የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ትልቅ የአመራር ክፍተትና አሁንም ድረስ ውስጥ ውስጡን የቀጠለው የስልጣን ሽኩቻ አምባገነኑን ስርአት ክፉኛ አዳክሞታል፡፡
በኢህአዴግ ቤት ውስጥ የተፈጠረው መጠላለፍ እና በጥርጣሬ አይን መተያየት ከውጫዊው ጫና ጋር ተዳምሮ ዛሬ የ21 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረውን አንባገነናዊ ስርዓት ለማስወገድ ከምን ግዜውም በላይ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ አገዛዙን ለማስወገድ ለትግል መነሳት እንዳለበት ደግመው ደጋግመው ጥሪ እያስተላልፉ ይገኛሉ፡፡
ምንም እንኳን ብዙዎቹ እንዲሁ በደፈናዉ “ለሰላማዊ ትግል ተነሱ” ከማለት በስተቀር ብዙም በታቀደ እና ዘርዘር ባለመልኩ እንዴት መታገል እንዳለበት ለህዝቡ ሲናገሩ እና አቅጣጫ ሲሰጡ ባይደመጥ፡፡ ባለፈው አመት አጋማሽ “መንግስት በሐይማኖታችን ጣልቃ መግባት ያቁም!” በሚል በሙስሊሙ ህብረተሰብ የተጀመረው ሰላማዊ ትግል አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ትግሉ እስካሁን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዙሪያ ብቻ የተወሰነ ቢሆንም ህዝባዊ መሰረቱ በፍጥነት እየሰፋ እና ሙስሊም ካልሆነው ህብረተሰብም የሞራል ድጋፍ በማግኘት የበለጠ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
እንዲያውም በቅርቡ መንግስት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄያችንን ለመመለስ ዝግጁ ሆኖ ባለመገኘቱ ከዚህ በኋላ ትግላችንን የምናካሂደው የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ጭምር ይሆናል በማለት ማስጠንቀቂያ ያሉትን ቢጫ ካርድ ለመንግስት በአደባባይ እስከ ማሳየት ደርሰው ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህን እና ሌላም መሰል በሀገራችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት በእርግጥም አሁን ላይ ስለ ሰላማዊ ትግል በዝርዝር መነጋገር እና መወያየቱ ተገቢ ሆኖ ናገኘዋለን፡፡ ለመሆኑ ሰላማዊ ትግል ምን ማለት ነው? ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃርስ ምን ያህል አዋጪ ነው? ቀጣዩ ጽሁፍ በሰላማዊ ትግል ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይሞክራል፡፡
የሰላማዊ ትግል ምንነት
ሰላማዊ ትግል ትልልቅ የአለማችን የፖለቲካ ምሁራን ጭምር “ትክክለኛው አንባገነኖችን የማስወገጃ መሳሪያ ነው” ሲሉ የሚመሰክሩለት ትልቅ ህዝባዊ መሰረት ያለው የትግል ስልት ነው፡፡ ስልቱ ከትጥቅ ትግል በተለየ ሁኔታ ብዙ የህይወት መስዋትነት ሳያስከፍል ፣ ዜጎችን ለስደት ሳይዳርግ ፣ በንብረት ላይ ውድመት ሳያስከትል አንባገነኖችን ማስወገድ በማስቻሉ ተመራጭ ለመሆን በቅቷል፡፡
ከሰላማዊ ትግል ጋር በተያያዘ በፃፋቸው መፅሐፎቹ ዓለም አቀፍ እውቅናን ማትረፍ የቻለው የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ጅን ሻርፕ “From Dictatorship to Democracy” በተሰኘው መፅሐፍ ላይ በግልፅ እንዳብራራው ፤ሰላማዊ ትግል በዋናነት ስነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስልቶችን አጣምሮ በመጠቀም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ትግል ነው፡፡ ጅን ሻርፕ አፅኖት በመስጠት አንደገለፀው፤ በራሱ የሚተማመን ህዝብ፣ ብልህነት የተሞላበት ስትራቴጅ፣ ስነ-ስርዓታዊ እና ደፋር እርምጃ በጥምረት ካሉ ከላይ የተጠቀሱት ስልቶች ማንኛውንም ዓይነት አንባገነን ስርዓትን
በቀላሉ ማፈራረስ የሚችሉ ናቸው፡፡
በቀላሉ ማፈራረስ የሚችሉ ናቸው፡፡
