Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, April 25, 2012

ለዳያስፖራው የተዘጋጀው መድረክ ብሶቶች ተስተናገዱበት

 ሪፓርተር ጋዜጣ
ለዳያስፖራው መረጃ ለመስጠትና ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገር መፍትሔ ለማፈላለግ በተጠራው የውይይት መድረክ፣ አብዛኛዎቹ የዳያስፖራ አባላት ብሶታቸውን ሲገልጹ ዋሉ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ደግሞ “ዳያስፖራውም ብሶታቸውን እኛም ብሶት ካወራን ለውጥ አናመጣም፤ አብረን እንሥራ፤” ብለዋል፡፡

ትላንት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደውና በአቶ ኃይለ ማርያም በተመራው የዳያስፖራውና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የውይይት መድረክ፣ የዳያስፖራው አባላት የፍትሕ እጦት፣ ሙስናና የቢሮክራሲ ችግሮች በአገሪቷ ተንሰራፍተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ሰርቫንቱ (የመንግሥት ሠራተኛው) በአግባቡ አገልግሎት አለመስጠትና የዳኝነት መጓደል በተለይ ጐልተው ከዳያስፖራው የተሰነዘሩ ችግሮች ሲሆኑ ከጉምሩክ፣ ከመሬት፣ ከሪል ስቴትና ከባንክ ጋር የተያያዙ ውጣ ውረዶች ለሥራዎቻቸው እንቅፋት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡መንግሥት ሁሌም ችግራችሁን ተናገሩ ይላል፡፡ ሆኖም ችግሮች ሲፈቱ አይታይም፡፡ የዳያስፖራው ቢሮ ቢቋቋምም አጥጋቢ መልስ አናገኝም ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ብሶታቸውን አሰምተዋል፡፡

በኢሉአባቦር አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን የገለጹ የስብሰባው ተካፋይ፣ “አገራችን ገብተን እንድንሠራ ይጮሃል፤ ሆኖም አገራችን ስንገባ የምናየው ሌላ ነው፡፡ ገብተን ከምንሠራው ገብተው ጥለው የሄዱት ይበልጣሉ፡፡ ኢሉአባቦር ላይ የጀመርኩት የእርሻ ሥራ ቢኖርም ውጣ፣ እንገልሃለን ተብያለሁ፡፡ የቡና እርሻችን ላይ እሳት ተለቆብናል፡፡ ከብት በእርሻ ላይ ይለቀቃል፡፡ ያልደረስንበት ቦታ የለም፡፡ እንገልሃለን ቢሉኝም መስዋእትነት ከፍሎ አገሬ በነፃነት እንድኖር ያደረገኝ ሕዝብ ስላለ ብሞትም ልሙት ብዬ እታገላለሁ፡፡ የዳያስፖራው ቢሮ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው፡፡ ለመተንፈስ ያህል እንተንፍስ እንጂ መፍትሔ የለም፤” በማለት የሚፈጸምባቸውን በደል በመከፋት አሰምተዋል፡፡

ደንበኛ ንጉሥ ነው የሚለው አሠራር ቀርቶ ሠራተኛው ንጉሥ የሆነበት አሠራር መንሰራፋቱን፣ ሁሉም ነው ባይባልም ሲቪል ሰርቪሱም በአብዛኛው ክፍተት ያለበት መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከላይ ጥሩ ፖሊሲና ጥሩ አመራር ቢኖርም ታች ሲደረስ ያለው አሠራር ልማትን የሚያደናቅፍና ለመሥራት የተነሳሳውን ሞራል የሚገል ነው ተብሏል፡፡ “ወደ አገራችን ስንገባ መንገላታቱ የሚጀምረው ከጉምሩክ ነው፤” ያሉም ነበሩ፡፡ የታክስ ክፈል አትክፍል ክርክር ብቻ ሳይሆን ታክስ እንክፈል ተብሎም ጉዳዮች በፍጥነት እንደማያልቁና የአሠራር ክፍተቱ የጐላና የሚያማርር እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ተሳታፊውን ለማያቋርጥ ጭብጨባ የዳረገውና መድረክ የሚመሩትን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ዮሐንስ አያሌውን፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒሰትሩን አቶ መኩርያ ኃይሌን፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ነጋ ፀጋዬን ፈገግ ያሰኘው፣ “የሊዝ አዋጁ ከወጣ በኋላ ሕዝቡን ለምን ማወያየት አስፈለገ? አወያይታችሁስ ያገኛችሁትን ግብዓት ታካትታላችሁ? አዋጁን ትሽራላችሁ? አወያይታችሁ ምን አደረጋችሁ?” የሚለውን ጥያቄ ያቀረቡት ከፈረንሳይ የመጡት ወ/ሮ ገነት አየለ ናቸው፡፡

