የፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ስርዓት እና በአንድ ግለሰብ ላይ የተከማቸ ስልጣን ዋንኛው ችግር፤ ቋማዊ የስልጣን ሽግግርን ሊያስተገብር አለማስቻሉ ነው፡፡ በአብዛኛው እንዲህ ያሉ የስልጣን ሽግግር መንገዶች በተጻፉ እና ዋጋ ባላቸው ሕገ መንግስቶች ውስጥ ተካተው ይገኛሉ፡፡
ቢሆንም ቅሉ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እና ኃይልን በማንአለብኝነት የመጠቀም አካሄድ ከጥቅም ውጪ አድርጎ ለሚንዳቸው፣ ተቋማት ቅቡልነትንም ሆነ ህዝባዊ ከበሬታን ሊያተርፉ አይችሉም፡፡ ይልቁኑም ስልጣንን የማስተላለፍ ግድ-ባይነት በተለያዩ ተቀናቃኞች መሀል መራር ሽኩቻን ይቀሰቅሳል፡፡ የተቀናቃኞች እንደአሸን መፍላት፣ ሀይልን በማንአለብኝነት የመጠቀም ተፈጥሯዊ ውጤት ነው፡፡ ስልጣን/ ኃይል ከቅቡልነት ማዕቀፍ ውጪ ሲተገበር፤ ለስልጣን ተፎካካሪዎች የሚያስተላልፈው መልእክት ተነጥቆ መወሰድ ያለበት ነገር መሆኑን ነው፡፡ ይህም የተቀናቃኞችን ሽኩቻ ያንረዋል፡፡ ሌላው የፈላጭ ቆራጭ ኃይል መልፈስፈስ የሚያስከትለው ውጤት ለህዝባዊ አመጽ የመነቃቃት አዝማሚያን ነው፡፡
እስከ ጊዜው ድረስ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ያለ አንዳች ተቃውሞ ሲቀበሉ የኖሩ ሰዎች የአፋኙን ሀይል
መዳከም ሲያስተውሉ በድንገት ለማመፅ የሚገፋፋ ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ የአፋኙ አገዛዝ ሀይል የሚዳከመውም በሁለት መልኮች ነው፡፡ አንድም በገዥ ልሂቃኑ መካከል ላለው የስልጣን ሽኩቻ ሳቢያ ሲሆን አልያም የአፈና መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉት እንደ ፖሊስ እና መሳሪያ አንጋች ኃይሎች ያለ በቂ ጠባቂ መቅረት የሚያስከትለው ውጤት ነው፡፡ ቀደምሲል ምሉዕ ታማኝነታቸውን ሲገልጹ የነበሩት እነኚህ አፋኝ ኃይሎች አሁን በተልፈሰፈሰው ወይም በሞተው አምባገነን የተነሳ እየፈራረሰ ያለ የስልጣን ስርዓትን ምስል ማየት ይጀምራሉ፡፡
መዳከም ሲያስተውሉ በድንገት ለማመፅ የሚገፋፋ ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ የአፋኙ አገዛዝ ሀይል የሚዳከመውም በሁለት መልኮች ነው፡፡ አንድም በገዥ ልሂቃኑ መካከል ላለው የስልጣን ሽኩቻ ሳቢያ ሲሆን አልያም የአፈና መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉት እንደ ፖሊስ እና መሳሪያ አንጋች ኃይሎች ያለ በቂ ጠባቂ መቅረት የሚያስከትለው ውጤት ነው፡፡ ቀደምሲል ምሉዕ ታማኝነታቸውን ሲገልጹ የነበሩት እነኚህ አፋኝ ኃይሎች አሁን በተልፈሰፈሰው ወይም በሞተው አምባገነን የተነሳ እየፈራረሰ ያለ የስልጣን ስርዓትን ምስል ማየት ይጀምራሉ፡፡
