Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 15, 2012

በዓል ድሮ ቀረ” የሚያሰኘው የፋሲካ ገበያ


                            
 

 By Reporter
                                                   
ወ/ሮ ትዘዘው ባይለየኝ በ1956 ዓ.ም. ከጎንደር ሲመጡ በወቅቱ የዶሮ ገበያ ዋጋ መደነቃቸውን ዛሬም ያስታውሳሉ፡፡ ጎንደር በሃምሳ ሳንቲም ይሸጥ የነበረ ዶሮ አዲስ አበባ በሁለት ብር ሲሸጥ አይተው ጉድ ብለው ነበር፡፡

ከ48 ዓመታት በኋላ ባለፈው ረቡዕ 160 ብር ያወጣል የተባለውን ዶሮ በመገረም እያዩ፣ “ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋጋ መለዋወጥ ቢኖርም አንድ ዶሮ 160 ብር ግዢ ስባል እኔም እንደ ሰው በዓል ድሮ ቀረ ማለት አሰኝቶኛል፤” ሲሉ የተናገሩት ሾላ ገበያ ውስጥ ነው፡፡

የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ትዘዘው በአሁኑ ጊዜ ገበያ ወጣ ብሎ የዕቃዎችን ዋጋ መጠየቅ እያሳቀቃቸው እንደሆነ የተናገሩት በብስጭት ነው፡፡ “በየቀኑ ሁሉም ነገር ዋጋው ጨመረ ይባላል፡፡ የእኛ የጡረታ ገቢ ደግሞ እንኳን ዋጋ ተጨምሮ፣ ለወትሮም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤” ብለው፣ “እኔ በበኩሌ አሁን የሚያሳስበኝ በዓል አይደለም፡፡ በዚህ ቅጥ አንባሩ በጠፋ ገበያ በዓል ቢቀርም አይደንቀኝም፡፡ ህቅታችን እስክትወጣ ድረስ ግን የእንጀራና የሽሮ ነገር በጣም ያሳስበኛል፤” ብለው ከገበያው ምንም ሳይገዙ ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዘጋቢ መርካቶ ዶሮ ተራ አካባቢ የተወዳጃቸው ገበያተኛ የልጆች አባት ዶሮ ይመርጣሉ፡፡ እያነሱ ይመዝናሉ፡፡ ኩልኩልቱን ይመረምራሉ፡፡ ጥፍሩን ያያሉ፤ ከዚያም ዋጋውን ከሻጩ ጋር ይደራደራሉ፡፡ ይከራከራሉ፡፡ አጠገባቸው ደግሞ አዛውንቱ ባዘቶ ፀራቸውን እየደባበሱ፣ ፂማቸውን እየጎነተሉ በዓይናቸው ይቃኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ዕድሜያቸው ወደ ሰማንያ እየተንደረደረ መሆኑ የሚያሳብቅባቸው አዛውንት ነጭ፣ ራሱ የከበደውን ዶሮ መርጠው አነሱ፡፡ ‹‹ስንት ነው?›› አሉ የያዙትን ዶሮ ክንፉን ጨምደድ አድርገው እያስጮሁ፡፡ ወይዘሮ ነጋዴዋ፣ 165 ብር መሆኑን ተናገሩ፡፡ ‹‹የአንዱ ዋጋ ነው!›› ግራ እንደመጋባትም እንደመደናገጥም እያላቸው ዶሮውን ሲያስቀምጡ፣ በቢጫ ፌስታል ጀርባቸው ላይ ያንጠለጠሉት ሽንኩርት ወደ ፊታቸው በመምጣቱ ሊቃኑ ከበዳቸው፡፡ በዚያም ላይ ያረጀች ጥቁር ኮታቸው የኑሯቸውን ደረጃ ታሳብቃለች፡፡