ጅን ሻርፕን ጨምሮ ብዙ የፖለቲካ ምሑራን እንደሚስማሙበት ሰላማዊ ትግል ከሌሎች የትጥቅና የአመፃ የትግል ስልቶች በተሻለና አንድን ህዝብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር የሚያስችሉ ናቸው የትግል ስልት ነው ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “ስልጣን ፣ ባህልና አገዛዝ…” በሚለው መፅሐፋቸው “በእኔ አስተሳሰብ የትጥቅ ትግል ለብዙ ዓመታት ስንተላለቅ የኖርንበትና የምናውቀው ነው ፤ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ግን በጭራሽ አዲስ ነው ፤ በትጥቅ ትግል አንዱን ጨቋኝ በሌላው እየለወጥን የአገዛዝን ባህል አጠነከርነው እንጂ ስልጣንን ለመግራት አልቻልንም…” በማለት የኢትዮጵያውያንን ያልተሳካ የትግል ታሪክ በመጥቀስ ሰላማዊ ትግል ለዲሞክራሲ ግንባታ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በሰላማዊ ትግል ውስጥ ዜጎች የስልጣን ምንጭ የመሆናቸውን ታላቅ ሚስጥር ከመረዳት ባሻገር በተግባር ስለሚተገብሩት በቀጣይነት ስልጣን ላይ የሚወጣው አካል አንባገነን የመሆን እድል አይኖረውም ፤ ልሁን ቢል እንኳን ህዝቡ ፍፁም ያን የሚሸከም ትከሻ ስለማይኖረው ውጤቱ ፈጣን ውድቀት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ እንደሚታወቀው ግብፃውያን የጦር መሳሪያ ታጥቀው ግዙፉን አንባገነናዊ የሙባረክ አገዛዝ ለመታገል አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም በመላ ሀገሪቱ የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ሰላማዊ የተቃውሞ ድምፃቸውን እያሰሙ እጅ ለእጅ ተያይዘው አደባባይ መውጣትን ነበር የመረጡት፡፡
ይህንም በማድረጋቸው ግዙፉን አገዛዝ በትንሽ መስዋዕትነት ማስወገድ የቻሉ ሲሆን ፤ በምትኩም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመረጡትን አካል ስልጣን ላይ ማውጣት ችለዋል፡፡ እዚህ ላይ የግብፃውያን ትግል የቅርቡ ጊዜ ክስተት በመሆኑ ለሁሉም ሰው በቀላሉ ሊታወስ ይችላል በሚል እሳቤ እንደምሳሌ ይጠቀስ እንጂ በዓለማችን የበርካታ ሀገራትም ይህን መሰሉ ህዝባዊ ድል ብዙዎችን አስፈንጥዟል፡፡ ይህንን የትግል ስልት በመጠቀም በወቅቱ እንኳን ለማስወገድ ለመነቅነቅ ይከብዳሉ የተባሉ ሃያላን አንባገነኖችን በትንሽ መስዋትነት አንኮታኩተው በማስወገድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ገንብተዋል፡፡ ምሳሌ ከሚሆኑን መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል፡- ህንዳውያን በጋንዲ መሪነት በወቅቱ የነበረውን የእንግሊዝ አንባገነናዊ ቅኝ አገዛዝ ማስወገድ የቻሉ ሲሆን ፤ ፊሊፒንሶችም በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1986 የፈርዲናንድ ማርኮን አገዛዝ አፈራርሰውበታል፡፡
በተመሳሳይም በሰርቢያ ፣ በጆርጅያ እና በዩክሬን ዜጎች ይህን የትግል ስልት በመጠቀም ስኬታማ የሚባል የስርዓት ለውጥ አካሂደዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስለ ሰላማዊ ትግል ሲሰበክ በርካታ አመታት ቢነጉዱም፣ በትግል ስልቱ ታግለው ለማታገል በተነሱት ዘንድ እናኳን የጠራ ግንዛቤ እንደሌለ ለማስተዋል አይከብድም፡፡ 21 ዓመታት ያስቆጠረው የኢህአዴግ ጨቋኝ አገዛዝ በሰላማዊ ትግል ሊወገድ እንደሚችል መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ስለ ሰላማዊ ትግል ምሉዕ ግንዛቤ መያዝ ብቻ ግን አንባገነኑን ስርአት ሊያስወግደው አይችልም፤ በመሆኑም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በቀላሉ ሊዋሀድ የሚችል የሰላማዊ ትግል ዘዴ በጥናት መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡
የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች
