Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 15, 2012

መኢአድ ከጉራፈርዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ደን ያቃጠሉ ሳይሆኑ በልማት የተሸለሙ ናቸው አለ



 By reporter:  ‹‹ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ የተሳሳተ ነው›› አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
 

 በደቡብ ክልል በቤንቺ ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች መፈናቀልን ተከትሎ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ‹‹ምንም የተባረረ ሰው የለም፤ ደን ሲያቃጥሉና ሲጨፈጭፉ የነበሩ 33 ሕገወጦች ከክልሉ እንዲወጡ ተደርጓል፤›› መባሉ እንዳሳዘነውና አሳፋሪ መሆኑን መኢአድ ገለጸ፡፡ ደን ያቃጠሉና የጨፈጨፉ ሳይሆኑ በልማት የተሸለሙ፣ ግብር እየከፈሉ ያሉና ሀብት ንብረት ያፈሩ መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡

ከክልሉ አሁንም ሰዎች እንደሚሰደዱ፣ እንደሚፈናቀሉ፣ ከመኖሪያ ቀያቸውና ከእርሻቸው እንዲነሱ እየተገደዱ መሆናቸውን የገለጸው መኢአድ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው እንደሚደበደቡ፣ እንደሚታሰሩ፣ እንደሚገረፉና በሐሰት እንደሚከሰሱ በመጥቀስ፣ በቅርቡ እየሩሳሌም በሚባለው አካባቢ በወረዳው ፖሊስ በደረሰበት ከባድ የድብደባ ጉዳት ራሱን ስቶ ከመኪና ላይ ወድቆ ሕይወቱ ያለፈውን ግለሰብ በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በጉራፈርዳ ወረዳ ‹‹የተፈናቀለ ሰው የለም፣ ሰዎችን ለመመለስም የተያዘ ዕቅድ የለም፤›› በማለት የሰጡትን መግለጫ ያጣጣለውና ከእውነት የራቀ መሆኑን የሚናገረው መኢአድ፣ ‹‹ፀሐይ የሞቀውን እውነት ለመሸፈን የሚደረገው መሯሯጥ፣ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም የዜጎችን ክብር የነካና ያዋረደ ነው፤” ብሏል፡፡

‹‹የክልሉ ባለሥልጣናት ድርጊት መንግሥት በሕዝብ ላይ ለደረሰው ሰቆቃ ጆሮና ዓይን ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ በተራ ፕሮፖጋንዳ ላይ በመጠመድ እውነትን ደብቆ በበደል ላይ በደል በመፈጸም፣ እኩይ ተግባር ላይ መሰማራቱን ይጠቁማል፤›› ያለው መኢአድ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የበላይ መመርያ ሰጭ በመሆናቸው፣ ከማንም በላይ ጉዳዩ በቀጥታ እንደሚመለከታቸው ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ፣ በደብረ ብርሃንና በሌሎችም አካባቢዎች የተሰደደው የሕዝብ ቁጥር ከሁለት ሺሕ በላይ በሆነበትና አሁንም ድረስ ከክልሉ እየታሰሩና እየተደበደቡ እንዲወጡ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ፣ ምንም እንዳልተፈጸመ ለመሸፋፈን መሞከር ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አለመሆኑን መኢአድ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

ከአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በሥራ ምክንያት ወደ ደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን እየሄዱ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ፣ በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት መሬት የተረከቡና ሀብት ንብረት ያፈሩ፣ ቤተሰብ የመሠረቱ ግብር ከፋይ መሆናቸውን ያብራራው መኢአድ፣ የክልሉ ባለሥልጣናት ቁጥራቸውን ወደ 33 በማውረድ ‹‹ደን ሲያወድሙና ሲያቃጥሉ የነበሩ ሕገወጦች ነቸው›› ማለታቸው አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል፡፡

ዜጎቹ ሕጋዊ ሆነው ይኖሩ እንደነበር የሚያረጋግጥ ሰነድና ግብር የከፈሉበት ማስረጃ በእጃቸው እንደሚገኝ፣ በ1996 ዓ.ም ወረዳቸውን (ጉራፈርዳን) በልማት ከዞኑ በአንደኝነት ያሸለሙ አምራች ዜጎች መሆናቸውን፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤትና ቀበሌዎችን የገነቡ፣ ቤተ ክርስቲያን ያነፁና መልካም መስተጋብር የፈጠሩ መሆናቸውን መኢአድ አብራርቷል፡፡

ከቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ተፈናቀሉ የተባሉ የአማራ ተወላጆችን በሚመለከት ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ለክልሉ ብዙኅን መገናኛ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹ምንም የተፈናቀለ ሰው የለም፤ ለመመለስም የተያዘ ዕቅድ የለም፤ ከ2001 ዓ.ም በኋላም ስለዚህ ጉዳይ የወጣ ዕቅድ የለም፤ ሰፋሪዎችንም በሚመለከት የተወሰነ ውሳኔ የለም፤›› ብለዋል፡፡

ደን በመጨፍጨፍና በማቃጠል መሬት በሕገወጥ መንገድ ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ 33 ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መደረጋቸውን እንጂ፣ ሰፋሪዎች እንዲነሱ አለመደረጋቸውን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

‹‹ችግሩ ከሰፋሪዎች ጋር እንዲያያዝ መደረጉ ትክክል አይደለም፤›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ 22 ሺሕ ዜጎች በጉራፈርዳ ሰፍረው እንደሚገኙና 1,520 ዜጎች ከሚኒት ጎልዲያ መውጣት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ንብረትና ሀብት በማፍራታቸው ‹‹መውጣት የለባቸውም›› በሚል አሁንም እየኖሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሸኮ ወረዳና ደቡብ ቤንች የነበሩት፣ መኒሻሻ ላይ ያሉት ሁሉ በሰላም እየኖሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽፈራው፣ ከ500 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደማንኛውም የክልሉ ተወላጆች ተከባብረው፣ ተፋቅረው በሚኖሩበት አገር ‹‹ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ በፍፁም የተሳሳተ ነው›› ብለዋል፡፡

ከጉራፈርዳ ተፈናቀሉ የተባሉትን የአማራ ክልል ተወላጆችን ጉዳይ ለማጣራት ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው ማቅናቱን፣ ተፈናቃዮቹም አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በመኢአድ ቢሮ ተጠልለው መክረማቸውንና ወደ ደብረ ብርሃንም መወሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡


No comments:

Post a Comment