Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, April 21, 2012

ትናንት ከጁምአ ጸሎት በሁዋላ ሙስሊሞች አደባባይ በመውጣት ከፍ ያለ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተዘገበ

ኢሳት ዜና:-
ትናንት ከጁምአ ጸሎት በሁዋላ በትልቁ አንዋር መስጂድ እና በ አወሊያ ከተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በተጨማሪ፣ በደሴ ከ80 ሺህ እና በሀረር ከ 50 ሺህ በላይ ሙስሊሞች አደባባይ በመውጣት ከፍ ያለ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተዘገበ።

ከመቼውም በተለየ መልኩ  የሙስሊሞቹ ተቃውሞ በ አገር አቀፍ ደረጃ  እያየለ የመጣው፤አቶ መለስ ሰሞኑን ፓርላማ ቀርበው  ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ለተሰነዘረው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ በ እውቀት ያልታገዘ ከመሆኑም በላይ፤ ሆነ ተብሎ ሙስሊሙን ማህበረሰብ እርስ በርሱና ከክርስቲያን ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የተጠነሰሰ ሤራ በመሆኑ ይበልጥ ስላስቆጣን ነው ብለዋል-አንድ የአዲስ አበባው ሰልፍ አስተባባሪ ለ ኢሳት ዘጋቢ በሰጡት አስተያዬት።

በሁሉም ከተሞች በተካሄዱት ሰልፎች ላይ ጎልተው ሲንጸባረቁ የነበሩት መፈክሮችም፦ ”አንከፋፈልም!  ድምፃችን ይሰማ! መብታችንን ሳናስከብር ወደ ሁዋላ አንመለስም!” የሚሉ ነበሩ።
የአዲስ አበባው ሰልፍ አስተባባሪዎች  ለሰልፈኛው የበተኑት ወረቀት እንደሚያመለክተው፤ በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት በመላው አገሪቱ በሚገኙ መስጊዶች  በሙሉ ተከታታይና የማያቋርጡ ሰልፎች ይደረጋሉ።

የትናንቱ የአዲስ አበባ ሰልፍ ከተጠናቀቀ በሁዋላ  በሚቀጥሉት ሳምንታት ስለሚደረጉት ሰልፎች ዝርዝር መርሀ-ግብር የያዘውን ወረቀት ለህዝበ-ሙስሊሙ ሲበትን የነበረ አንድ አስተባባሪ በስፍራው ተገኝተው ሰልፉን በዓይነ ቁራኛ  ሲከታተሉ በነበሩ የፌዴራል ፖሊሶች  ይያዛል።

ይሁንና የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ  ወረቀት ሲበትን የነበረውን ወጣት በመኪና በመጫን ወደ እስር ቤት ሊወስዱት ሲሞክሩ ሰልፈኛው ህዝብ  በአንድ ላይ ተባብሮ  ፖሊሶቹን በመክበብ በቁጣ፦ “ልቀቁት!ልቀቁት!” እያለ በመጮኹ፤ በሁኔታው ፍርሀት ያደረባቸው ፖሊሶች ወዲያውኑ ወጣቱን ለቀውታል። በምርጫ 97 ወቅት አቶ መለስ ፦”ለአንድ ወር ታግዷል” ያሉትና  ለዓመታት ጸንቶ የቆየው የሰልፍ ክልከላ አዋጅ፤በተያዘው ዓመት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች  ተሽሯል።

አቶ መለስ በቅርቡ በሙስሊሞች ጥያቄ  ዙሪያ በፓርላማ ምላሽ ሢሰጡ ‘አክራሪ’ ያሏቸውን ሀይሎች  በነቀፉበት ክፍል ላይ፦”እነዚህ ሀይሎች በግብጽ፣ በቱኒዚያ እና በየመን ያደረጉትን አይተናል” በማለት  በተጠቀሱት አገሮች የተካሄዱትን የአብዮት ለውጦች ከአክራሪዎች እንቅስቃሴ ጋር በማገናኘት በመጥፎነት መፈረጃቸው ብዙዎችን ያስገረመ ሆኗል።

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የመድረክ ከፍተኛ አመራር፦” የአቶ መለስ መንግስት የሙስሊሞችን ጥያቄ መመለስ ያልፈለገው ለምን እንደሆነ አሁን ግልጽ ነው። በቱኒዚያና በግብጽ የተካሄዱትንና ሀያላኑን ጨምሮ መላው ዓለም ያደነቃቸውን ህዝባዊ አብዮቶች አቶ መለስ የአክራሪዎች ውጤት ሊያደርጓቸው ሲሞክሩ ማየት አስቂኝ ከመሆኑም በላይ፤ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰልፍ ምን ያህል ጭንቀት ውስጥ እንደገቡ ሚያሳይ ነው”ብለዋል።

“ይህን  ተሞክሮና ምክር ያገኙት ከየመኑ አብደላ ሳላህ እንዳይሆን ብዬ እጠረጥራለሁ?” በማለት  እኚሁ  የመድረክ አመራር ተሳልቀዋል። ትናንት በአወልያ የተደረገውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የአልጀዚራ አረብኛ ክፍል ማቅረቡ ታውቋል።

No comments:

Post a Comment