ብዙ ጊዜ ስለ ሰላማዊ ትግል ሲነሳ ብዙ ሰዎች ወደ አዕምሯቸዉ ቶሎ የሚመጣላቸው ሰላማዊ ሰልፍ ፣ የስራ ማቆም አድማ እና የመሳሰሉ በጣም ጥቂት በተለምዶ የሚታወቁ የትግሉ ዘዴዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ሰላማዊ ትግል በርካታ የትግል ዘዴዎችን በስሩ አቅፎ የያዘና በጥናት የሚመራ የትግል ስልት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ከ250 በላይ ሰላማዊ የትግል ዘዴዎች በግልፅ ተለይተው ታውቀዋል፡፡ እነዚህ ዘዴዎች ጠቅለል ባለ መልኩ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደቡ ሲሆን ፤እነርሱንም ሰላማዊ ተቃውሞና ማግባባት (Nonviolent protest and persuasion) ፣ ትብብር መንፈግ (Noncooperation) እና ሰላማዊ ጣልቃ መግባት (Nonviolent intervention) በመባል ይታወቃሉ፡፡
ተቃውሞና ማግባባት፡- ይህ የሰላማዊ ትግል ዘዴ 53 ዓይነት ዝርዝር ዘዴዎችን በስሩ ይዟል፡፡ ለምሳሌ፡- የተቃውሞ ጉዞ እና ሰልፍ ማካሄድ፣ የስራ ማቆም አድማ ፣ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ፣ የመማፀኛ ፊርማ ማሰባሰብ ፣ የአንባገነኖችን ኢ-ፍትሀዊ እርምጃ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማውገዝ ፣ የተቃውሞ አርማዎች እና ምልክቶች የታተሙባቸውን ልብሶች መልበስ ፣ የተቃውሞ ተምሳሌታዊ ቁሳቁሶችን ማሳየት ፣ በየሀይማኖቱ ሕዝባዊ የፀሎተ ምህላ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ፣ ወካይ ተምሳሌታዊ የተቃውሞ ድምፆችን ማውጣትና መጠቀም ፣ በተለያየ መልኩ የባለስልጣናትን መጥፎ ተግባር ማጋለጥ ፣ ባለስልጣናትን መንቀፍ፣ ማሽሟጠጥ፣ መዝለፍ፣ በአንባገነኖች የተገደሉ ሰዎችን በማሰብ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ፣ መንግስታዊ ስብሰባዎችን ረግጦ መውጣት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ቶማስ ዌበር “Nonviolence: An Introduction” በሚለው ፅሑፉ እንዳብራራው እነዚህ ዘዴዎች የአገዛዙን ወንጀልና በደል አጉልተው የሚያሳዩ እና ለውጥ መፈለጋችንን ለዓለም ህብረተሰብ መልዕክት የሚያስተላልፉ እንዲሁም አገዛዙ ከወዲሁ የተጠየቀውን እንዲፈፅም የሚያግባቡ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ጅን ሻርፕ ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደገለፀው ዘዴዎቹ ግልፅ የተቃውሞ መልዕክት ማስተላለፋ ከማስቻላቸው ባሻገር ምልዓተ ህዝቡን ያሳተፈ ከባድ ትብርር ነፈጋን ለማካሄድ እንዲሁም ቀጣይ ተቃውሞዎችን ለማድረግ በእጅጉ ይረዳሉ፡፡ ትብብርን መንፈግ፡- ይህ ዘዴ ለአገዛዙ ፣ በአገዛዙ ስር ላሉ ማንኛውም ተቋማት ፣ ለባለስልጣናቱ ፣ ለአፋኝ ህጎቻቸው ፣ ለተግባራቸው… የሚደረግን ማንኛውም አይነት ትብብር የመንፈግ ተግባርንን የሚመለከት ነው፡፡ ይህን ዘዴ ጅን ሻርፕ ማህበራዊ ትብብር መንፈግ ፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ እና የፖለቲካ ትብብር መንፈግ በሚሉ ሶስት ንዑሳን ክፍሎች የከፍሎ ተንትኖታል፡፡ ማህበራዊ ትብብር መንፈግ በሚለው ስር የመንግስት ባለስልጣናትን እና ደጋፊዎቻቸውን ማግለል፣ ማውገዝ፣ ከማህበራዊ ግንኙነት መነጠል፣ ማኩረፍ እና ግላዊ ትብብርን ለባለስልጣናት እና ደጋፊዎቻቸው መንፈግና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ከመንፈግ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም መዋጮዎችን ማቆም ፣የስርአቱ ባለሟሎችና አጋፋሪዎች ንብረት በሆኑ የንግድ ድርጅቶችና ምርቶች ያለመገልገል፣ የገንዘብ ተቀማጭን ከመንግስትና ከመንግስት ደጋፊዎች ባንክ ማውጣት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የፖለቲካ ትብብር ከመንፈግ ጋር በተያያዘ ደግሞ ለወጉ የሚደረጉ ምርጫዎችን መቃወም፣ የመንግስት ተቋማትን መተው ፣ በመንግስት የሚደገፉ የተለያዩ ድርጅቶችን መተው/የንግድ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል/ ያጠቃልላል፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡን ያሳተፈ ትብብር መንፈግ በአንባገነኖች ላይ ትልቅ የሚባል ተፅዕኖ ማድረስ የሚችል የትግል ዘዴ ነው ፡፡
