Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, October 24, 2012

ሐሙስን ከሚኒስትሩ ጋር!

 ዕለቱ ሐሙስ ነው፡፡ ቀኑ ደግሞ ‘08’፡፡ ወርሃ ጥቅምት፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢህአዴግ ግንባር ቀደሞች ተሰብስበናል፡፡ በታሪካዊው የ”FBE” አዳራሽ፡፡ ታሪካዊ ማለቴ ቆራጡ መንጌ የፖለቲከ ርዮት ያጠጣበት የነበረ አዳራሽ በመሆኑ ነው፡፡ ካለመናችሁ ወንበሮቹን እዩአቸው፡፡ መደገፊያዎቹ ላይ “ፖ/ት ይላሉ፡፡ ፖለቲካ ት/ቤት እንደማለት፡፡
በቀኝ እጃቸው ሴቷ ማጭድ ወንዱ መዶሻ ይዘው ግራ እጃቸውን “የሁሉም ሐገር ሠራተኞች ተባበሩ!” የሚል መፈከር ያነገቡ የሚመስል ቅርፅም መግቢያው ላይ አለ፡፡ እናስ ታሪካዊ አይደለም ትላላችሁ?! እኛም ግንባር ቀደሞቹ በዚህ ታሪካዊ አዳራሽ ታሪካዊ ስብሰባ እያደረግን ነው፡፡ ሰብሳቢዎቻችን ደግሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም እና የ ዩኒቨርስቲያችን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ናቸው፡፡
ከጠዋቱ 3፡00 ከአራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የተውጣጣን ግንባር ቀደሞች አዳራሹን ሞላነው፡፡ የመሰረታዊ አደረጃጀት አመራሮች በር ላይ ሆነው ግንባር ቀደም ያልሆነውን ግንባሩን አዙሮ እንዲሄድ ለማድረግ በጥንቃቄ እየለቀሙ ያስገባሉ፡፡ አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ፡፡ ስብሰባው ለታላቁ መሪያችን ጸሎት በማድረግ ተጀመረ፡፡ ክቡር ሚንስትሩ አጀንዳውን አስተዋወቁ፡፡ 
ስለ ‘አክራሪነት’ ነው፡፡ አቶ አምባዬ የተባሉ ሰው (ይቅርታ ማዕረጋቸው ስላልተነገረን) ያዘጋጁትን ጽሑፍ “በፕሮጀክተር” ዘረገፉት፡፡ የቀረ የለም፡፡ ሁለም በአክራሪነት ተፈርጇል፡፡ አንዳንድ ዋሃቢያዎች… አንዳንድ ሰለፊዎች… አንዳንድ ካዋርጃዎች… አንዳንድ ማኅበረ ቅዱሳኖች… አንዳንድ…፡፡ አክራሪዎች ናቸው ተባለ፡፡ ከንጉሡ ጀምሮ እስከ አምባ ገነኑ ደርግ ድረስ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት እንዳልነበር አስተጋቡ ፤ የዛሬውንም መንግሥት ቸርነት ሰበኩ፡፡
አቶ አምባዬ ረጅሙን ትንተናቸውን ሲጨርሱ ክቡር ሚንስተሩ ተተኩ፡፡ ትንሽ ላጠናክረው ብለው አንዳንድ ነገሮችን አንስተው በአንዳንዶች ላይ ዙሩን አከረሩት፡፡ እኝህ ክቡር ሚኒስትር ንግግራቸው ጠንካራ ነው ፤ ልክ እንደ ጓዳችን፡፡ ትንሽ የሚለዩት በአማርኛቸው ነው፡፡ ያዝ! ያደርጋቸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 90/2/ን ተነተኑት፡፡ “ትምህርት ከፖለቲካ ፤ ከሃይማኖት እና ባህላዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት” ይላል አሉ፡፡ 
