በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማና በሎጊያ የሰሞኑ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ህዝብ ውጥረት፤ የክልሉ ነዋሪዎችና ባለስልጣንት የመወያያ ርእስ ሆኖ ነው የሰነበተው። ሁኔታው በአፋሮች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን ነው፤ ከግማሽ ደርዘን የሚበልጡ አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሰጡ ነዋሪዎች የገለጹት።

የጸጥታ ውጥረቱ የተጀመረው እንዲህ ነው፤ በሳምንቱ መጀመሪያ አንድ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ከባለቤቱ ጋር በሚኒባስ ሲጓዝ ሁለቱም ተገደሉ። ከዚህ ግድያ አስቀድሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት አንድ የ17-ዓመት የአፋር ተወላጅ በፌዴራል ፖሊስ አባላት መገደሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ግድያው በተካሄደበት የሸንኮር አገዳ ልማት ጣቢያ በጥበቃ ስራ የተሰማራው ወጣት የተገደለውም ትጥቁን እንዲፈታ በፖሊስ ተጠይቆ፤ ትእዛዙን ባለመቀበሉ እንደሆነ ምስክሮች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።