ይህ ዘዴ አንባገነኖች ያላቸውን የኢኮኖሚ ፣ የማህበራዊና የፖለቲካዊ የበላይነት እንዲያጡ በማድረግ ለማንበርከክ ይረዳል፡፡ ጣልቃ መግባት፡- ጅን ሻርፕ “The Politics of Nonviolent Action, Boston, Porter Sergeant” በሚለው መፅሐፉ እንዳብራራው ዘዴው የአገዛዙን ተቋማት ፣ ፖሊሲዎች ፣ አሰራሮች ፣ መርሆች ፣ ግንኙነቶች… ፋይዳ በማሳጣት አንባገነናዊውን አገዛዝ እንዲንኮታኮት የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ዘዴ በስሩ ተከታታይ ሁሉን አቀፍ አድማ (የሰራተኞች ፣ የተማሪዎች ፣ የመምህራን ፣ የነጋዴዎች ፣ የላባደሮች…)፣ ህጋዊነት ለሌላቸው ሕጎች ሙሉ በሙሉ አለመገዛት፣ ህገወጥ ፍርድን አለመቀበል ፣ አማራጭ ተቋማትን ማቋቋም…የሚሉ በርካታ ዝርዝር ዘዴዎችን ይዟል፡፡
የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች አመራረጥ እና አተገባበር
የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን እንደሚናገሩት በማንኛውም መልኩ አንድ ህብረተሰብ ወደ ሰላማዊ ትግል ከመግባቱ በፊት በአካል በመገናኘት ወይም ደግሞ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ምን አይነት የትግል ዘዴዎችን እንዴት መጠቀም እንዳለበት በሰፊው በመወያየት፣ ወጥ አቋም መያዝ እና ጥሩ እቅድ ማቀድ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ይህን ውይይት በማስተባበር እና በመምራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና/ወይም የሲቪክ ማህበራት እና ልዩ ልዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የአንበሳውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡
የሰላማዊ ትግል ዘዴዎች የአንባገነኖችን ድክመት ከግምት ውስጥ በማስገባት እና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ባገናዘ በመልኩ ሲተገበሩ ይበልጥ በተሳካ መልኩ አንባገነኖችን በፍጥነት ማስወገድ ያስችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ክርስቶፐር ኤ.ሚለር “STRATEGIC NONVIOLENT STRUGGLE”
በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የስልጠና መመሪያ ላይ ይህን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ በመደገፍ አፅኖት ሰጥቶ ፅፏል፡፡
እዚህ ላይ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ባገናዘበ መልኩ ሲል ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ግልፅ ለማድረግ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር መገለጫ የሚሆን አንድ ምሳሌ በማንሳት መመልከት እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው በሀገራችን ኢትዮጵያ በቀላሉ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞን ማሰማት ወይም የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ እዚህ ላይ በ97 የታየው ዘግናኝ የመንግስት የሐይል እርምጃ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
እንዲህ አይነት ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ባለበት ሀገር የትግል ዘዴዎችን እንዲሁ በጅምላ ሳይሆን ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ መምረጥ እንዲሁም አጠቃላይ ትግሉን ስልታዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ አንባገነኖች የሚወስዱት የአፀፋ እርምጃ ብዙ መስዋትነት ሊያስከፍለን ይችላል፡፡ ክርስቶፐር ኤ.ሚለር እንደሚጠቁመው እንዲህ አይነት ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ባለበት ሁኔታ እንደ ፀሎተምህላ፣ ባንዲራን እና ወካይነት ያላቸው የተቃውሞ ምልክቶችን ማሳየት ፣ የስራ ማቆም አድማ….. ያሉ ብዙም ለአደጋ የማያጋልጡ ዘዴዎችን መርጦ በእነርሱ ተቃውሞን መጀመር ብልህነት ነው፡፡