በእርግጥ እሳቸው ከ‘ሃይማኖት’ የሚለው ላይ ነው ጠበቅ ያሉት፡፡ ይሄኔ ከጎኔ የተቀመጠው ግንባር ቀደም ጓደኛዬ “what about this” አለኝ፡፡ በዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ፖለቲካ እየሰበኩ እንዴት ነው አንቀጹ የሚነሳው ማለቱ ነው፡፡ የአይኖቼን ቅንድቦች ብቻ ከፍና ዝቅ በማድረግ “እኔም አልገባኝ!” አልኩት፡፡ ክቡር ምኒስትሩ ማጠናከሪያቸውን እስኪበቃው ድረስ እንደ ብረት ካጠነከሩት በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆነ፡፡
የመጀመሪያው ተናጋሪ ‘ማይኩን’ ተቀበለ፡፡ ወደፊት አካባቢ ስለነበር አካላዊ ገፅታው አይታየኝም፡፡ ድምፁ ግን ወፍራም ነው፡፡ “በእውነቱ ዛሬ የተወያየንበት ነገር በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እህ! (ድምፁ ይበልጥ እየወፈረ መጣ) ሥራ አጥነት አገብጋቢ ሆኖብን ፣ ተምረን መውደቂያ እያጣን እናንተ አክራሪነት ትላላችሁ!” ከባድ ጭብጨባ፡፡
ክቡር ሚንስትሩ ገላመጡን፡፡ “ስሙ! ይሄ ጭብጨባ እኮ የደርግ መገለጫ እንጂ የግንባር ቀደሞች አይደለም፡፡ ደርግ ነው በባዶ አዳራሽ የሚያስጨበጭብ፡፡” ሌላም ተግሳፅ አወረዱብንና ለሌላኛው እድል ሰጡ፡፡ ሁለተኛው ተናጋሪ ስሙንና ድርጅቱን ተናግሮ ቀጠለ “እኔም የምለው ነገር ስለ ሥራ ነው፡፡ ሥራ ስጡነ ስንል ‘ኮብልስቶን’ ስሩ ትሉናላችሁ፡፡ 
የተማረውም ያልተማረውም ‘ኮብልስቶን’ ከሰራ ልዩነቱ ምንድነው?” ደማቅ ጭብጨባ ፤ በጭብጨባው ታግዞ ንግግሩን አረዘመ፡፡ “እናንተ መብታችሁ ተከብሮ ትላላችሁ የትኛው መብታችን ነው የተከበረው? በቀደም ለታ እሁድ ቀን ኳስ ልናይ ከተሰለፍንበት ፌደራል ቀጠቀጠን፡፡ ስንቱን ሽባ አደረገው፡፡ ደሞ… ምን መብት አለነ፡፡” ሌላ ጭብጨባ… “ደሞ ሚዲያዎቻችን ውሸት ብቻ ነው ሥራቸው፡፡ ትናንት በቴሌቭዥን 40 ኩንታል ጤፍ በጭልጋ ተመረተ ሲል ነበር፡፡
 እኔ ራሴ የጭልጋ ልጅ ነኝ፡፡ እንኳን 40 ኩንታል አንድ ገበሬ ሊያመርት 4 ኩንታልም የለ፡፡ ይህ ለምን ነው እሚዋሽ? እንዴ! ነውር አይደለም?” አዳራሹ በሁካታ ተሞላ፡፡ የ‘ህዋስ’ አመራሮች ዐይናቸውን ማፍጠጥ ጀመሩ፡፡ የአንዳንዶቹ ጉንጭ የበሰለ ቲማቲም ይመስል ጀምሯል፡፡ ክቡር ሚንስትሩ ድምፅ ማጉያውን አበሩ፡፡ “ጎበዝ! ይሄ እኮ የግንባር ቀደሞች ስብሰባ መስሎኝ ነበር (ትንሽ ፋታ ወስደው)… እና እንግባባ፡፡ አታጨብጭቡ ማለት አታጨብጭቡ ነው፡፡ በቃ!... እንስማማ እንጂ…”

No comments:

Post a Comment