ቆፍጣናዋ ነጋዴ የሚሉትን ብለው እየማሉም እየተበሳጩም ያስተናግዳሉ፡፡ ጠያቂ ብቻ እንጂ ገዥ በመጥፋቱ ትክን ያሉ መስለዋል፡፡ እዚያው ገበያ ውስጥ እንደአጋጣሚ ጓደኛዬ ዶሮ ሲገበያይ አገኘሁት፡፡ ‹‹አሁን ለዚህ ዶሮ አምስት ብር አልጨምርም ትላለህ? በል ውሰድ መቼም በዓል ነው ብዬ እንጂ አያዋጣኝም…፤›› ይህንን የተባለው የገበያ ጓደኛዬ፣ መጀመርያ የ140 ብር ዶሮን ከአዟሪ በ120 ብር ሊገዛ ፈልጎ ሳይቻለው ሲቀር ወደ ዶሮ ተራ ማምራቱን ነግሮኛል፡፡ እዚህም በ155 ብር የተጀመረው ክርክር በ130 ብር ሲታሰር ነበር የአምስት ብር ጨምርና ቀንስ ንትርኩ የመጣው፡፡

በመርካቶ ገበያ ሴቶች በብዛት፣ ጥቂት ደግሞ እንደ ሽበታሙ ያሉ አዛውንቶችና፣ ከእሳቸው ትንሽ ደልደል ያለ ኪስ ያላቸው ደመወዝተኞችም ጎራ ይላሉ፡፡ የመርካቶ ዶሮ ገበያ የዋጋው መናር ብቻ አይደለም ሰቀቀኑ፡፡ የአንዳንዱ ዶሮ ሻጭ ቁጣና ስድብም እግዚኦ የሚያሰኛቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹም እጥፍ ይመልሱለትና የውስጥ ብሶታቸውን ሁለቱም እስኪበቃቸው ያወርዱታል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከበዓል ሳምንት ቀደም ብሎ የሚገዛው ዶሮ እስከ በዓል ድረስ ሳይሞት መቆየቱም ሌላው ሰቀቀን ነው፡፡ አንዴ ራሱን አንዴ ክንፉን እየነካኩ ‹‹ይሞት ይሆን፣ በሽተኛ ነው መሰል›› የሚለው ስጋት በመርካቶ የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንድ ተባራሪ ነጋዴዎች ዋጋ ቀነሰ ብላችሁ ‹‹እንዳትደነዝዙ›› በማለት ምክር መሰል ማስጠንቀቂያ ይለግሳሉ፡፡ ይቺን ተገን ያደረጉ አንዳንድ ገዥዎች ታዲያ አይ የዋዜማው ዕለት ብገዛ ይሻለኛል እያሉ ትተው ይሄዳሉ፡፡

አንዳንዱ የዶሮ ዋጋ የበግ ዋጋ እኮ ሊሆን ነው ይላል፡፡ እውነትም፣ የዘይት፣ የሽንኩርቱ፣ የቅቤው፣ የበርበሬው፣ የእንቁላልና ሌላ ሌላ ወጪው ሲታሰብ፣ የሰውንም ጉልበት ካከልንበት አንድ ዶሮ ሠርቶ ለመብላት በትንሹ ስድስት መቶ ብር ያስፈልጋል፡፡
በአዲሱ ገበያ፣ ያየናቸው ጥቂት ገበያተኞች ደግሞ እንደ መርካቶዎቹ ብዙዎች እግረኞች አልነበሩም፡፡ ከመንገድ ዳር መኪኖቻቸውን ያቆሙና የሚፈልጉትን በግ  በዓይናቸው ይመርጣሉ፡፡ በዓይናቸው ላትና ሽንጡን ያገላብጣሉ፡፡ ታዲያ የነጋዴው እንክብካቤም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ጠብ እርግፍ ይላል፡፡ ሰው ሁሉ የመኪናው ወንበር ላይ እንደተንፈላሰሰ ገዝቶ ቢሄድ በምን እድሉ፡፡ ከዋጋ ይልቅ የሚያሳስባቸው የበጉ ይዞታ ስለሆነ ጥርሱን ሳይቀር እየፈለቀቀ፣ የበጉን ሁለት እግሮቹን ወደ ሰማይ እየወደረና እየለቀቀ አገላብጦ ያሳያቸዋል፡፡ ከወደዱት የተባሉትን ይከፍሉና ያለ ጭቅጭቅ እብስ ይላሉ፡፡

