Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Saturday, April 28, 2012

አንድ የምስራች፤ ሀገራችን ፈጣን እድገት አሳየች!

 በአቤ ቶክቻው
ትላንት ለሊቱን በሙሉ ማውጊያ ብሎጋችን ኢትዮጵያ ውስጥ የማይዘጋበትን መላ ሳንሰላስል ነበር። ታድያ አንዳች ዘዴ መጣልኝ። ልማታዊ ጨዋታዎችን  መጨዋወት ጥሩ ዘዴ እንደሚሆን አስብኩ። ታድያ ልማታዊ ዜና ከየት ይመጣል…? ብዬ ሳስብ፣ ሳስብ፣ ሳስብ… አንድ ወዳጃችን በዚህ ሳምንት ውስጥ በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ የለጠፈው አሪፍ ልማታዊ ዜና ትዝ አለኝ። 

ወዳጄ ስሙ ጠፋኝ… (ምን የስደተኛ ነገር እንኳን የሰው ስም የራሱንም ስም ይረሳል እኮ…! እናም ወዳጃችንን ይቅርታ ጠይቄ እቀጥላለሁ!) ይህ ወዳጃችን የለጠፈው የምስራች ሮይተርስን ጠቅሶ ሲሆን፤ ሀገራችን አለ የተባለ እድገት እያሳየች እንደሆነ ያወሳል። ዕድገት ቢልዎት ደግሞ ዕድገት ብቻ አይምሰልዎ “ፈጣን እድገት” ብሎ ነው የዜና ወኪሉ ሮይተርስ የገለፀው። 

ታድያልዎ ክፉ ክፉውን ብቻ ሁሌ ከምናወራ እና ብሎጋችንንም ከምናዘጋ፣ ከፀሐዩ መንግስታችንም ከምንቀያየም ለምን እንዲህ ልማታዊ ጨዋታዎችን እየተጨዋወትን ግዜውን አንገፋም ስል አሰብኩ። በርግጥ በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው እድገታችን 7.5% የሚል ነው። በዚህ ብዙ ቅር አይበልዎ። ይሄ የምናዛሬ ጉዳይ ነው ድሮም ቢሆን ቁጥር በነርሱ ሲሆን ዝቅ በኛ ሲሆን ከፍ ይላል። 

እንኳንስ ሌላ ይቅርና ሰዓት ራሱ እኛ ሰባት ሰዓት ሆኗል ስንል እነርሱ አንድ ሰዓት ነው ይላሉ። ገንዘባቸውም እንደዛው ነው። እነሱ አንድ ሲሉ እኛ አስራ ሰባት እንላለን። ባጠቃላይ እኛ ቁጥር ላይ ቁጥ ቁጥ አናውቅም እነሱ ደግሞ የቁጥር ገብጋቦች ናቸው። ስለዚህ በእድገቱም 7.5 ቢሉንም 11.2% ጋር እኩል ነው እና ደስታዎን ይቀጥሉ። አዎ መንግስታችንን ማመስገን አለብን! የእምነት ተቋማት ረዥም እድሜ ለምንግስታችን እንዲሰጠው ምዕመናኖቻቸውን ለፀሎት መጥራት አለባቸው። 

ባለውቃቢዎች የእድገት ባለቤት ያደረገን መንግስታችን ዘላለም እንዲኖር ውቃቢያቸውን መለማመን ይገባቸዋል። መጫኛ የሚያቆሙ ደብተራዎች መንግስታችንን እንደመጫኛው ቀጥ ብሎ እንዲቆም ጥበባቸውን ሊጠቀሙ ይገባል። (እዝች ጋ አሽሟጣጮች አሁንስ ተጠቅልሎ ነው ያለው? ብለው ፈታኝ ጥያቅ ቢጠይቁንም እንዳልሰማ እናልፋለን!) የዚህ አይነት ዕድገት ባለቤት ያደረገን እርሱ ኢህአዴግ የተባረከ ነው! ብለንም እንዘምራለን! እልልታውንም እናቀልጠዋለን! ሀገራችንን በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉ ሀገሮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ አሰልፏታልና! እርስዎም ይደሰቱ! … እኔ በበኩሌ ደስታዬን ለመግለፅ ድግስ ሁሉ ለመደገስ አስቢያለሁ። 

   አስቡት እስቲ ከሃምሳ ምናምን አገሮች በእድገታችን ግንባር ቀደም ከሚባሉት ወገን መሆን ከየት ይገኛል? እውነቴን ነው የምልዎ እስከዛሬ ድረስ መንግስታችን ሲናገር ለፕሮፖጋንዳ ይመስለኝ ነበር። ለካስ እርሱቴ ምን በወጣው…! በእውነቱ ስናውቅ በድፍረት ሳናውቅ በስህተት ላንጓጠጥነው እና ላሽሟጠጥነው ይቅርታ መጠየቅ አለብን! ወዳጃችን ከሮይተርስ ያገኘው ዜና ይህ ነው፤
Reuters- According to reports released by the International Monetary Fund, five of the fastest growing countries last 2011 are in Africa. This includes the countries of Ghana (13.5%), Eritrea (8.2%), Ethiopia (7.5%), and Mozambique (7.2%).
ምነው…? ምን ያስቅዎታል? አዎ ፈጣን እድገት እያሳዩ ያሉ ሀገሮች ውስጥ ተካተናል። በርግጥ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ኤርትራ በዕድገት ደረጃዋ ከእኛ ትበልጣለች። ይሁና! እባክዎ ወዳጄ አይሳቁ ብሎጉን እንዳያዘጉብን! እኔም ሳቄ ሳያመልጠኝ ልሰናበትዎ… ካልተዘጋ በዚህ ከተዘጋ በሌላ ማውጊያ እንገናኛለን!

No comments:

Post a Comment