Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Friday, April 20, 2012

የፍትህና የነጋድራስ ጋዜጣ አዘጋጆች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ኢሳት ዜና:-
የፍትህና የነጋድራስ ጋዜጣ አዘጋጆች ፍርድ ቤት ቀረቡ፣ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ተጨማሪ አቤቱታ ቀርቧል::  በእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ የፍርድ ቤት ዘገባን አዛብተው አቅርበዋል በማለት የፌዴራል ዐቃቤ ህግ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤቱታ ባቀረበባቸው መሠረት መልስ እንዲሰጡ ፍርድ ቤት የተጠሩት የፍትህና የነጋድራስ ጋዜጦች ዋና አዘጋጆች በጽሑፍ ምላሽ ሰጡ፡፡

በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ችሎቱ ቢሰየምም፣ የፍትህ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያቀረበው የፍርድ ቤት የመልስ ወረቀት እያንዳንዱ ገጽ በአንድ ገጽ ያልታተመ በመሆኑና በጀርባ ገጽ ጭምር መታተሙ አግባብ አይደለም ያለው ፍርድ ቤቱ፣ የነጋድራስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሱራፌል ግራማ በበኩሉ በቃል መልስ ለመስጠት በመምጣቱ በአግባቡ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ ለከሰዓት 8፡30 ተቀጥሮ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

በከሰዓት በኋላው ችሎት ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች የመልስ ወረቀት የተቀበለ ሲሆን ግራ ቀኙን አይቼ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት 2፡30 ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቻለሁ ብሎ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ዐቃቤ ህግ በፍትህ ጋዜጣ ላይ በተለይ አብሮ የሚሄድ ሌላ አቤቱታ አለኝ በማለቱ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎታል፡፡ የፌዴራል አቃቤ ህግ- በተመሳሳይ የምናቀርበው አቤቱታ ተያያዥ ስለሆነ ከቀጠሮው በፊት ከቀድሞው አቤቱታ ጋር እንዲያያዝልንና የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም አሁኑኑ በቃል መልስ እንዲሰጡልን እንዲደረግ እንጠይቃለን በማለት ዝርዝሩን በንባብ አሰምቷል፡፡ ዐቃቤ ሕግ- በቀድሞው አቤቱታችን እንደገለጽነው በተለይም ፍትህ ጋዜጣ የፍርድ ቤት ተግባርን ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት፣ የዐቃቤ ህግ የክስ አቀራረብን የፈጠራ ሥራና የሀሰት አስመስሎ በዘገባ በማቅረብ በፍርድ ሂደት ላይ ባለ ነገር ላይ የቅድሚያ ብይን ሰጥቶ የፍርድ ሥርአቱን ክብር አጉድፏል ብሏል፡፡

አሁንም ይህ የጋዜጣው ተግባር ያልቆመ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በሚያዚያ 5 ቀን 2004 ዓ.ም እትሙ ገጽ 4 ላይ “ማቆሚያ ገደብ ያጣው የምስኪኗ እናቴ እንባ” በሚል በክንፈሚካኤል ደበበ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት ተብሎ በቀረበው ጽሑፍ ከመጨረሻው 2 አንቀጾች ከፍ ብሎ በሚገኘው አንቀጽ- “ምስኪኗ እናቴ ሚሊዮኖችን በግፍ ውሳኔያቸውና ፍርዳቸው አስነብተውና አስለቅሰው እንዳለፉት የንጉሱና የደርግ ዘመንኞች ሁሉ የዛሬውም የነርሱ ተተኪ የሆኑት የአምባገነኑ ኢህአዴግ ፍርድ ቤት ዳኞች በእኔ በልጇ ላይ የሚበይኑትንና የሚያነቡትን ግፍና ጭካኔ የተሞላበትን የፍርድ ውሳኔያቸውን ለመስማት ወደዚህ ፍርድ ቤት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል በመመላለስ ላይ ናት፤ እነሱም ይህን የግፍ ፍርዳቸውን በማንበብ እንደሚተባበሯት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

 እንደሷ ሁሉ እኔም ለመስማት ጓጉቻለሁ ” ብሎ መጻፉን በንባብ አሰምቶ ይህ የፍርድ ቤቱንና የዐቃቤ ህግን ክብር የሚነካ ነው ብሏል፡፡ በዚህ ላይ አስተያየትህ ምንድን ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ የጠየቀው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ- እኔ መልስ ልሰጥ የመጣሁት ዐቃቤ ህግ ቀደም ሲል ባቀረበብኝ አቤቱታ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ ይህን አዲስ የተናጠል አቤቱታ ገና አሁን ማድመጤ ነው፣ ስለዚህ አሁን ምንም ዓይነት መልስ ለዚህ መስጠት እቸገራለሁ፤ ስለዚህ ከድርጅቱ ጠበቃ ጋር ተነጋግሬ በቀጠሮው መልስ እሰጣለሁ፣ አሁን አልተዘጋጀሁበትም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኝ ተነጋግሮ ቀደም ሲል የያዘውን የውሳኔ ቀጠሮ ፣ ሚያዚያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ፣ አለመሰረዙን ገልፆ ተጨማሪ ትዕዛዝ በንባብ አሰምቷል፡፡ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ዐቃቤ ህግ በተጨማሪ ላቀረበበት አቤቱታ ከቀጠሮው በፊት በሬጂስተራር ጽ/ቤት በኩል በጽሑፍ መልስ እንዲሰጥና ፍርድ ቤቱም አንድ ላይ ግራ ቀኙን ተመልክቶ በእለቱ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታውቆ ችሎቱ ተበትኗል፡፡ በእለቱ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅን የፍርድ ቤት ውሎ ለመከታተል በርካታ ወጣቶችና የህግ ባለሙያዎች በሰፊው ፍትህ አዳራሽ የታደሙ ሲሆን ጋዜጠኛውንም አበረታተውታል፡፡

የፍትህ ጋዜጣ ለፍርድ ቤት ያቀረበው መልስ እጃችን ላይ የገባ ሲሆን በአጠቃላይ ይዘቱ ተመስገን በአቃቢ ህግ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል። ተመስገን ደሳለኝ ለፍርድ ቤት ያቀረበውን መልስ በድረ ገጻችን ላይ ማንበብ እንደሚችሉ ለማስታወቅ እንወዳለን። ኢሳት ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋዜጦችን ሳንሱር ለማድረግ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን መዘገቡ ይታወሳል። ኢሳት ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋዜጦችን ሳንሱር ለማድረግ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን መዘገቡ ይታወሳል።

  

                                                                                            

No comments:

Post a Comment