ከእግረኞች ጠያቂዎች ገዝቶ የሚሄደው በጣት የሚቆጠር ስለሆነ፣ ‹‹ጠይቆ ለመሄድ እንጂ መቼ ይገዛሉ፤›› ይሏቸዋል፡፡ የማይገዙ ለመሰሉት፣ ነጋዴው የማይመስል ዋጋ እየጠራ ካጠገቡ ያርቃቸዋል፡፡

ዝቅተኛ ዋጋቸው ከ1500 ብር በታች የሆኑ ጠቦቶች ማግኘት አይታሰብም፡፡ ደህና ሙከትን 3000 ብር ሲጠራበት እንደዘበት ነው፡፡ ሥጋ ነጋዴዎች በአንድ በሬ እስከ 3000 ብር የዋጋ ጭማሪ እንደገጠማቸው ሲገልጹልን የነበረው፣ ለፋሲካ ገና ሁለት ሳምንት ሲቀረው ነበር፡፡ ስድስት ሺሕ የነበረው ስምንት ሺሕ ሲባል፣ ዘጠኝ ሺሕ የተገዛው 12000 ብር እንደደረሰ ነጋዴዎቹ ተናግረው፣ ከዚህ የበለጠ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ሲገልጹ፣ ‹‹ገና ምን አይተህ…›› ይላሉ፡፡

ቅቤ አንደኛው 200 ብር ተሸጧል፡፡ በ160 ብር ደግሞ ዝቅተኛው ሲገበይ ከርሟል፡፡ ደቃቃና እርጥብ ሽንኩርት እስከ ዘጠኝ ብር፣ ደህናውን ግን እስከ 13 ብር በየሰፈሩ ካሉ አትክልት ቤቶች የተሸጡበት የፋሲካ ሰሞን ገበያ፣ ለወትሮውም የማይስማሙትን ገዥና ሻጭ ይብሱን ያነታረከ ነበር፡፡ ነጋዴው ‹‹እኛ አላስወደድነው፤ በውድ እየገዛን እኛስ ምን እናድርግ…›› የሚሉ ቃላትን እየመዘዘ አንዴ ሲለሳለስ እንዴም ‹‹ከገዛህ ግዛ…›› በማለት ብስጭቱን ይለቀዋል፡፡

በበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ብቻ አልነበሩም እንዲህ ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ ያሳዩት፡፡ የጾሙን ወራት ተገን አድርገው የአትክልት ምርቶች ዋጋም ንሮ ከርሞ ነበር፡፡ ለአብነት ፎሶልያ በኪሎ ስምንት ብር ገደማ ሲሸጥ የቆው ከጾሙ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እስካሁን ሲሸጥ የቆየው በኪሎ 25 ብር ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በአትክልት ተራ ባለፈው ሳምንት ረቡዕና ሐሙስ ቀናት በነበረው ገበያ ወደ 11 ብር ዝቅ ማለቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጎመንም እንዲሁ ተወዷል የሚባልበት ዋጋ ይጠራለታል፡፡ ቲማቲም በኪሎ አምስት ወይም ስድስት ብር ሲሸጥ የነበረበት አጋጣሚ በጾሙ ወቅት ግን ከ13 ብር በላይ ሲሸጥ ከርሟል፡፡ አንዲት እስር ጎመን በሁለት ብር ይገዙ የነበሩ አሁን ከአምስት ብር በላይ ይጠየቃሉ፡፡

እጅግ በርካታ ጎብኚዎችን ሲያስተናግድ የከረመው የኤግዚብሽን ማዕከሉ ‹‹አዲስ ንግድ ለእድገት›› የፋሲካ ንግድ ትርዒት፣ እንደሚገባው ሰው ብዛት ሸምቶ የሚወጣው ይህን ያህል ቢሆንም፣ አንዳንድ ምርቶች ከመሸጫ ዋጋቸውን መጠነኛ ቅናሽ አሳይተዋል፡፡ ለአብነት እንደ ጫማና አልባሳት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ግን ለንግድ ትርዒቱ ሲባል የተደረገ እንጂ በመሸጫ አካባቢያቸው ቅናሹ አይታይም፡፡

