Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, April 22, 2012

ከተገኘ ነውጠኛ ሊሆን ነው ቃተኛ

ይድረስ ላስጠራዥ – መለስ ዜናዊ
ከተጠራዥ ስደተኛ – ዳዊት አበበ ,  ኦስሎ ( ኖርዌይ)

በሽተኛ – የማስታወስ ችሎታዬ ከጠፋ ሰነባብቷል ፣አንዳንድ ጊዜ በመንገድ ላይ ሆኘ ሳለሁ ከቤቴ ተነስቼ ወደ ቢሮዬ መሄዴን ? ፣ ወይ ደግሞ ከቢሮዬ ወጥቼ ወደ ቤቴ መመለሴን እስከማላውቅበት ድረስ ይምታታብኛል መድሃኒቱ ምንድነው ብሎ ይጠይቃል ዝንጉው- ህመምተኛ ሳይካትሪስቱን ፡፡

ሳይካትሪስቱ – በእንደዚህ ባለ ሁኔታ ላይ ማድረግ ያለብህ ነገር ቢኖር ፣ ዘወትር ወደ ሥራህ ስትሄድ የምሳ ዕቃ መያዝህን አትርሳ ፡፡ የምሳህ ዕቃ ባዶ በሆነበት ሰዓት ወደ ቤትህ መመለስህን ተገንዘብ ፡፡ የምሳህ ዕቃ ደግሞ ምግብ በያዘ ጊዜ ወደ ቢሮህ እንደምትሄድ ያስታውስሃል ፡፡ መድሃኒቱ እሱ ነው ብሎ ይመልስለታል የስነ ልቦናው ሃኪም፡፡

እኝህ ያገራችን ጉልበተኛ መሪ ፣ ሳይካትሪስት አያስፈልጋቸውም ብላችሁ ነው ጃል ? እኔ በዚህ ሃሳብ ስጸና ፣ ብዙዎች ደግሞ የለም ! እሳቸው ለቀቅ ፥ ለቀቅ የሚያደርግ የውሸት ህመም ወይም (pathological lier ) ስለሆኑ ጠበል የሚወስዳቸው አጥተው እንጂ ህመሙ የመጃጃት አይደለም የሚሉ አሉ ፡፡ እኔ እንኳ ከላይ እንዳለው ቀልድ ሳይካትሪስት ያስፈልጋቸዋል ያልኩበት ምክንያት ፣ እዛችው ፓርላማ ውስጥ ፣ ሃያ አመት ሙሉ ሲያገሱ ፣ ሁልጊዜ ቀደሞ ያሉትን ነገር እረስተው እንደገና ሲደረማምሱት ስላስተዋልኩኝ ነው ፡፡ የፓርላማውን በር ግን ስለመሳታቸውና ስለመደረማመሳቸው ያልኩት ነገር የለም፡፡

A pathological liar is someone who often embellishes his or her stories in a way that he or she believes will impress people. Some think a pathological liar is different from a normal liar in that a pathological liar believes the lie he or she is telling to be true at least in public and is “playing” the role. 

ለቀቅ ፣ ለቀቅ ስለሚያደርጋቸው ህመም ፣ በውኑ ይህ ደዌ ተጸናውቷቸዋል ወይ ? ብለን ምክር ቤቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ሃኪሞችን እንዳንጠይቅ – ለጊዜው ያሉት አንድ ታማኝ ተቃዋሚ የጥርስ ሃኪም እንጂ ፣ የአይምሮ ሃኪም ስላልሆኑ ፣ ለሳቸው አሳልፎ ማስመርመር ደግሞ በአረንጓዴው ጓደኛዬ ቅጠል የሳሳውን ጥርሳቸውን ሊያውልቋቸው ስለሚችሉ ፣ እኛም በአፈ- ላማ እንዳንያዝ ባናነሳው ቢቀርብን ይመረጣል፡፡ ምናልባት ባዮሎጂስቱ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በዳማ ከሴ ወይ ባንካሴ የጠቅላይ ሚንስትራችንን በሽታ እንዲገላግሉን እንማልዳቸዋለን፡፡ አለበለዚያ ምድረ ነውጠኛን ቃተኛ ላደርገው ነው እያሉ ማስፈራራቱን ስለተያያዙት በጠፋ የመኽር ዝናብ ጤፋችንን በቃተኛ ባይጨርሱት መልካም ነው፡፡

