቋረጡን ለማረጋገጥ ተችሎአል። የመለስ መንግስት በወሰደው ውሳኔ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ የሚገኙትን የሀወሀት አባላትና ደጋፊዎች ሳይቀር ያሳዘነ ጉዳይ ሆኗል። በደቡብ ሱዳን ስራ ለመስራት የገቡ በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በውሳኔው ተበሳጭተዋል። የአቶ መለስ መንግስት የደቡብ ሱዳን መንግስት በጋምቤላ በሚታየው ግጭት እጁ አለበት ብሎ ያምናል። በቅርቡ በጋምቤላ በተካሄደው የሁለቱ አገሮች ውይይት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን መንግስት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ ዜና ደግሞ በቅርቡ በጋምቤላ 19 ሰዎች መገዳለቸውን ተከትሎ ሁለት የአኝዋክ ተወላጅ ተጠርጣሪዎች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለዋል። አንደኛው ተጠርጣሪ የተያዘው ክልሉን በበላይነት በሚያስተዳድሩት የመከላከያ ሰራዊት በሽጉጥ ከተመታ በሁዋላ ነው። የጋምቤላው ወኪላችን እንዳለው በክልሉ አሁንም ውጥረት እንዳለ ነው፤ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ስራ የመጀመር አዝማሚያ ቢታይባቸውም በተሟላ መልኩ ስራ አልጀመሩም።

 የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚጠረጥሩዋቸውን ነዋሪዎች ሁሉ እየያዙ በማሰር ላይ መሆናቸው በክልሉ ያለው ውጥረት እንዳይበድር ማድረጉን ዘጋቢያችን የላከው ሪፖርት ያመለክታል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦሩን ከአወዛጋቢው ሄግሊግ ከተማ ማውጣቱን አስታውቋል። የደቡብ ሱዳን መንግስት  በላከው ፕሬስ ሪሊዝ ለማወቅ እንደተቻለው የአገሪቱ ጦር ከዛሬ ጀምሮ አካባቢውን ለቆ ይወጣል። ደቡብ ሱዳን መንግስት ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሚመሩት የሽምግልና ጥረት ላይም ጥያቄ እንዳለውና እንደገና መመርመር እንዳለበት ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment