Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Monday, April 16, 2012

ማቆሚያና ገደብ ያጣው የምስኪኗ እናቴ ዕንባ!

 
  By Kinfe Michael Abebe (Abebe Kesto), Kaliti Prison

የዘንድሮው የዓድዋ በዓል 116ኛ ዓመት ሲከበር በምኒልክ አደባባይ ለመገኘት እድሉን አላገኘሁም። ሆኖም ግን በቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ሆኜ ዕለቱን ለማስታወስ ሲባል የተዘጋጀውን የኢቴቪን ልዩ ዝግጅት ለመከታተል እድሉን አግኝቻለሁ። እጅግ የተገረምኩት ደግሞ በዓድዋ ዘመቻ ላይ ታሪካዊ ጀግንነትና ገድል ከፈፀሙት መካከል አንዱ የሆኑት የእኔ የቅድመ አያቴ አኩሪ ታሪክና ተግባር ብኮራና ብደሰትም እርሳቸው ለሀገራቸው አንድነት፣ ለነፃነትና ለእኩልነት፣ ያደረጉት ተጋድሎ ዋጋ አጥቶ እኔ ልጃቸው ነፃነት አልባ ሆኜና ለነፃነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት መቆርቆሬ ከወንጀል ተቆጥሮብኝ፣ የእኔ እያልኩት የእኔ ባልሆነው መንግስት ወህኒ መወርወሬ በእጅጉ አሳዝኖኛል።  አሳፍሮኛል።                             

ምን ይኼ ብቻ እንደ ቅድመ አያቴ ሁሉ ከአያቶቼ አንዱ ደግሞ በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን እምቢ ሀገሬንና ነፃነቴን ሲሉ፤ ከሌሎች መሰል አርበኞች ጋር በመሆን ለፋሽስት ኢጣሊያ መንግስት አልገዛ ፣ አልሰግድና አልንበረከክ ማለታቸው ብቻ ከወንጀል ተቆጥሮ አዚናራ ተብሎ በሚጠራው የፋሽስቱ ወህኒ ቤት ተወርውረው ፍዳቸውን ለመቁጠር በቅተዋል።አያት-ቅድመ አያቶቼ ይህን ሁሉ ያደረጉት ከራሳቸው አልፈው ለእኔ ዛሬ በግፍ ለታሰርኩት የልጅ ልጃቸው ነፃነትና እኩልነት ከልብ በማሰብ የተነሳ መሆኑን ማንም ሰው ሊክደው የማይችለው የዘመን ሀቅ ነው። 

እድለቢሱ እኔ ግን ፋሽስት ኢጣሊያ ከተባረረ ከብዙ ዓመታትም በኋላ የአያት ቅድመ አያቶች ልፋትና ትግል ፍሬ አጥቶና መክኖ የአምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የግፍ ሰለባ ሆኜ ወደ ዘብጥያ ተወርውሬ /ተጥዬ/ እገኛለሁ። ልክ እንደ እኔ ሁሉ እድለቢሷ እናቴም ብትሆን አባቷ፣ አያቷና ቅድመ አያቷ ለታገለሉት ነፃነትና እኩልነት ተቋዳሽ ለመሆን አልታደለችም፡ ፡ በተለይም የእኔ እናት በተከታታይ በአገራችን የነገሱትን አምባገነኖች የግፍና የጭካኔ ተግባር እንደ ሆሊውድ ፊልም ስትኮመኩም ለመኖርዋ ታሪክዋ ህያው ምስክር ነው።

ይህች የእኔ እናት በ1953 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን መንግስት በመቃወም ተካሂዶ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጦስ የተነሳ በዘመኑ በነበሩ ዳኞች በተሰጠ የግፍ ውሳኔ የቅርብ ዘመዶቿ የስቅላት ፍርድ በአደባባይ ሲፈፀምባቸውና የተረፉትም ሀገር ጥለው ሲሰደዱ በቅርበት አይታለች። ሰምታለች። ከዚያም በ1966 ዓ.ም. በሀገራችን በፈነዳው ግብታዊ አብዮት ወደ መንበረ ስልጣኑ ብቅ ያለውና ንጉሱን ከስልጣን ያስወገደው ወታደራዊው የደርግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ለውጥን እንደሚያመጣና በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ስልጣኑን አስረክባለሁ በማለት የገባውን ቃል ኪዳን ሲያፈርስና ቃሉን ሲበላ ተመልክታለች።

መቼ ይኼ ብቻ ይህች እናቴ በዘመነ ደርግ በ1969 ዓ.ም. አካባቢ እንኖርባት በነበረችው የገጠር ከተማ በዘመኑ የተቀናቃኝ ፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ ከሚሰራበት መ/ቤት በግፍ ተባርሮ በወቅቱ በቤት ውስጥ ያለ ስራ የተቀመጠውን እንጀራ አባታችንን ለመያዝ በመጣ ግብረ ኃይል ቤታችን በፍተሻ ሲተራመስና ሲታመስ የእንጀራ አባታችንም በወቅቱ ለነበረው ለወረዳው ፖሊስ አዛዥ እጁን ሰጥቶ በቁጥጥር ስር በመዋሉና በመታሰሩ ለተወሰኑ ጊዜያት ቀለብ የማመላለሱን ስራ ተያያዘችው። 

በእሱ ይብቃ ያላላት እናቴ በወቅቱ በአገራችን በሰፈነውና በነገሰው ገላጋይ ያጣ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ገደብ ያጣ ንትርክና ትርምስ የተነሳ የእህቶቿ ልጆችና የቅርብ ዘመዶቿ በመታሰራቸው ከጣቢያ ጣቢያ፣ ከወህኒ ቤት-ወህኒ ቤት፣ እየተንከራተተች መጠየቅና ቀለብ ማመላለስ መደበኛ ስራዋ ሆኖ ከዚሁ ጋር ልጆቻቸውን በግፍ ተነጥቀው የልጆቻቸውን ሬሳ በመግዛትና በመቅበር መሪር የሀዘን እንባ ያፈሰሱ እናቶች ጋ ለቅሶ መድረስና ማስተዛዘንንም አቋርጣ አታውቅም ነበር።

እንደ ዕድል ሆኖ ግፈኛው የደርግ ስርዓት ወድቆ የኢህአዴግ መንግስት ሲተካና እሱም እንደ ቀደምቶቹ እንደውም ከእሱ ብሶ በተሻለና በአማረ ቋንቋ የዴሞክራሲና የፍትህ ብቸኛው ጠበቃ እኔ ነኝ እያለ ምሎ ሲገዘትና በአደባባይ ሲለፍፍና ሲያውጅ ስትሰማ እውነት መስሏቸው ከተደሰቱት እናቶች መካከል አንዷ ነበረች ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። እንደውም ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ግንቦት 19 ቀን 1986 ዓ.ም. ለቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያነት ለሚቆመው ሐውልት የመሰረት ድንጋይ ሲያኖሩ ‹‹ከእንግዲህ ወዲያ እንደ ደርግ ዘመን የልጆቻችሁን ሬሳ በገንዘብ የምትገዙበት ስርዓት ተመልሶ አይመጣም።

 የልጆቻችሁም ሬሳ እንደ ውሻ ሬሳ ጐዳና ላይ አይጣልም›› ሲሉ ቃል መግባታቸው እውነት መስሏት ከልብ መደሰቷን አስታውሳለሁ፡፡ ሲፈጥራት ለደስታ አላደላትም መሰለኝ ይህ ደስታዋ ረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ዴሞክራት ነኝ ባዩ የኢህአዴግ መንግስት የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ያነገቡ ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ዕድሜና ፆታ ሳይለይ በአግአዚና በፌደራል ጥይት ግንባር ግንባራቸውን እያለ ጐዳና ላይ ሲደፋቸውና ጐዳናው በንፁሐን ኢትዮጵያውያን ደም ሲረጥብና ሲቀላ በማየቷና በመስማቷ፣ አቶ መለስም ቃላቸውን በማጠፍና በመካድ የሟች ህፃናትን አስከሬን ከየሆስፒታሉ ገንዘብ እያስከፈሉ በመሸጥ ወላጆቻቸውን ሲያስነቡና ሲያስለቅሱ በመታዘቧ ፍፁም ከአዘኑትና የምር በማንባት ፈጣሪያቸውን ከአማረሩት ኢትዮጵያውያን እናቶች መካከል አንዷ ናት።
አቶ መለስም የንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ደም በከንቱና በግፍ በማፍሰስ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ወቅት ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለፍትህ ሲታገሉ የወደቁትን ሰማዕታት ለማሰብ በመቀሌ፣ በባህር ዳርና በናዝሬት የቆሙትን የሰማዕታት ሐውልቶች በቁማቸው አፈረሷቸው። የሰማዕታትንም ደም ደመከልብ አደረጉት። እኛም የሰማዕታቱ ሐውልት በቁሙ ሲፈርስ በትዝብት አይተናል። የአቶ መለስ አስተዳደርና በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን የምርጫ ውጤት መጭበርበርን ተከትሎ በተነሳው የህዝብ ድምፅ ይከበር፣ የሚል ጥያቄና ህዝባዊ ቁጣ ሳቢያ ከነጓደኞቻቸው በወሰዱት እርምጃ የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑት እጅጉ ብዙ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ።