በመቀጠልም ማንኛውንም ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትብብሮችን ሙሉ በሙሉ በመንፈግ ስርዓቱ በሂደት ሲዳከም ጠንከር ወዳሉት ሰላማዊ ሰልፍ እና የመሳሰሉ የትግል ዘዴዎች መግባት ይቻላል፡፡ እንደ ክርስቶፐር ኤ.ሚለር ማብራሪያ ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ህዝብን በአንድ ላይ የሚያሰባስቡ የተለመዱ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን በመጠቀም ተቃውሞን በአደባባይ መጀመር ይቻላል፡፡ ከላይ ካነሳነው ሀሳብ ጋር በተያያዘ ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድ ስርዓትን ሲታገሉ የተቃውሞ ድምፃቸውን በአደባባይ ለማሰማት የተጠቀሙበትን ዘዴ እንደ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የነበረው መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድን በጥብቅ ከልክሎ ነበር፡፡ ስለሆነም ደቡብ አፍሪካውያን የተቃውሞ ድምፃቸውን በአደባባይ ለማሰማት ከሰላማዊ ሰልፍ የተለየ ሌላ ዘዴ መፈለግ ነበረባቸው፡፡ በመጨረሻ ጥሩ “ ዘዴ አገኙ፡፡ ዘዴውም የቀብር ስነስርዓት ለመፈፀም በሚሰባሰቡበት ጊዜ ተቃውሞን ማሰማት ነበር፡፡
ከዚያም ደቡብ አፍሪካውያን የወዳጃቸውን አስከሬን በክብር ተሸክመው በትልልቅ ጎዳናዎች ላይ እየተንጎራደዱየተቃውሞ ድምፃቻን ማሰማት ጀመሩ ፤መንግስትም አትቅበሩ ብሎ መከልከል ስለማይቻል ዝም ብሎ ለመመልከት ተገደደ፡፡ በተመሳሳይ ብዙም ሳንርቅ እዚሁ በሀገራችን የመንግስትን በሐይማኖት ጣልቃ መግባት የተቃወሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ድምፃቸውን በአደባባይ ለማሰማት እየተጠቀሙት ያለው ዘዴ ሌላው በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ሙስሊሞች ፍፁም ሰላማዊ ሆነው በእጅ ምልክት፣አፍን በመሸፈን፣ ታላቅ የተቃውሞ ድምፅ በማሰማት እንዲሁም የተለያ የትርጉም ያላቸውን ቀለሞች በማሳየት ከአምልኮ ስፍራቸው ብዙም ሳይርቁ (በርግጥ ሐይማኖታዊ በአሎቻቸውን ሲያከብሩ በከተማዋ ዋና ዋና ክፍሎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል) ያሳዩት ተቃውሞ ብዙ ትምህርት ሊቀሰምበት የሚገባ ነው፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ቃሊቲ የታሰሩ መሪዎቻቸውን በነቂስ ወጥተው በመጠየቅ መንግስትን የሚቃወሙበት መንገድ የተቃውሞ ሂደታቸውን በሳልነትና እያደገና እየሰፋ መምጣት፣ በተጨማሪም ከአምልኮ ስፍራዎች ባሻገር መተግበር መጀመሩን የሚያመላክት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ የትግል ዘዴ በጠባብ የፖለቲካ ምህዳርን መሰረት በማድረግ የትግል ዘዴዎችን በስልት በመምረጥ እራስን ከአንባገነኖች ጨካኝ የአፀፋ እርምጃ መከላከል እንደሚቻል እና እንዴት የተለመዱ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ ስነስርዓቶችን በመጠቀም ጠንካራ ተቃውሞ በአደባባይ ማሰማት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ጅን ሻርፕ እንደሚያስረዳው የሀገርን የፖለቲካ ምህዳር መሰረት ባደረገ መልኩ የትግል ዘዴዎችን መምረጥ እና የትግል ስልትን መንደፍ ብቸኛ ከአምባገነኖች የሚሰነዘርን ዘግናኝ የአፀፋ እርምጃ መከላከያ ስልት አይደለም፡፡