ደህና ገበያ ከነበራቸው ሸቀጦች ዘይት ዋናው ነው፡፡ መቶ በመቶ ከኑግ እንደተመረቱ የሚገልጹ ጽሑፎች የሰፈሩባቸው የአገር ውስጥ ዘይቶች በሊትር 43 ብር ተሸጠው ነበር፡፡ የመያዣ ዕቃቸውም እንደዋጋቸው ሁሉ ለገዥዎች የተስማሙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት የፋሲካ በዓል መዳረሻ ሰሞን 140 ብር ገባ የተባለው አንደኛ ደረጃ ቅቤ የብዙ ሸማቾችን ስሜት ነክቶ ነበር፡፡ አንድ ኪሎ ቅቤ 140 ብር ለመግዛት አቅም ያነሳቸው ሸማቾች “ለሽታ” ብለው ሩብ ኪሎ ቅቤ ሲሸምቱ መታየታቸውና ቅቤ ሻጮችም ይህንን ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ለሩብ ኪሎ የሚሆን መለኪያ ይዘው እንደማያውቁ የገለጹበት ያምናው ገበያ፣ “ምነው ባይበላስ፣ ሆድ እንደሁ አየሁ አይል. . . .” ሲባልለት እንደነበር አሁን ይብሱን ዋጋው ተሳቅሎ ሲያሳቅቅ ይታያል፡፡

ለዚህም ይመስላል ዘንድሮ ቅቤ ነጋዴዎቹ የሸማቹን አቅምና ጥያቄ መሠረት አድርገው የሩብ ኪሎ መለኪያ ለማዘጋጀት የተገደዱት፡፡ በዘንድሮው ገበያም እስከ ሩብ ኪሎ የሚደርስ መለከያ ቀድመው ማዘጋጀታቸውን መናገር ወይም ማስታወቅ ሳያስፈልጋቸው በአብዛኛዎቹ የቅቤ መሸጫ መደብሮች፣ የሩብ ኪሎ መለኪያ ጠጠሮች ከዓይን የተሰወሩ አይደሉም፡፡ ዘንድሮ የቅቤ ዋጋ ደግሞ ከአምናውም ከፍቷል፡፡ ከሩብ ኪሎ በታች የሚፈልግ ቢኖር እንኳ ለክቶ መሸጥ ግን ከባድ እየሆነ ነው፡፡

እንደ ቅቤ ሁሉ ባሳለፍነው ዓመት ተወደደ ተብሎ የነበረው የጤፍ ዋጋ ዘንድሮ ለይቶለት ከ40 በመቶ በላይ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ በሚያዝያ 2003 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት 950 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ በዚህ ሳምንት አጋማሽ 1300 ብር ደርሷል፡፡

950 ብር ይሸጥ የነበረ መለስተኛ ጤፍም ከ1100 እስከ 1200 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ እርግጥ ከጥቂት ወራት በፊት እስከ 1700 ብር መሸጡ የሚታወስ ነው፡፡

ከቅቤና ከጤፍ ምርት የበለጠ በዘንድሮው የፋሲካ ዋዜማ ዋጋው የተሰቀለው ዶሮ ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ጥሩ የሚባል ሥጋ ያለው ዶሮ ከ90 እስከ 100 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ በዘንድሮው ገበያ ግን እስከ 200 ብር ድረስ ዋጋ የሚጠይቀበት ዶሮ አጋጥሟል፡፡  በአብዛኛው ግን ከ130 እስከ 170 ብር ደርሶ ግብይት ሲካሄድበት ቆይቷል፡፡

የበዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን ከበዓል ውጭም ባለው ጊዜ የገበያ ዋጋ እያደገ መምጣት ሸማቹን ከግብይት እንዲቆጠብ እያደረገውም ይመስላል፡፡

No comments:

Post a Comment