Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, October 24, 2012

የእስክንድር ነጋ ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ለክርክር ተቀጠረ

Eskendir Nega
ከሰሰበት የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውሳኔውን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ለክርክር ለጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጠረ፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ያስተላለፈበትን የጥፋተኝነት ፍርድና የቅጣት ውሳኔ በመቃወም ‹‹ንፁህ ነኝ፣ የቀረበብኝ ማስረጃ የለም፡፡ ፍርድ ቤቶች የተከበሩ ተቋማት በመሆናቸውና የበቀል፣ የአፈናና የጭቆና መድረክ መሆን ስለሌለባቸው በነፃ ልለቀቅ፤›› በማለት ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ይግባኝ ማለቱን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው አቤቱታ ያስረዳል፡፡ 


ጋዜጠኛ እስክንድር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፣ ከግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች ጋር በህቡዕ ግንኙነት በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ስብሰባ በማድረግ፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በመስማማት፣ የግንቦት 7 ልሳን ለሆነው ኢሳት መረጃ በመስጠት፣ ቀስቃሽ ጽሑፎችን በመጻፍና በማሠራጨት ወንጀል የመጀመሪያው ክስ ተመሥርቶበታል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(2)ን በመተላለፍ ደግሞ የግንቦት 7 አገር ውስጥ ወኪል በመሆን ወንጀል ሁለተኛ ክስ ሲመሠረትበት፣ የወንጀል ሕግ 32 (1/ሀ) እና 248(ለ)ን በመተላለፍ ደግሞ የኤርትራ መንግሥት የሽብር አጀንዳ ለማስፈጸም እንዲመቸውና እንዲቀናጅ በመርዳት ከፍ ባለ የክህደት ወንጀል ሦስተኛ ክስ ተመሥርቶበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሦስት ክሶች መሥርቶበት አንድ የሰው ማስረጃ፣ የኦዲዮና የቪዲዮ ማስረጃዎችን ያቀረበ ቢሆንም፣ አንዳቸውም እንደ ክሱ እንዳላስረዱና እንዳልተመሰከረበት አብራርቷል፡፡ ዕውቀትና ልምድ በቅጡ ያልዳበረበት የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ 652/2001 (23) በተሳሳተ መንገድ እንደተተረጐመ፣ የላባ ያህል ክብደት ያለው ማስረጃ ሳይቀርብበት ጥፋተኛ ለማሰኘት ዓቃቤ ሕግ የተጠቀመበት አግባብ አለመሆኑን እስክንድር በአቤቱታው አስረድቷል፡፡ 

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ባስተላለፈበት ባለ 68 ገጽ የቅጣት ውሳኔ ውስጥ ተፈጽመዋል ያላቸውን ስህተቶች በ11 ርዕሶች ከፋፍሎ በዝርዝር ያቀረበው ጋዜጠኛው፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ቀርበው የነበሩት የመኢዴፓ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ‹‹የፋይናንስ ችግር ካለ ከአንተ 20 ሺሕ ብር፣ ከእሱም 20 ሺሕ ብር፣ ከእኔም 20 ሺሕ ብር እረዳችኋለሁ ብሎኛል፤ ከአቶ ፋሲል የኔዓለም ጋርም በስልክ እንደሚገናኙና በፋይናንስ እንደሚረዳው ነግሮኛል፤›› ብለው መስክረዋል በሚል በውሳኔው ላይ የሰፈረው ዓረፍተ ነገር ሐሰት መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲያይለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረፀው የኦዲዮ ማስረጃ እንዲሰማለትና እሱም ያቀረበው መስቀለኛ ጥያቄ እንዲደመጥለት በማመልከቻው ጠይቋል፡፡ 

በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰነድ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃልና ምስክሮቹ በችሎት የተናገሩት ቃል ያለቦታው እየገባ ፍርድ ቤቱ ለውሳኔ በሚያመቸው ሁኔታ እንደተጠቀመበት፣ ገጹንና የሰፈረውን ቃል ጭምር በመጥቀስ ዝርዝር የይግባኝ አቤቱታ ያቀረበው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ ፍርድ ቤቱ በአፅንኦት እንዲመለከትለት ጠይቋል፡፡ 

መኢዴፓ መስከረም 21 ቀን 2004 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሊያደርግ በነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ዙሪያና በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ከተደረገ ስብሰባ ጋር በተያያዘ ለቀረበበት ክስ፣ በመከላከያ ምስክሮቹና በቪዲዮ ያቀረበው ማስረጃ ከግምት ውስጥ እንዳልገባለት የጠቀሰው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ መኢዴፓ ሰላማዊ ሠልፉን እንዳያደርግ፣ ውጭ አገር ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ገንዘብ እንዳይቀበሉና ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ መምከሩን በአስረጂነት ጠቅሷል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔም መሠረታዊ የሆነ ስህተት ስላለበት ኦዲዮውን ፍርድ ቤቱ እንዲያደምጥለት ደጋግሞ ጠይቋል፡፡ በአንድነት ቢሮ ያደረገውን ንግግርና የመራውን መድረክ በሚመለከት ቪዲዮውን መመልከት በቂ ምላሽ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር በአቤቱታው ላይ አንድነት ቢሮ ተገኝቶ የገለጸው በመሠረታዊ ባህሪያቸው ተፈጥሮአዊ ሆነው በሕገ መንግሥቱም ዕውቅና የተሰጣቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ መሆኑን፣ በአፍሪካ አገሮች እየተከበሩ በኢትዮጵያ አለመከበራቸው ታላቅ አገራዊ ውርደት መሆኑን፣ ለመብቶች አለመከበር ምክንያት የሆኑት ጥቂት የኢሕአዴግ አመራር አባላት በተለይ በኪራይ ሰብሳቢነት የተሰማሩት እንጂ ብዙኅኑ የኢሕአዴግ አባላት አለመሆናቸውን፣ የመሳሰሉት መሆናቸውን በማመልከቻው ጠቅሶ ‹‹ታዲያ ይኼ ምኑ ነው የሚያስከስሰው?›› በማለት ጠይቋል፡፡ 

በአጠቃላይ የሥር ፍርድ ቤት ያስተላለፈበት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ተጨባጭ የሆኑ ማስረጃዎች ሳይቀርቡበት፣ በማመሳሰልና የቃላቶችን አገባብ በማዘበራረቅ መሆኑን በመጥቀስ፣ ፍርድ ቤቱ ንፅህናውን በማየትና የቀረበበት ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመኖሩን በማረጋገጥ፣ በነፃ እንዲያሰናብተው ባቀረበው ባለ አሥር ገጽ የይግባኝ አቤቱታ ላይ ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ክርክር እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር በሥር ፍርድ ቤት ክርክሩን ያደርግ የነበረው በጠበቃ ታግዞ የነበረ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚኖረው ክርክር ላይ ግን ያለጠበቃ ራሱ እንደሚከራከር ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር በይግባኙ ላይ ክርክር ለማድረግ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. 43ኛ ዓመት የልደት በዓሉንም ያከብራል፡፡

ለአሥራ ስምንት ዓመታት ፅኑ እስራት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ለአምስት ዓመታት ከሕዝባዊ መብቶቹ ከመሻራቸውም በላይ፣ የእሱ፣ ዕድሜ ልክ የተፈረደበት አንዱዓለም አራጌና በሌለበት 15 ዓመታት የተፈረደበት አበበ በለው ንብረቶች እንዳይሸጡ፣ እንዳይለወጡና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ በፍርድ ቤት መታገዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡.

No comments:

Post a Comment