ከዚህም ባሻገር ለፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት አባላት በግልፅ የትግሉን አላማ በማስረዳት፣ ለትግሉ ቀና እይታ እንዲኖራቸውና ሰላማዊነቱን እንዲረዱ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ በመስራት የአንባገነኖችን እርምጃ በጉልህ መቀነስ ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ለነፃነት እና ለዲሞክራሲ በሚደረግ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ከአንባገነኖች የሚሰነዘርን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የሚቻል አለመሆኑን ነው፡፡ አንባገነኖች የትግሉን እንቅስቃሴ ለማፈን ሲሉ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ ላይሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖምግን እንደ ጅን ሻርፕ ማብራሪያ መሰልእርምጃዎች አንባገነኖች በአለም አቀፍ ደረጃፍፁም እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል ፣ ትልቅ የዲፕሎማሲ ክስረት ይፈጥርባቸዋል፣ በሚታገለው ህብረተሰቡ ውስጥም እልህን እየፈጠረ ትግሉን የበለጠ ያቀጣጥለዋል፡፡
እነዚህ ያልታሰቡ ውጤቶችም የኋላ ኋላ በእኩይ እርምጃቸው እንዳይቀጥሉበት ያደርጋቸዋል፡፡ጅን ሻርፕ እንደሚመክረው የህብረተሰቡ ቆራጥነት እና ስነ-ስርዓት የታከለባቸው ተቃውሞዎች እየተጋጋሉ በሚሄዱበት ወቅት በተመሳሳይ ሁሉን አቀፍ ትብብር የመንፈግ እርምጃዎች እየጨመሩ እና እየተጠናከሩ መሄድ አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን የአንባገነናዊው አገዛዝ ውስጣዊ ድክመቶች እየጎሉ እና አገዛዙ እየተሽመደመደ ይሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት ግን ሊሰሩ የሚገባቸዉ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነርሱም ነፃ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማትን ማቋቋም እና ያሉትንም ማጠናከርን የሚጨምሩ ናቸው፡፡ እንደ ምሁሩ ማብራሪያ የእነዚህ ተቋማት ማቆጥቆጥ ለትግሉ አለም አቀፋዊ ተቀባይነትን የሚያስገኝለት ሲሆን ፤ በተጓዳኝ አንባገነናዊው አገዛዝ የሚደርስበት አለም አቀፋዊ ውግዘት እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡
በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሉ ቁልፍ ነገሮች
በሰላማዊ ትግል ላይ ጥናት ያደረጉ ምሑራን አፅኖት ሰጥተው እንደሚናገሩት አንድ ሰላማዊ ትግል የታቀደለትን ግብ ይመታ ዘንድ ብልህና ቆራጥ አመራር የሚያስፈልግ ቢሆንም በዋናነት በራሱ የሚተማመን ህዝብ ፣ ብልህነት የተሞላበት የትግል ስትራቴጂ እና ደፋር እርምጃ በጥምረት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እነዚህ ሦስት መሰረታዊ ነገሮች በጥምረት ባሉበት ሁኔታ ማንኛውም ሰላማዊ ትግልመጨረሻው ደማቅ ድል ነው፡፡
አንባገነኖች ወደዱም ጠሉም አይናቸው እያየ የገነቡት እኩይ ስርዓታቸው መፈራረሱ እና እነርሱም በህዝብ እጅ ላይ መውደቃቸው የማያጠያይቅ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ሆኖም እነዚህ የተጠቀሱት ሦስት ነገሮች እንዳሉ ሆኖ ከእነርሱ ባሻገር ሌላ ተጨማሪ ለሰላማዊ ትግል ስኬታማነት ቁልፍ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ እና በማንኛውም ሰላማዊ ትግል ውስጥ ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች አሉ፡፡
ከእነዚህ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ቁልፍ ከሚባሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ አንድነት ነው፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው ሁሉ በሰላማዊ ትግል ወቅት የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል በአንድነት መቆም አንባገነኖችን በፍጥነት ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ እንዲንኮታኮቱ ያደርጋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዶ/ር ሲንቲያ ቦአዝ “Nonviolent Revolution Clarified: Five Myths and Realities Behind Egypt’s Uprising” በሚለዉ ፅሑፋቸው እንዳስነበቡት ከግብፃዊያን የሰላማዊ ትግል የስኬት ሚስጥሮች መካከል አንድነት አንዱ እና ዋናው ነበር፡፡ ይህንን ቁልፍ የሰላማዊ ትግል ቁልፍ ነጥብ ከኢትዮጵያነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘን እንመልከት፡፡