አቶ መለስ ፣ ልክ እንደቀልዱ ፣ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንም ሆነ ወደ ምክር ቤት መሄዳቸውን ያጡት እየመሰሉ ነው ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የምገዛት አገር ኢኮኖሚዋ አድጎ ፥ አድጎ ተስፈንጥሮ 11% ደርሷል እያሉን ከርመው ፣ በቅርቡ መምህራን በደመወዝ ጭማሪው አለመርካት ለተወሰነም ቀን ቢሆን ያደረጉትን የሥራ ማቆም አድማ ፣ለማጣጣል ሲሉ የተጠቀሙበት ያልተሞረደ ቋንቋ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ንቀት አሳድሮባቸዋል፡፡ አቶ መለስ የመምህራኑን ጥያቄ ለማጣጣል በሚመስል የመፍጨርጨር ትንተና ሲንዘባዘቡ እንዲህ አሉ፡፡

በአገራችን ባለው ደሞዝ የረካ የለም ፡፡ የኑሮ ዉድነቱ ከፍ ያለ ነው ፡፡ ጥሩ ደመወዝ አይከፈልም ፡፡ ይህን እናቃለን፡፡ ለዚህ ማስታገሻ ደሞዝ ብንጨምር – ግሽበቱን ከፍ ስለምናደርገው አንሞክረውም ፡፡ ለዚህ ማስተካከያ ያደርግነው ነገር ቢኖር ፣ የደመወዝ ርከን ነው ፡፡ መምህሩ የደመወዝ ጭማሪና ፣ የርከን ጭማሪ ስላልገባው ነው የተምታታበት፣ መምህሩ 99.9 % በተደረገው የርከን ማስተካከያ የተደሰተ ነው አሉን፡፡እግዜር ያሳያችሁ ፣ ከዋሹ አይቀር እንዲህ ሽምጥጥ አድርጎ ነው ፡፡ የደመወዝ ጭማሪና ፣ የርከን ማሻሻያ ያልገባው መምህር ፣ ምን አይነት ተማሪ ይፈጥር ይሆን ? ይህ ንቀት አይደለም ?

አቶ መለስ ፣ ኧንደው ለአፋቸው ሻብያ ፣ ሻብያ ፣ ይላሉ እንጂ ፣ ከሻብያ በላይ እሳቸውን ምርር አድርጎ የሚያበሳጫቸው ነገር ቢኖር ፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስም ሲጠቀስ ነው ፡፡ ምድረ ነውጠኛ ሰሞኑን ፣ መምህራን ባደርጉት አድማ ፣ ቋምጦ – ቶሎ ቶሎ በሉ እንጂ ! አቀጣጥሉት እንጂ ! እያለ የውስጥ አርበኞቹን ይዞ ቢሞክርም አልተሳካለትም በማለት ምርር ብለው ሲናገሩ ፣ የሻብያን ደጃፍ ግን ፣ ቢያንስ በወር ፥ ወር ፣ እንደሚያንኳኩ ፣ በአመትም እስከ አስራ አምስት ጊዜ ያህል ለማንኳኳት እንደሞከሩ ለሻብያ በተንቦጫቦጨ አንጀታቸው ይገልጹና ፣ ነውጠኞች ግን ከሻብያም በላይ ደመኞቻቸው እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ 

የአቶ ኢሳይያስ መንግሥት አበሳጭቶ ስላባረራቸው ኤርትራውያን ዜጎች በመቆርቆር ከግብጽ ድረስ የተበተኑትን የኤርትራ ወጣት ኃይሎች ፣ የግብጽ መንግስት ለኢሳይያስ መንግሥት ሊያቀብላቸው በደረሰ ጊዜ ፣ ግብጾችን በማግባባት ኤርትራውያንን እንደታደጉዋቸው እንዲህ ይገልጻሉ፡፡አንዳንድ አገሮች አስገድደው ይሄን ስደተኛ ፣ ወደ ኤርትራ ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ፣ ይህን እንዳያደርጉ ፣ ለማግባባት ጥረት እያደረግን ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት ፍላጎቱ የሌላቸው ለምሳሌ ከግብጽ ወደ ኤርትራ እንዲመልሳቸው ያልፈለጉ የተወሰኑ ወጣቶችን ፣ በግብጽ መንግሥት ፈቃድና በስደተኞቹ ፣ ፍላጎት ወደ ኤርትራ ከምንመለስ ይልቅ ፣ ወደ ኢትዮጵያ እንድንሄድ እንፈልጋለን ብለው ሲጠይቁ ፣ ከግብጽ መጥተው ኢትዮጵያ እንዲጠለሉ እየተደረገ ነው ፡፡ አሉን አቶ መለስ በእርሳቸው አርአያ ጠፍጥፈው ለፈጠሩት ፓርላማ ፡፡

