Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, November 28, 2012

ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በማንኛውም ማተሚያ ቤት እንዳይታተም መመሪያ ተላለፈ


“ጋዜጣው ቆሻሻ ይዘት ያለውና አመፅ ቀስቃሽ ነው” አቶ ሽመልስ ከማል በሚኒስትር መአረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ም/ሀላፊ  “የአቶ ሽመልሽ ንግግር የወረደ ቢሆንም የማተሚያ ችግሩ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳስተባበሉት እንዳልሆነ በግልፅ ያረጋግጣል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት“  ጋዜጣችን እንዲቋረጥ አቶ ሽመልስ ሊያዙ እንደሚችሉ ቅንጣት አልጠራጠርም” አቶ ዳንኤል ተፈራ የአንድነት ፓርቲ ም/ህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የኤዲቶሪያል ቦርድ አባል “ስራችንን አላቆምንም መረጃዎችን በኦን ላይን ሚዲያ ለማሰራጨት ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ  


ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ማተሚያ ቤት እንዳትታተም በመንግስት ትዕዛዝ መተላለፉ ታወቀ፡፡ ከነሐሴ 24 ጀምሮ በብርሃንና ሰላም እንዳትታተም በመንግስት አካላት ትዕዛዝ መተላለፉን የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል እና የአንድነት ፓርቲ ኤዲቶሪያል ቦርድ ማረጋገጣቸውንና የግል ማተሚያ ቤቶችም ጋዜጣዋን እንዳያትሙ የመንግስት ደህንነቶች እንደሚያስፈራሩ ተናግረዋል፡፡

ከብዙ ጥረትና ርብርብ በኋላ በቅርቡ ለሁለት ሳምንታት በሁለት የግል ማተሚያ ቤቶች ለመታተም በቅታ የነበረችው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ከ2005 ምርጫ በፊት በየትኛውም ማተሚያ ቤት እንዳትታተም መንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ መወሰኑ ታውቋል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ስጋት ውስጥ የገባው ኢህአዴግ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ፍኖተ ነፃነት በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት እንዳት ታተም ማድረግ ነው፡፡

ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተገኘው መረጃ በሚኒስትር መአረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የሆኑት በአቶ ሽመልስ ከማል ትዕዛዝ ጋዜጣዋ እንዳትታተም እንደተደረገች ያስረዳል፡፡ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዳግም በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት እንድትታተም የተደረገውን ጥረት ተከትሎ ከማተሚያ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያ መለክተው ነሃሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣችው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ይዘት ቁጣ የቀሰቀሰባቸው ባለስልጣናት ወደ ማተሚያ ቤቱ ደውለው ቁጣቸውን ገልፀው እንደ ነበር ነው፡፡ 

ሆኖም የአቶ ሽመልስ ከማል ግን የተለየ ነበር፡፡ ሰውየው ለማተሚያ ቤቱ ኃላፊ ደውለው  “ምንድነው እያደረጋችሁ ያላችሁት? ከአሁን በኋላ ፍኖተ ነፃነት የሚባል ጋዜጣ እንዳታትሙ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ መስጠታቸውን ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት ምንጮች ለአንድነት ፓርቲ ተናግረዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት አቶ ሽመልስ ግን ይህን እንዳላደረጉ በቁጣ ጭምር ተናግረዋል፡፡ “የተከለከላችሁት በግልፅ በወጣ ህጋዊ ምክንያት ነው” ያሉት  አቶ ሽመልስ “ጋዜጣው ቆሻሻ ይዘት ያለውና አመጽ ቀስቃሽ ስለሆነ አይታተምም” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “የፍኖተ ነፃነት ጉዳይ የሳንሱር ጉዳይ አይደለም  እናንተ ስለሳንሱር አታውቁም፡፡ እራሳችሁን አትቆልሉ፣ ትልቁ ችግራችሁ ይሄ ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በአሜሪካ ፈርስት አሜንድመንት ላይ ማንኛውም ማተሚያ ቤት የማይፈልገውን ፖለቲካ ፓርቲ የሚመለከት ጽሁፍ ያለማተም መብት አለው ያሉት አቶ ሽመልስ ብርሃንና ሰላምም የአንድነት ፓርቲን ልሳን አላትምም ማለቱ ትክክል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
 