ኢህአዴግ የኢትዮጵያውያን አንድነት የስልጣን እድሜውን እንደሚያሳጥረው አስቀድሞ በመረዳቱ ህዝቡን በክልል፣በብሄር፣በሐይማኖት እና በተለያዩ መደቦች በመከፋፈል የልዩነትና የጥላቻ ዘርን ዘርቷል፡፡ በተለያዩ ወቅቶችም የተደራጁ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለማክሰም ከሚጠቀምበት የሃይል እርምጃ ጎን ለጎን አንዱን በአንዱ ላይ በጠላትነት በማስነሳት አንድነትን በማጥፋት የስልጣን እድሜውን ሲያራዝም ቆይቷል፡፡ ስለዚህም ኢህአዴግን ለመጣል የሚደረግ ትግል በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የአንድት መንፈስን ማኖርና ልዩነቶችን ማቻቻል አስፈላጊ ነው፡፡ ከአንድነት ቀጥሎ ለአንድ የሰላማዊ ትግሉ መሳካት ቁልፍ ተደርጎ የሚጠቀሰው ስነ-ስርዓት Discipline) ነው፡፡ ብዙ ምሑራን አንድ ሰላማዊት ትግል የአንባገነኖች ትንኮሳ ቢፈታተነውም እንኳን ሰላማዊ ስነ-ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ መካሄድ ይገባዋል በማለት ያሳስባሉ፡፡
እንደ እነርሱ ማብራሪያ አንድ ትግል ፍፁም ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከተካሄድ አንባገነኖች በሐይል ጣልቃ ለመግባት ይቸገራሉ፡፡ ይህም የሚከፈለውን የህይወት መስዋዕትነት በከፍተኛ ደረጃ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሰላማዊው ተቃውሞ ወደ ሐይል አመፅ ከተለወጠ ግን ለአንባገነኖች የሀይል በትራቸውን እንዲያነሱ በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ከስነስርአት ጋር በተያያዘ አንድ ኢትዮጵያውያን ታጋዮችን የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ የጋመውን የሙስሊም ምዕመናን ተቃውሞ ወደ ግጭት እንዲለወጥ መንግስት የተለያዩ ያልተሳኩ ጥረቶችን አድርጓል፡፡
ከዚህ ጥረት ውስጥ የሚጠቀሰው ምዕመናኑ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙበት ወቅት የከተማ አውቶብሶችን ከፊታቸው በመደርደር ለጥቃት ማመቻቸቱ ነው፤ምዕመናኑ ግን ይህን ተንኮል አስቀድመው በመረዳታቸው “አንሰብርም...አንሰብርም” በማለት ስነስርአታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት አስርጎ ያስገባቸውን በጥባጮች በመገሰፅ፣በማጋለጥና በካሜራ በማንሳት ፍፁም ስነስርአት የተላበሰ ሰላማዊ ትግል በማድረግ ላጥ ናቸው፡፡
ዲሲፕሊን ከዚህ ባሻገር ጥቅም እንዳለው ጅን ሻርፕ እንዲህ ሲል ይገልፃል፡- “Nonviolent discipline is extremely important… the stark brutality of the regime against the clearly nonviolent actionists politically rebounds against the dictators’ position, causing dissention in their own ranks as well as fomenting support for the resisters among the general population, the regime’s usual supporters, and third parties.” ይህን ቃል በቃል ስንተረጉመው እንዲህ ይላል፤ “የሰላማዊ ትግል ዲስፕሊን እጅግ ጠቃሚ ነው… አንባገነኑ አገዛዝ ፍፁም ሰላማዊ በሆኑ ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደው የሀይል እርምጃ በራሱ የስልጣን ተዋረድ ውስጥ አለመግባባት በመፍጠር በራሱ ላይ ችግር ከማስከተሉ ባሻገር ለተቃዋሚዎች ከብዙኃኑ ህዝብ ፣ ከራሱ ከአገዛዙ ደጋፊዎች እና ከሌላ ሦስተኛ ወገን የፖለቲካ ድጋፍ
ያስገኛል፡፡”
ያስገኛል፡፡”
Source: Finote Netsanet
No comments:
Post a Comment