በ1998 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በፌደራል ፖሊስ አባላት ዘግናኝ የሆነ የግድያ ሙከራ ተካሂዶብኝ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ሆኖ ተርፌአለሁ። የፌደራል ፖሊስ አባላት በምሽት በዱላና በሰደፍ ደብድበውኝ የለበስኩት ልብስ በደም ጨቅይቶና በራሴ ደም ርሼ ሳለሁ ጭነው ሲወስዱኝ ከነበረው የፌዴራል ፖሊስ ፒክአፕ መኪና ላይ ኮልፌ መብራት ኃይል ድልድይ ስር የሞትኩ መስሏቸው ወርውረውኝ ሲሄዱ ያዩ ኢትዮጵያውያኖች በአቅራቢያው በሚገኝ ዘመዴ ክሊኒክ አሳክመው በኋላም ለዚያችው እናቴ ደውለው  ተደብድቦ ተጥሎ አግኝተነው ነው ኑና ውሰዱት ብለው ነግረዋት በተዓምር ከሞት የተረፍኩትንና በሞትና በህይወት መካከል ያለሁትን ልጇን አንስታ ወደ ቤት ለመውሰድ በቅታለች።

ይህም ብቻ አይደለም አሁን ደግሞ በ11/01/2004 ዓ.ም. ሊይዙኝ ሲፈልጉ እዚያው ባለፈው ደብድበው ሞቷል ብለው የጣሉኝ ስፍራ ላይ ከዓመታት በኋላም እንደገና የኢህአዴግ ደህንነቶች በሚነዱት ፓጃሮ መኪና ገጭተው በመግደል በመኪና አደጋ የደረሰ ድንገተኛ አደጋ ለማስመሰል ሞክረው በእኔ ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ብርታት ልተርፍ ችያለሁ። 

ይህች የእኔ እናት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን 20 ዓመታት ከሞላው በኋላም እንኳን እኔን ልጇን የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ አንግበሃል፣ ስለኢትዮጵያና ስለአንድነቷ አስበሃል፣ ለህዝብ ጥቅም ተቆርቁረሃል፣ በሚል በሽብርተኝነት ፈርጆ በደም የፀደቀ ነው የሚለው የራሱ ህገ መንግስት ከሚፈቅደውና ከሚያዘው ውጭ ዘብጥያ ስለወረወረባት ቀድሞ በደርግ ዘመን ታደርገው እንደነበረው ሁሉ አሁንም በእርጅና ዘመኗ የሚያዝንላትና የሚያሳርፋት አጥታ አንዴ ማዕከላዊ አንዴ ቃሊቲ እየተንከራተተች ቀለብ ማመላለሷን ቀጥላለች። ቴዲ አፍሮ ‹‹አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ›› ሲል በምፀት ያዜመው ይህን የሀገር ሃቅ አይደለምን? ይህች ያልታደለችው የእኔ እናት የሚሊዮን ሀዘንተኛ ኢትዮጵያውያን እናቶች ምርጥ ማሳያና ምርጥ ምሳሌ ናት።

ምስኪኗ እናቴ ሚሊዮኖችን በግፍ ውሳኔያቸውና ፍርዳቸው አስነብተውና አስለቅሰው እንዳለፉት የንጉሱና የደርግ ዘመን ዳኞች ሁሉ የዛሬው የእነርሱ ተተኪ የሆኑት የአምባገነኑ የኢህአዴግ ፍ/ቤት ዳኞች በእኔ በልጇ ላይ የሚበይኑትን እና የሚያነቡትን ግፍና ጭካኔ የተሞላበትን የፍርድ ውሳኔያቸውን ለመስማት ወደዚሁ ፍ/ቤት ደከመኝና ሰለቸኝ ሳትል በመመላለስ ላይ ናት። እነሱም ይህን የግፍ ፍርዳቸውን አናሰማም እንደማይሏትና የጭካኔ ፍርዳቸውን በማንበብ እንደሚተባበሯት
ተስፋ አደርጋለሁ። እንደሷ ሁሉ እኔም ለመስማት ጓጉቻለሁ።

ከዚህ በላይ የጠቀስኩት ሃቅ የሚያስረዳው በሀገራችን ለዘመናት በዙፋኑ ላይ የሰውና የልብስ ለውጥ እንጂ የአስተሳሰብ፣ የአመራርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለውጥ እንዳልመጣ ነው። እናም እባካችሁ መቼ ይሆን በምንፈልገውና በምናምነው የእኛ በሆነ ስርዓትና የአስተሳሰብ ጥበብ የምንመራው? የምታውቁ ንገሩኝ። ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት አያት ቅድመ አያቶቻችን ዛሬ በራሳችን ሰዎች ጭቆና ወድቀን ለምንማቅቀው እድለ ቢስ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ነፃነትና ለሀገር አንድነት ያደረጉት ትግልስ ፍሬ አፍርቶ የሀገራችንና የነፃነታችን ባለቤቶች የምንሆነው መቼ ነው?... መቼ ነው? … መቼ ነው?

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Source: Fetehe.com

No comments:

Post a Comment