እድለኞቹ የኤርትራ ወጣቶች ፣ አንቺ ምን ቸገረሽ ሁለት እናት አለሽ እንዲሉ ፣ በክብር መጥተው ኢትዮጵያ እንዲኖሩና በከፍተኛ ደረጃ ባሉ ዩንቨርስቲዎችም በነጻ እንዲማሩ ሲደረግ ፣ አቶ መለስ ባሳለፍነው የግንቦት ወር ኦስሎ ኖርዌይ ፣Energy for all ተብሎ በተጠራው ጉባኤ ላይ ፣ ባለ ሁለት መልኩን መለስን በመቃወም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ፣ እጅጉን ቅያሜ ስለገባቸው ፣ጊዜ ጠብቀው ፣ ተቃዋሚዎቻቸውን ለመበቀል ከኖርዌይ መንግሥት ጋር በመዋዋል ታላቅ ንግድ ተዋዋሉ፡፡ 

አቶ መለስ በግንቦቱ የኦስሎ ጉባኤ የተደረገባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ አስመልክቶ ፣ የኖርዌይ ጋዜጠኛ ባደረገላቸው ጥያቄ –ይህን ድምጽ ይሰሙታል ? በመንግሥትዎ ላይ የተደረገ ተቃውሞ ነው ፣ ለዚህ መልስዎ ምንድነው ? ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት መልስ ፣ – እንኳን ውጭ አገር ቀርቶ አገራችንም ቢሆን ዜጎች በተቃውሞ ሰልፍ ይወጣሉ ፡፡ ይህ ተቃውሞ ልክ እንደዚህ ደመና ነው ፤ ቀስ እያለ ይጠፋል ነበር ያሉት ለጋዜጠኛው፡፡ ዕለቱ በርግጥም ደመናማ ነበርና፡፡

አንዳንድ አገሮች አስገድደው ስደተኛውን ወደ ኤርትራ ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ፣ የኢሳይያስ መንግሥት እንዳይበላቸው ታደግናቸው ያሉት መለስ ፣ ኢትዮጵያውያንን ያለፍላጎታቸው ተገድደው ከኖርዌይ እንዲመለሱ ለምን ተስማሙ ? ምድረ ነውጠኛን ለማሸማቀቅና ለመምታት ፣ እንዲሁም ወደ አገሩ ተገድዶ በሚመለስበት ጊዜ እንደቃተኛ ሰልቅጦ ለመብላት የተደረገ እንቅስቃሴ እንደሆነ ፣ ኖርዌይ ውስጥ ያለው ስደተኛ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

አቶ መለስ እኛን ለማስመለስ የሚደረግልዎት የርዳታ ዳረጎት በብዙ ሚልዮኖች ክሮነር እንደተጨመረልዎት ኖርዌይ ውስጥ በታተሙት ጋዜጦች አንብበናል ፡፡ አሁን በቅርቡ ከሥልጣናቸው እንዲባረሩ በተደርጉት የርዳታ ሚንስቴር ጓደኛዎ ኤሪክ ሱልሃይም እንደተጨመረልዎት ተረጋግጧል፡፡ የቅርብ ጓደኛዎት ኤሪክ ሱልሃይም ኖርዌይ ውስጥ ባሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ታላቅ ሥራና የማጋለጥ ትግል ፣ ከቦታቸው ለጊዜው ገለል ተደርገዋል፡፡ ፣ ኖርዌይ ውስጥ ባለው አሠራር ደግሞ ፣ ይህ ክርበታ ያልተለመደ ነው ፡፡ 

አሁንም ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ድምጻችንንም በአለም ዙርያ እንዲሰማ እንታገላለን፡፡ በምንም አይነት ሁኔታ ለጌታቸው አሰፋ ደህንነት ማሰቃያና ማስገደያ ቄራ ጭዳ አንሆንም፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!

No comments:

Post a Comment