- የእምዬ ሚኒሊክ ሐውልትም ሊፈርስ ይችላል
Saint Petros monument |
(አንድ አድርገን ህዳር 13
2005 ዓ.ም)፡- የግብፅ
ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ
ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18
ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ
ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው ተሾሙ።
በ1928
ዓ.ም. አረመኔው የኢጣልያ ፋሺስት በግፍ አገራችንን ለመውረር ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት በማለት ውቅያኖስ አቋርጦ በመምጣት
ኢትዮጵያን ሲወርና ሕዝቧን፣ ሊቃውንቷን፣ ገዳማቷንና አድባራቷን በግፍ ሲጨፈጭፍ ያዩት ብፁዕነታቸው ወራሪውን ኃይል
ከኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎት ሊዋጉት ቆረጡ። የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሰሜኑ የአገሪቱ
ክፍል ከአረመኔው ፋሺስት ጦር ጋር በመፋለም ላይ የነበረውን አርበኛ ለማበረታታት ወደ ማይጨው በሔዱ ጊዜ ብፁዕነታቸው ተከትለው
ሔዱ። ከዚያ እንደ ተመለሱም በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ተሰባስበው የቤተ ክርስቲያን አምላክ በኢትዮጵያውያን ላይ የመጣውን
ችግር እንዲያስታግሥ በጸሎት እየተጉ ወደነበሩት አባቶችና አርበኞች በመሔድ ለአገርና ለነጻነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን
በመስበክ ሁሉም እንዲጋደሉ ማሳሰብ እና ማትጋት ጀመሩ። ኋላም የገዳሙ መነኮሳትና የሰላሌ አርበኞች ይባሉ የነበሩት አርበኞች
ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተሳታፊ ሆኑ። ከዚያም አርበኞቹ የቻሉትን ሁሉ አድርገው ወደ ሰላሌ ሲመለሱ ብፁዕነታቸው አዲስ አበባ
ቀሩ። ብዙም ሳይቆዩ በጠላት እጅ ተያዙ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስምንት ጥይት አሁን ሃውልታቸው ከሚገኝበት ቦታ ዝቅ ብሎ ባለው ቦታ
ላይ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ የባቡር
መንገድ ስራ ከተማዋን ከጊዮርጊስ ፤ በአትክልት ተራ በመርካቶ በኩል አድርጎ በአብነት ኮካ ኮላ ጋር ይገጥማት ተብሎ የታሰበው የመጀመሪያው ምዕራፍ የባቡር መንገድ ምክንያት የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ሙሉ በሙሉ ከቦታው እንደሚነሳ
ታውቋል ፤ በመሰረቱ የመንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በማንኛውም ሃገር በሚደረጉበት ጊዜ የእምነት ተቋማትንና እና ለሀገር
እና ለህዝብ ትልቅ ውለታ የዋሉትን ለስማቸው መታሰቢያ የተሰየሙ ሃውልቶችን መነካት እንደሌለባቸው ይታወቃል ፤ የአገራቸው በጠላት መወረር፣
የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ መታሰቢያቸውን ለማንሳት
በስመ የባቡር ፕሮጀክት ለዚች ሃገር የዋሉት ውለታ ፤ ለአርበኞች ያሳዩት ተጋድሎ ፤ ህዝቡ በእምነቱ አንድ በመሆን ጠላትን
እንዴት መመከለት እንዳለበት ያስተላለፉት መልዕክት ከግምት ውስጥ ሳይገባ እንደ ተራ ሃውልት ለማንሳት ሃውልቱ የቀናት እድሜ በቦታው
ላይ እንደሚቀረው የባቡር ስራ ፕሮጀክት ስራን በበላይነት የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዛሬ በሸገር ሬዲዮ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች
የእምነት ተቋማትንና ታሪካዊ ሃውልቶችን በጥናት ወቅት ለምን ግምት ውስጥ አስገብተው እንደማይሰሩ መነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል ፤ ባልጠፋ
ቦታ ዋልድባ ላይ ስኳር ልማት ማቋቋም እና ባልጠፋ መንገድ ሃውልቶችን እያነሱ መንገድ መስራት የሃገሪቱን ታሪክ ጥላሸት ከመቀባት
በላይ ሃገሪቱ አለኝ የምትላቸውን ቅርሶች ከማጥፋት የማይተናነስ ስራ መስሎ ይታየናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስለ ሚኒሊክ ሐውልት ከተማ መስተዳድሩ ያለው ነገር ባይኖር ስለ አጼ ሚኒሊክ ሐውልት ባለሙያዎች
እንደሚሉት የባቡር መንገዱ ዲዛይን ካልተቀየረ በቀር የሚኒሊክንም ሐውልት እንደሚነካው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እኛ እያልን ያለነው ሀገሪቱ ላይ
የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ለምን ቅድመ ጥናት ሲካሄድ የእምነትና የሐውልት ቦታዎች ፤ የአባቶቻችን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለኢትዮጵያ አሻራቸውን
ያስቀመጡበት ቦታ ከግምት ውስጥ አይገባም ? ወይስ ከበስተጀርባ ሌላ ነገር አለ……?..
“አይጥ ለሞቷ የድመትን አፍንጫ ታሸታለች” ይላል ያገሬ ሰው
“አይጥ ለሞቷ የድመትን አፍንጫ ታሸታለች” ይላል ያገሬ ሰው
የታሪክ ምንጭ፡- ዲያቆን መልአኩ እዘዘው
No comments:
Post a Comment