ከላይ የተገለፀው ማብራሪያ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ይገልጻል፡፡ አቶ መለስ እስካሁን ሞተውም ሆነ በበሽታቸው የአልጋ- ቁራኛ ሆነው አሊያም ጥቂት ጊዜያት ቀርቷቸው፣ በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡- የስልጣን ክፍተት በመኖሩ እና ስልጣኑን ለመያዝ የሚራኮቱ ተቀናቃኝ ሀይሎች ሽኩቻ መጀመራቸውን፡፡ እስካሁን ድረስ የኢህአዴግ መንግስት ስለ አቶ መለስ ሁኔታ አስተማማኝ መረጃ ሊሰጥ የማንገራገሩ ሀቅ እንኳ፣ የአቶ መለስ ጊዜ ለማብቃቱ በቂ ማመላከቻ ነው፡ ፡ “በህክምና እየተረዱ ነው!” የሚለው ማረጋጊያ ወይም “እረፍት ላይ ናቸው፤ በቅርቡ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ!” የሚሉት ማስተባበያዎች ህዝባዊ አመፅ እንዳይቀሰቀስ ለመከላል እና አሁን እየተካሄደ ያለውን የስልጣን ሽኩቻ አሸንፎ የሚወጣ አንጃ በውል እስኪለይ ድረስ ደባብቆ ለመቆየት የተነገረ ቅጥፈት ነው፡፡ በኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ላይ የተጨመረው ጠንካራ ተቋም ያለመመስረት ውድቀት፣ የአቶ መለስ የሁለት አስርተ ዓመታት አገዛዝ ምንያህል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ኪሳራ እንደነበር አመላካች ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳስባቸው ጉዳይ የአቶ መለስ አሊያም የተከታዮቻቸው እጣ ፈንታ ሳይሆን በድህረ-መለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት አዳዲስ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ነው፡፡ ሀሳቤ መጪውን ጊዜ መተንበይ አይደለም፤ የወደፊቱ ጊዜ ካለፉ ሁኔታዎች ብቻ ተነስቶ የሚጓዝ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የታሪክ የጉዞ አቅጣጫ በተለያዩ ለመተንበይ በሚያስቸግሩ ተለዋዋጭ ቶች/ጉዳዮች (variables) እንዲሁም ባብዛኛው ሰዎች እና ግለሰቦች በሚወስዷቸው ውሳኔዎች ላይ ይመሰረታል፡፡ የወደፊቱ ጊዜ በፈጠራ የተሞላ ሂደት(creative process) ውጤት ከመሆኑም በላይ በወጥነቱ አዲስ በመሆኑ ለመተንበይ የማያስችል ያደርገዋል፡፡ በሂደቱ ላይ የሚሰጥ ትንታኔ ሊያደርግ የሚችለው ትልቁ ነገር ሊከሰቱ ይችሉ ይሆናል የሚላቸውን መላምታዊ ሁኔታዎች (scenarios) ፣ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እና ነገሮች ወዴት ሊያድጉ እንደሚችሉ(potentialities) ማቅረብ
እንጂ መተንበይ አይደለም፡፡
ከዚህ በፊት እንደተጠቆመው፣ የአቶ መለስ ሞት ወይም ከተግባር ውጪ መሆን የስልጣን ሽኩቻ ፈጥሯል፡፡ ይህም የስልጣን ሽኩቻ በኢህአዴግ ውስጥ በዋናነት በወሳኙ ኃይል በህወሓት ፓርቲ መሀል እየተከሰተ ነው፡፡ ‹‹ተፅእኖ ፈጣሪ›› በተባሉ ግለሰቦች ዙሪያ የሚከሰቱት የአንጀኝነት ሁኔታዎችም የዚህ መገለጫ ናቸው፡፡ የነዚህን ግለሰቦች ስም ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የተባሉቱ ግለሰቦች ወሳኝ ተዋንያን ይሁኑ አሊያም ሆነው እየቀጠሉ ያሉ ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡ እጅግ ያልተረጋገጠ የስልጣን ክፍተት ባለበት ሁኔታ ውስጥ፤ ባብዛኛው እምብዛም የማይታወቁ ግለሰቦች ወደ መድረኩ ብቅ ይላሉ፡፡ አዳዲስ አንጃዎች ሊፈጠሩ መቻላቸው አንድ ነገር ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የበፊቶቹ ሊጠፉ ወይም ከአዳዲሶቹ ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ በሌላ አባባል በህወሓት ውስጥ የሆነ አዲስ አወቃቀር መጠበቅ ይገባናል፡፡ የተፎካካሪ ሃይሎች የተለየ መቀናጀት ሊከሰት ይችላል፡፡
