Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, April 26, 2012

የዓለም አቀፉ የፕሬስ ቀን በውዝግብ ታጅቦ ከነገ ጀምሮ ይከበራል

ኢሳት ዜና:-
 የዓለም አቀፉ የፕሬስ ቀን ከነገ ሚያዝያ 18-21/2004 ድረስ በአዋሳ ከተማ ለጋዜጠኞች በሚሰጥ ወርክሾፕ  ይከበራል፡፡ በዓሉን ዩኔስኮ ስፖንሰር ያደረገው ሲሆን አዘጋጆቹም በዋንኛነት የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት የአቶ አማረ አረጋዊ ድርጅት የሆነው ሆርን ኦፍ አፍሪካ የፕሬስ ኢንሰቲትዩት እና የኢህአዴግ ተለጣፊ መሆኑ የሚነገርለት የኢትዮጽያ ብሄራዊ የጋዜጠኞች ህብረት ናቸው፡፡

በኢትዮጽያ ቴሌቪዥን ባልደረባ አቶ መሰረት አታላይ የሚመራው ሌላው ተለጣፊ ኢጋማ የተሰኘው ማኀበር “ዝግጅቱ ይመለከተኛል፣መገለል ደርሶብኛል፣ልሳተፍ ይገባል” በማለት ቅሬታ ማቅረቡ ውዝግብ አስከትሏል፡፡፡ውዝግቡን ተከትሎ ሶስቱም አካላት በተናጠል  ለጋዜጠኞች እየደወሉ ስለወርክሾፑ  በስልክ ጥሪ ሲያሰተላልፉ ታይተዋል፡፡ ውዝግቡ በኮምኒኬሸን ጽ/ቤት በእነአቶ ሸመልሽ ከማል ሸምጋይነት እንዲፈታ ተደርጓል፡፡

ባለፈው ዓመት በሒልተን ሆቴል በተጠራው የዓለም የፕሬስ ቀን በዓል ላይ አቶ አማረ አረጋዊ በአንድ በኩል በሌላ በኩል የኢትዮጽያ ጋዜጠኞች ህብረትና የመንግስት ኮምኒኬሸን ጽ/ቤት እና በአቶ አርጋው አሸኔ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ የኢንቫሮመንት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ማሕበር በጋራ ሆነው በፕሮግራም አፈጻጸም ቅደም ተከተል ጉዳይ መግባባት ባለመቻላቸው አቶ አማረ ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውና በሌሉበት መካሄዱ ይታወሳል ይህ በእንዲህ እንዳለ አንጋፋው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት በፕሬስ ውጤቶች ላይ ቅድመ ምርመራ ሊጀምር መሆኑ አሳታሚዎችን አስደንግጧል በቅርቡ የዘጠና ዓመት ልደቱን  ያከበረው አዛውንቱ የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት በሕትመት ውጤቶች ላይ ቅድመ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችለውን ውል አሳታሚ  ድርጅቶች እንዲፈርሙ ማስገደድ መጀመሩን ተከትሎ የጋዜጣ አሳታሚዎች ድንጋጤያቸውን ለኢሳት ዘጋቢ ገልጠዋል፡፡

በአማራጭ እጦት ምክንያት የተቸገሩ በርካታ ጋዜጦችን በማተም ላይ የሚገኘውና ብዙዎች አንድ ለእናቱ በሚል ቅጽል የሚያውቁት ብርሃንና ሠላም “ የሕትመት ስታንዳርድ የሥራ ውል ” በሚል አዘጋጅቶ ሰሞኑን ለደንበኞቹ ባሰራጨው ውል ላይ አሳታሚዎች የፕሬስ ሕጉን እንዲያከብሩ ከመገሰጽ አልፎ ሕግ ተላልፏል ብሎ ያሰበውን አሳታሚ ጋር ያለውን ውል እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ በረቂቅ ውሉ አንቀጽ 3 ላይ “ አሳታሚው ለሕትመት የሚያቀርበው የጹሑፍ ስክሪፕት የአገሪቱን ሕግና በተለይም ፕሬስን በሚመለከት በሕግ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች  የማይጥስና ተጠያቂነት የሌለው ሕትመት የማቅረብ ግዴታ አለበት” ይላል፡፡

አንቀጽ 10.1 “ አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የጹሑፍ ስክሪፕት ሕግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው” ሲል ደንግጓል፡፡ ብርሃንና ሠላም ለደንበኞቹ የላከው ይህው ረቂቅ ውል አያይዞም በአንቀጽ10.2 ላይ “አታሚው የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ግዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል” የሚል ጠበቅ ያለ አንቀጽም አካቷል፡፡ሆኖም ይህን ያህል እርምጃ የሚያሰወስደው ጥፋት ምንዓይነት ስለመሆኑ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡ ይህው በአስገዳጅነት መፈረሙ እንደማይቀርም የሚገመተው ውል አታሚው የሕትመት የአገልግሎት ዋጋ ለመጨመር ሲፈልግ ከ15 ቀናት በፊት ለደንበኞች ማሳወቅ ብቻ በቂ መሆኑን ደንግጓል፡፡

የማተሚያ ቤቱ ዝንባሌ የገባቸው ብዙዎቹ አሳታሚዎች ድርጊቱ ቅድመ ምርመራ መሆኑን በመገንዘባቸው ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር ተመሣሣይ እርምጃ የወሰደው የቦሌ ማተሚያ ደርጅት ሕግን ይጥሳሉ ያላቸውን በእስልምና ሃይማኖት ጉዳይ ላይ የሚ,ታተሙ ጋዜጦችን አላትምም ማለቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አንድ  አሳታሚ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው  ወትሮም በቋፍ ላይ ላለው ፕሬስ ይህ ዜና  ትልቅ መርዶ ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በኢትዮጽያ ሕገመንግስት መሠረት ቅድመ ምርመራ የተከለከለ ነው፡፡በአዲሱ የወንጀል ሕግ የፕሬስ ጥፋት አሳታሚውን ብቻ ሳይሆን አታሚውን፣አዟሪውንም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ኢሳት ጉዳዩን በማስመለከት የብርሀንና ሰላም ባለስልጣናትን ለማነጋገር ቢሞክርም አልተሳካለትም።

No comments:

Post a Comment