በትግራይ ተምቤን - አቢይ አዲ የሚገኘውና በጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ስም ተሰይሞ የቆየው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስያሜው ተቀይሮ በመለስ ዜናዊ ስም እንዲሰየም መወሰኑን ታማኝ ምንጮች አስታወቁ።
በደርግ ዘመን የተሰራውና በራስ አሉላ ስም ተሰይሞ የ 9 – 10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የት/ቤቱን አቅም ለማሳደግ በሚል የ11-12ኛ መመሪያ ክፍሎችን ለመገንባት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ አዋጥተው ስራው መከናወኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል። ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው ነሃሴ ወር ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንዳለ አቶ መለስ በማለፋቸው ፕሮግራሙ መሰረዙን ሲታወቅ; ከሁለት ሳምንት በፊት በተከናወነው የምረቃ ስነ-ስርአት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በስፍራው እንደተገኙ ማወቅ ተችሎዋል።
ከምረቃው ጋር በተያያዘ የራስ አሉላ አባነጋ ስም ተሰርዞ “መለስ ዜናዊ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት” ተብሎ መሰየሙን ባለስልጣናቱ በይፋ እንደገለጹ ምንጮች አረጋግጠዋል። በት/ቤቱ በይፋ የመለስ ስም ተፅፎ መለጠፉ ተጠቁሞዋል። በህዝብ ገንዘብ መዋጮ የተገነባን ት/ቤት በጡንቻና በማን አለብኝነት ህዝብን በመናቅ የተፈጸመ ተግባር ነው ሲሉ የአካባቢው ተወላጆች ማውገዛቸው ታውቁዋል።
በተለይ በአውስትራሊያ፡ ጀርመን፡ ኖርዌይ፡ አሜሪካ፡ ካናዳና… ሌሎች አገራት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ባካሄዱት ቴሌ ኮንፈረንስ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ እንዳሉት « የአፄ ምንሊክን፡ የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስን ሃውልት ለማፍረስ የተጀመረው አፍራሽ እንቅስቃሴ ወደ ራስ አሉላ ተሻግሮዋል።
ይህ የሚያመለክተው የቆየውን የኢትዮጲያን ታሪክ ለማጥፋት ቆርጠው መነሳታቸውን ነው። ይህ ትውልድ ታሪኩን አስጠብቆ የማቆየትና የተጀመረው አደገኛ አፍራሽ እንቅስቃሴ ከማውገዝ ባለፈ ለትግል መነሳሳት አለበት።ኢትዮጲያዊያን እጅ ለእጅ መያያዝ አለብን፤» ብለዋል። አክለውም « የኢትዮጲያዊነት ጉልህ መታወቂያና መገለጫ የሆኑ አኩሪ ታሪኰችንና ታሪክ ሰሪ ጀግኖችን ለማጥፋት ኤርትራዊው ቴውድሮስ ሃጎስ፡ በረከት ስሞንና ስብሃት ነጋ የሚመሩት አካል በአገራችን ላይ የጥፋት ዘመቻ ከፍተዋል» ሲሉ አንድ ተሳታፊ ተናግረዋል። « የዶጋሊ ዘመቻ » በሚል በየአመቱ ራስ አሉላ የሚዘከሩበት ታሪካዊ ቀን እንደነበረና ሕወሓት ወደ ስልጣን ከመጣ በሑዋላ ግን ይህ እንዲቀር መደረጉን እነዚሁ ወገኖች ያስታውሳሉ።
በሌላም በኩል በመቀሌ ከተማ ፒያሳ አካባቢ የአፄ ዮሃንስን መታሰቢያ ሃውልት ለማቆም ተጀምሮ የነበረው እንቀስቃሴ እንዲቆም መደረጉን የቅርብ ምንጮች አጋልጠዋል። ባለፈው አመት ከህዝብ በተዋጣ ገንዘብ ሓውልቱን ለማቆም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ እንደነበር ጠቁመው፤ በኋላ ግን “የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ስለተቃወሙ ሃውልቱን መስራት አይቻልም» በማለት እነ ቴውድሮስ ሃጎስ መወሰናቸውን ምንጮቹ ገልፀው፦ “አሳፋሪና ተቀባይነት የሌለው ተራ ምክንያት» ሲሉ ሁኔታውን በቅርብ የተከታተሉት ምንጮች አጣጥለውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአድዋ ከተማ አደባባይ ላይ ተሰቅሎ የነበረ የመለስ ፖስተር ተቀዳዶ መጣሉን ምንጮች ጠቆሙ። የክልሉ ካድሬዎች «የመድረክ ተለጣፊ የሆነው አረና ፓርቲ ነው ይህን የፈፀመው » በማለት ያልተጨበጠ የፈጠራ ወሬ እያሰራጩና እየዛቱ ነው ያሉት ምንጮች አክለውም ድርጊቱን የፈፀመው የአካባቢው ህዝብ እንጂ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ አይደለም ብለዋል።
No comments:
Post a Comment