አሸናፊው አንጃ የታጠቁ ሃይሎቹን የድጋፍ መሰረት የሚይዝ ወይም የሚያረጋግጥ መሆኑ ሊጠበቅ የሚችል ነው፡፡ በዚህ አፍላ የስልጣን ትግል ሁኔታ ውስጥ የትኛውም ግለሰብ ወይም አንጃ የራሱን ፍላጎት ያለ አፋኝ ሃይሎቹ ድጋፍ ሊጭን አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ህወሓት ብቻ ቢያንስ በዚህ ወቅት የታጠቁ ኃይሎቹን ታማኝነት ሊ ያገኝ ስለሚችል፤ ሃይል የተቀላቀለበት አካሄድ እንኳን ቢከተል በስልጣን ላይ ሊቆይ መቻሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከውስጣዊ የስልጣን ስርጭት በኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ርዕሰ-መንግስት ሆነው ቢቀጥሉ እንኳ ማስመሰያ መሳሪያ ከመሆን አያልፉም፡፡ እንደኔ ግምት ከሆነ የአቶ ኃይለማርያም ምሉዕ አቅም አልባነት እንዳለ ሆኖ አሸናፊው አንጃ እሳቸውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ደረጃ ከፍ በማድረግ ነገሮች እስኪሰክኑ ድረስ ሁኔታዎችን በጥበብ መያዣ ሊያደርገው ይችላል፡፡
እንዲህ ያለውን ሁኔታ ምን አይነት ነገሮች ሊቀይሩት ይችላሉ? አንዱና ወሳኝ ጉዳይ ሊሆን የሚችለው ወታደሩ የራሱን ፖለቲካዊ ፍላጎት በማዳበር የህወሓትን የሲቪል ክንፍ ሃይል በማንኮታኮት ወደ ስልጣን መገስገሱ ነው፡፡ ይህ ክስተት የመሆን እድሉ ያን ያክል እሩቅ አይደለም፤ ልምድ እንደሚያሳየው አንድ አንጃ በሌላው አንጃ ላይ የበላይነት ለማግኘት ሲል ለጦር ሰራዊቱ ጥሪ ባቀረበ ቁጥር በሰራዊቱ ውስጥ የስልጣን ጽኑዕ ፍላጎትን ይቀሰቅሳል፡፡ ሠራዊቱ እራሱ ሥልጣኑን ለራሱ መጠቅለል ሲችል ለሌላ አካል መስራት ለምን ያስፈልገዋል? ነገር ግን ይህ ሁኔታ ሊከሰት የሚችለው ሰራዊቱ አንድነት ሲኖረው ነው፡ ፡ ካለበለዚያ በውስጡ ያሉ ቅራኔዎች በተለይም በከፍተኛ እና ዝቅተኛ መኮንኖች መሀል ወይም በተለዩ ከፍተኛ ባለማዕረጎች መሀል ያለ የሀሳብ ልዩነት ገኖ ከወጣ ሠራዊቱን ሊያሽመደምደው እና የሲቪሉን አመራር እንዲቀበል ሊያስገድደው ይችላል፡፡
ሁለተኛው የህወሓት አገዛዝን መቀጠል አደጋ ላይ ሊጥል የሚችለው ጉዳይ ህዝባዊ አመጽ ነው፡፡ የህዝቡን እየተንተከተከ ያለ አጠቃላይ መማረር ስንመለከት፣ የሕወሓት አገዛዝ ካለ ጠንካራና ታማኝ የአፈና ኃይል ሊቀጥል ስለማይችል ማንኛውም የመዳከም ምልክት ህዝባዊ ዓመፅን ያበረታታል፡፡ የአጠቃላይ ህዝባዊ ዓመፅ መከሰት ደግሞ ሁኔታውን በበለጠ ያወሳስበዋል፡፡ የደም አፋሳሽ ግብግብ መጀመር እጅግ አደገኛና ከቁጥጥር የወጡ ነገሮችን በማስከሰት ገዢውን ፓርቲና ሰራዊቱን የበለጠ ይከፋፍላል፡፡ አንደኛው ከቁጥጥር የወጣ ክስተት የብሔር አፀፋዊ መልስ ነው፡፡ የሁለት አስርተ-ዓመታት ብልሹ አገዛዝ እና የኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ መጥለቅለቅ ህዝባዊ ቁጣን ወደ መንግስት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ወደ ብሔር ቡድኖችም እንዲያነጣጥር ያደርጋል፡፡ እንዲህ ያሉ አንዳንድ ግብግቦች ኢህአዴግን በመሰነጣጠቅ ሰዎች ከመደባቸው አሊያም ከብሔራዊ አንድነታቸው ይልቅ በብሔር አጥራቸው እንዲሰባሰቡ ያደርጋሉ፡፡
ሌሎችም ጉዳዩን የሚያወሳስቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፡- የኤርትራ አካሄድ፣ እጅግ ከፍተኛ ህዝባዊ መነሳሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ ኤርትራ የኔ ናቸው የምትላቸውን ግዛቶች ለመቆጣጠርና የባድመን ወታደራዊ ድል ለመበቀል ወደ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ልትገባ ትችላለች፡፡ ሌላኛው ለመገምገም እጅግ አስቸጋሪ የሚሆነው ጉዳይ ደግሞ የተቃዋሚው ሚና ነው፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ራሱን እንደ አንድ የተጠናከረ እና የተባበረ ኃይል አድርጎ ካቀረበ እንደብሔር ግብግቦች ያሉ እጅግ አስከፊ ሁኔታዎችን በማስቀረት ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወት ይችላል፡፡
ህዝባዊ መነሳሳት ከተከሰተ ይህ ተቃዋሚ ኃይል ራሱን እንደ አማራጭ መንገድ ማቅረብ ይቻለዋል፡፡ በዚያም አለ በዚህ ሕወሓትን የመተካት እድሉ የሚወሰነው በህዝባዊ አመጽ መከሰት ላይ ነው፡፡ ያኔም እንኳ፣ እንዲሁ እንደተከፋፈለ ከቀጠለ ያን ያህል ተጽእኖ አይኖረውም፡፡ መድረክ ራሱን ወደ ግንባር ደረጃ ማሸጋገሩን እንደ መልካም ዜና እወስዳለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም፡፡ ከህወሓት አንፃር እውነተኛ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ፤ ህብረቱ ሊተማመኑበት የሚገባ ሊሆን ከማስፈለጉም በላይ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብሎም ቢሮክራሲውንና ወታደራዊ መዋቅሩን ሊያግባባ ያስፈልገዋል፡፡
በመጨረሻም፣ የምዕራባውያን ኃይሎች ቀጥተኛ ተሳትፎ እና እውነተኛ ተጽእኖ ሁሉንም ተፎካካሪ ኃይሎች ሊወክል የሚችል መንግስት ለማቋቋም የሚደረገውን ጉዞ በማቀላጠፍ ይህነው የሚባል ተጽእኖ ሊያሳርፍ አልቻለም፡፡ የምዕራባውያን ተጽእኖ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሰትን ወይም የህወሓት ዳግም ወደ ስልጣን መመለስን ማስቀረት ይችላል፡፡ የህዝባዊ መነሳሳትን ጭምር ሊከላከል ይችላል፡፡ የምዕራባዊያን ተጽእኖ ውጤታማ እንዲሆን መሰረት የሚሆኑ ሁለት አበይት ጉዳዮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
1ኛ) ምዕራባውያን ኃይሎች ራሳቸው የተባበረ ግንባር መፍጠርና እንደ ታማኝ አደራዳሪ መቅረብ
መቻል አለባቸው፡፡
2ኛ) ተቃዋሚው ጎራ በበኩሉ በአንድ ድምጽ ተባብሮ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግስት
እንዲቋቋም አሳማኝ በሆነ መንገድ ሊከራከር ይገባዋል፡፡,ይህ የመጨረሻው አማራጭ እጅግ
ተመራጭ ነው፣ ምክንያቱም ይህ ብቻ የሰላማዊ ሽግግር ተስፋ ነውና !
No comments:
Post a Comment