Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, July 31, 2012

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕመም የዋልድባ መነኰሳት ተጠያቂ ተደረጉ


  • ከአብረንታንት እና ማይ ለበጣ ሁለት መነኰሳት ወደ ማይ ፀብሪ ተወስደዋልበዶንዶሮቃ 50 በላይ የመነኰሳት እና መነኰሳዪያት ቤት በፖሊስ ተፈትሿል
  • ከፖሊሶቹ አንዲቱ ከጾታዋ የተነሣ ወደ ዋልድባ ለመግባት የማይፈቀድላት ሴት ናት
  • የአብረንታንቱ አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ እንደታሰሩ ናቸው
  • 49 ያላነሱ የቤተ ሚናስ መነኰሳት በፖሊስ ይፈለጋሉ
  • ‹‹እናንት ምታታሞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም ተጠያቂዎች ናችሁ›› /የማይ ፀብሪ ፖሊሶች/

(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 23/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 30/ 2012)ምሽቱን ወደ ገዳሙ በገቡት ዐሥር ያህል የማይ ፀብሪ ፖሊሶችና ታጣቂዎች የተወሰዱት ሁለት መነኰሳት አባ ወልደ ጊዮርጊስ ከዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም፣ አባ ገብረ ማርያም ጎንዴ ከማይ ለበጣ (የማኅበረ መነኰሳቱ ሰፊው የአትክልት ቦታ) ናቸው፡፡ ሁለቱ አበው መነኰሳት በፖሊሶቹ ተይዘው ከመወሰዳቸው አስቀድሞ በኣቶቻቸው በፖሊሶቹ ፍተሻ እንደተካሄደበት ተገልጧል፡፡ ከፖሊሶቹ አንዲቱ ከጾታዋ የተነሣ ወደ ዋልድባ ለመግባት የማይፈቀድላት ሴት መኾኗ የወረዳው አስተዳደር ለገዳሙ ትውፊታዊ ሥርዐትና ክብር መጠበቅ ያለውን የወረደ ግንዛቤ የሚያሳይ ነው፡፡
ትናንት ምሽት በገዳሙ ውስጥ ከተካሄደው ፍተሻ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ዓርብ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2004 .ም፣ ከጠዋት እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በዋልድባ ዶንዶሮቃ ገዳም የሚገኙ ከኀምሳ ያላነሱ መነኰሳትና መነኰሳዪያት ቤት ቁልፎች በኀይል እየተሠበሩ ፍተሻ እንደተካሄደበት ተመልክቷል፡፡
ኻያ ስምንት ያህል የገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት የሁለቱን አባቶች መወሰድ በመቃወም ወደ ማይ ፀብሪ ተጉዘው አቤቱታቸውን ለማቅረብ ወደ ወረዳ ከተማው ከሚወስደው ፅርጊያ መንገድ ሲደርሱ በፖሊሶቹ የኀይል ርምጃ መገታቱ ተነግሯል፡፡ የጉዟቸው መገታት ብቻ ሳይኾን ‹‹መመለሳቸውም አሳሳቢ ነው ብለዋል›› ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የተናገሩ አንድ የገዳሙ መነኰስ፡፡
ያለፈው ሳምንት መጨረሻ መጠነ ሰፊ ፍተሻ እና እስር ምክንያት በተለይ ከቆላ ወገራ የመጡ ናቸው በተባሉ አርሶ አደሮች ድንገተኛ ርምጃ እንዲሁም በጅብ መንጋና በእባብ በፕሮጀክቱ የጥበቃ ኀይል አባላት እና ሠራተኞች የሕይወት እና አካላዊ ደኅንነት ላይ ደርሷል የተባለው ጉዳት ነው፡፡
አስገራሚው ጉዳይ ግን በሽታቸው ይኹን የወቅቱ መገኛቸው አነጋጋሪ ስለኾነው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጽኑ ሕመም የፀለምት - ማይ ፀብሪ ፖሊሶች በመነኰሳቱ ላይ የተናገሩት ቃል ነው - ‹‹እናንተ ምታታሞች [ምትሃተኞች] ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕመም ተጠያቂዎች ናችኹ፡፡››
በተደጋጋሚ በወረዳው ፖሊስ ድብደባ፣ እንግልትና እስር ተጋልጠው ከሚገኙት የዋልድባ አብረንታንት ቤተ ሚናስ መነኰሳት መካከል ‹‹ፕሮጀክቱን እንቃወማለን፤ ለገዳማችን ክብር እና ህልውናም እንሰየፋለን›› በሚል ግልጽ ተቃውሞ ያሳዩ 49 መነኰሳት ስም ዝርዝራቸው ተይዞ በፖሊስ እየተፈለጉ መኾኑን ምንጮች ከስፍራው ገልጸዋል፡፡ ፖሊሶቹ በየጊዜው እየመጡ መነኰሳቱን እየለዩ ለሚያደርሱት እንግልትና እስር ከዋልድባ ቤተ ሚናስ መነኰሳት ጋራ የአስተምህሮ ልዩነት ያላቸው የዋልድባ ቤተ ጣዕማ መነኰሳት ‹‹ተባባሪዎች ናቸው›› ተብሏል፡፡ ሐምሌ 13 ቀን 2004 . ከዋልድባ አብረንታንት ገዳም በማይ ፀብሪ ፖሊስ ተወስደው የታሰሩት መነኮስ አባ ገብረ ሥላሴ ዋለልኝ አሁንም ያልተለቀቁ መኾናቸውን ምንጮቹ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በተለይም ከሰኔ ወር ጀምሮ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክትና የዛሬማ ወንዝ ግድብ በዋልድባ ገዳም ላይ ከሚያደርሰው ተጨባጭ አደጋ እና ታሳቢ ስጋቶች ጋራ ተያይዞ በፀለምት - ማይ ፀብሪ ፖሊስ በማኅበረ መነኰሳቱ ላይ የሚደርሰው ወከባ፣ እስርና እንግልት ተባብሶ ስለ መቀጠሉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ማይ ፀብሪ ፖሊሶች እንደተናገሩት ለገዳማቸው ክብርና ህልውና መጠበቅ የቆሙት ጽኑዐኑ የዋልድባ ማኅበረ መነኮሳትምታታሞችባይኾኑም÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ዜናዊ የተያዙበትን ጽኑ ሕመም እንደ እግዚአብሔር ተግሣጽ (እንደ መቅሠፍት) የሚቆጥሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ጥቂት እንዳልኾኑ በሕመማቸው ዙሪያ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚተላለፉ መልእክቶች ያስረዳሉ - ‹‹ደዌ ዘመቅሠፍት›› እንዲሉ፡፡
በርግጥም ሰው ኾኖ መታመም የሚያነጋግር ባይሆንም የታላቁ ገዳም መነኰሳትና ባሕታውያን አባቶች የዘወትር ሐዘንና ልቅሶ÷ በተለይም በዚህ የሱባኤያቸው ወቅት÷ ግዳጁን አይፈጽምም ለማለት አይቻልም፡፡

No comments:

Post a Comment