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ የባለስልጣኑ ንግግር ጋዜጣዋን ማን እንዳፈናት የጠቆመ እንደሆነ ተናግሮ “ማንኛውንም ታትሞ ያልወጣ ፅሁፍ አንብቦ ይሄን አላትምም ማለት ግልፅ የሳንሱር ተግባር ነው፡፡ የኛ ጋዜጣ ተነጥሎ እንዳይታተም መደረጉ መንግስት የሚጠቀምበትን አፓርታይዳዊ የመከፋፈልና አንዱን ተጠቃሚ አንዱን ተጎጂ የሚያደርግ ተግባር/act of segregation/ የሚያሳይ ነው ብሏል፡፡ ዋና አዘጋጁ “አቶ ሽመልስ ገዢው ቡድን በምን አይነት የግለሰቦች እንደተሞላ የሚያሳይ ስድብ አውርደውብናል፡፡” ካለ በኋላ “ህዝቡ በምን አይነት ግለሰቦች ስር እንዳለ እንዲያውቀው የአቶ ሽመልስን ሙሉ ንግግር በድረ-ገፃችን ይፋ እናደርገዋለን፡፡ እኛ ስራችንን አላቆምንም መረጃዎችን በኦን ላይን ሚዲያ ለማሰራጨት ዝግጅታችንን ጨርሰናል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ይህን አስመልክቶ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “የአቶ ሽመልሽ ንግግር የወረደ ቢሆንም የማተሚያ ችግሩ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳስተባበሉት እንዳልሆነ በግልፅ አረጋግጧል፡፡” ካሉ በኋላ “ሰውየው እንዲህ አይነት ንግግር እንዲናገር ማን መብት እንደሰጠው አይገባኝም፡፡ እኛ ስለአሜሪካ አላነሳንም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳንሱር እንዲቀር በአዋጅም በህገ መንግስትም ተከልክሏል፡፡ እኛ በአስቸኳይ ልሳናችን ለህትመት እንድትበቃ እንፈልጋለን፤ ማተሚያ ቤቶች የማይፈልጉትን የፓለቲካ ድርጅት ልሳን እንዳትሙ የሚፈቅድ ህግ ከወጣም ለህዝብ ይፋ ሊደረግ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጨምረውም አንድነት ፓርቲ ላይ መንግስት እያደረሰ ያለውን አፈና አንድነት በቀላሉ እንደማይተወው አስጠንቅቀዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ም/የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው “ጋዜጣችን እንዲቋረጥ አቶ ሽመልስ ሊያዙ እንደሚችሉ ቅንጣት አልጠራጠርም፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአፈናው ላይ የመንግስት እጅ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያሉ ምንጮቻችን በአቶ ሽመልስ ቀጭን ትዕዛዝ ጋዜጣችን መታፈኑን አስረድተውናል፡፡” ብለዋል፡፡ አቶ ዳንኤል አያይዘውም አቶ ሽመልስ ጋዜጣዋን ቆሻሻ ይዘት ያላት ማለታቸውን ተችተዋል፡፡ “የሰውየው ንግግር  ከአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የማይጠበቅ፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው ተራ የመንደሬ ንግግር ነው፡፡ 

ሽመልስ ‹ቆሻሻ ይዘት አላችሁ› በማለታቸው ተፀፅተው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡ ‹ቆሻሻ› ብለው የሰደቡት ጋዜጣዋን ብቻ ሳይሆን አንድነት ፓርቲንና በሚሊዮን የሚቆጠር የፓርቲውን አባልና ደጋፊ ጭምር ነው” ካሉ በኋላ የሞራል የበላይነት የሌለው አካል በረጋ መንፈስ ከመነጋገር ይልቅ ተራ ስድብ ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል፡፡ ጨምረውም “የጋዜጣዋን ህትመት ለማስቀጠል ብቸኛ አማራጫችን የማተሚ መሳሪያ መግዛት ነው፡፡ ይህንንም ፓርቲው ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰበት ነው፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጠና ታመው በውጪ ሀገር እየታከሙ በነበሩበት ወቅት ስለ አቶ መለስ የጤና ሁኔታ በፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ የተጠየቁት አቶ ሽመልስ ከማል “ይሄ የእሳትና የኢሳት ወሬ ነው ጠ/ሚኒስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውና ብዙም ሳይቆይ አለቃቸው አቶ በረከት ስምኦን የአቶ መለስን መታመም ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

No comments:

Post a Comment