በነፃ ገበያ ሥርዓትና በዋጋ ግሽበት መናር ላይ ምን ተሠራ፣ ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሠራ ለምን አይፈቀድም? የሚሉ ጥያቄዎችና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ማዕከልና የዳያስፖራ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ቢቋቋም የሚሉ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ዮሐንስ አያሌው ነፃ ገበያንና የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም ብዙ ለውጥ አልመጣም፡፡ ስለሆነም የገበያ ሥርዓቱን አስተካክሎ የመነሻና የመድረሻ ዋጋ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የብድር ችግር አለ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ በብድር ጥያቄው ላይ በተፈጠረ ችግር ካልሆነ በስተቀር አዋጭ ፕሮጀክቶች እስከቀረቡ ድረስ ብድር የመስጠት ችግር እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው በባንክና በኢንሹራንስ ዘርፍ ለምን አይሳተፍም ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ በመንግሥት በኩል በተገባው ቃል መሠረት ጥናቱ እየተደረገ ነው፡፡ ጥናቱ እንዳለቀ በመንግሥት በኩል ውሳኔ ያገኛል ብለዋል፡፡

የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩርያ ኃይሌ በበኩላቸው ቤቱን በስፋት ላስጨበጨበው የሊዝ አዋጁ ጥያቄ በመንግሥት በኩል ክፍተትና ውስንነት እንደነበረ አምነዋል፡፡ መነሻውም አዋጁ ለሦስተኛ ጊዜ በመውጣቱ ነው፡፡ ከሕዝቡም ጥያቄ ያስነሳል የሚል እሳቤ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከሕዝቡ ጋር በተደረጉት ውይይቶች መሠረት የተገኙ ግብዓቶች በደንቡ ላይ ገብተዋል ብለዋል፡፡ ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሰው መድበው ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

የቤት አቅርቦትን በተመለከተ ዳያስፖራው መቶ በመቶ የሚከፍልበትና ቤት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያገኝበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡ ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ የቀረቡት አስተያየቶች ከግልጽነትና ከተጠያቂነት ጋር የመጡ መሆናቸው ከባለሥልጣኑ ተደምጧል፡፡ በሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች ከብቃትና ከአመለካከት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ሥልጠና እየተሰጠ ግምገማም እየተደረገ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ በአሠራሩ ላይም አዲስ ሥርዓት ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ታቅዷል ተብሏል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ውይይቱን ሲያጠቃልሉ ሲቪል ሰርቪሱ በሚገባ አገልግሎት እንደማይሰጥና የመንግሥት ሠራተኛው ንጉሥ እንጂ አገልጋይ እንዳልሆነ ለተነሳው ጥያቄ፣ ይህ ሊሆን እንደሚችልና ሲቪል ሰርቪሱ በሚሰጠው አገልግሎት ጥራት ላይ ክፍተት እንዳለ ይታወቃል ብለዋል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው ብለው፣ ‹‹ከደርግ ጋር ሲነፃፀር ይህንን ለውጥ ያስመዘገብነው ትንሽም ቢሆን ስለሠራን ነው፤ በማለት አስረድተዋል፡፡ 

“መድረኩ የተዘጋጀው ብሶት ሰምተን ብሶት መለዋወጫ ለማድረግ አይደለም፡፡ ተወያይተን በጋራ ታግለን ችግሩን ለመፍታት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ካልተሳተፈ ችግሩን ለመፍታት አንችልም፡፡ አብረን መፍታት እንችላለን፡፡ ሲቪል ሰርቫንቱ በደንብ እየሠራ አይደለም ተብሎ መነገሩ ራሱ የሚፈጥረው ነገር አለ፡፡ በየክልሉ የዳያስፖራ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ አሁን የሰሙትን ችግር ሰምተው ዝም ካሉ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እኛም እንደዚህ ስንቀጠቀጥ ቆይተን ችግር የማንፈታ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በቀጣይ የተነሱ ችግሮችን ፈትተን መገናኘት አለብን፤” ብለዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪሱና በዳኝነት በኩል ችግር መኖሩ በመንግሥት በኩል የታመነበት ቢሆንም ለውጥ መምጣቱ መዘንጋት የለበትም ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ያሉትን አሠራሮች ወደ ሕዝብ እያወረዱና ሕዝቡ የችግሩ ፈቺ አካል እንዲሆን የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል በማለት ገልጸዋል፡፡

መኪናና ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ከዳያስፖራው ለተነሳው ጥያቄ አቶ ኃይለ ማርያም ሲመልሱ፣ “እናንተ ተሰብስባችሁ እዚህ ስለተወያያችሁ እናንተ ብቻ ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም፡፡ ሁለት ሚሊዮን ዳያስፖራ ቢኖር 79 ሚሊዮኑ ኢትዮጵያዊ አገር ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ሁሉም በመኪና መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ይህ ቅንጦትም አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው መኪና ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የመጠየቅ መብት አለው፡፡ አሠራሩ ፍትሐዊ መሆን ስላለበት መንግሥት ተሳስቶ የወሰነውን የቀረጥ ነፃ መብት ለሁሉም መዝጋት ነበረበትና ዘግቷል፡፡ አገር ውስጥ ያለውም ታክስ ይከፍላል፡፡ መኪና ከቀረጥ ነፃ አይደረግም፤ አይሆንምም፡፡ ታክስ የሚቀነስም ከሆነ ለዳያስፖራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መቀነስ አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ የፖሊሲ ጥያቄ ነው፤” ሲሉ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተው ስብሰባው ተጠናቋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment