በብዙአየሁ ወንድሙ, Finote netsanet
በፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት 14 ዓመት ጽኑ እስራትና 33ሺ ብር ተፈርዶባት በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቅጣቱ ወደ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተቀይሮ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የምትገኘው ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” የሚል መጽሐፍ ባለፈው ቅዳሜ አስመርቃለች፡፡
በምረቃው ዕለት ርዕዮት ባትገኝም ወላጆቿ፣ ወንድሞቿ፣ እህቶቿ፣ ጓደኞቿ፣ የሞያ አጋሮቿ፣ አድናቂዎቿና ዘመድ አዝማዶቿ በተገኙበት ባለፈው ቅዳሜ በራስ አምባ ሆቴል በደማቅ ሥነ ሥርዓት የመጽሐፍ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ርዕዮት ዓለሙ “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶን” ለመፃፍ ምን አነሳሳት? የመጽሐፉ ይዘትስ ምን ይሆን? ለእስር የበቃችበትን ምክንያት እንዲህ ብላ ነው የገለፀችው፡- “ገዢው ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጉዳይን የወረቀት ጌጥ ሲያደርገውና ያለ ፍትሀዊ ውድድር ራሱን በ ‹አውራፓርቲ› ነት ሾሞ ስመለከት አዘንኩ፤ ከዚያም ፃፍኩ፡፡
የፕሬስ ነፃነትን እነማን የማይነካውን እንደሚነኩ ማወቂያና እነዚህ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር
የራቀ አመለካከት ያላቸውን የዜጎች ማጥቂ ታክቲክ እንዳደረገው ስረዳ ተበሳጨሁ፤ ከዚያም ጻፍኩ፡፡ የህብረተሰቡ እኩሌታ የሆኑ ሴቶች ከሚያዘጋጃቸው ሰልፎች ማድመቂያነት ባለፈ ዋጋ እንደማይሰጣቸው ሲገባኝ ተቆጨሁ፤ ከዚያም ፃፍኩ፡፡
የሥራ ማግኛ መስፈርትን ከትምህርት ደረጃ፣ ከብቃትና ከስራ ልምድ ዝቅ አድርጎ የኢህአዴግ አባልነት መታወቂያ ማድረጉን ስታዘብ ተናደደኩ፤ ከዚያም ፃፍኩ፡፡ እንዲህ አይነቱን አምባገነንነት ሀይ ማለት የሚኖርባቸው ሲቪል ማህበራትን ሽባ ሲያደርጋቸውና በሰበብ አስባቡ ምክንያት እየፈለገ ሲኮረኩማቸው ሳይ ‹ለምን?› ብዬ ተብከነከንኩ፤ ከዚያም ፃፍኩ፡፡ ግፈኞችን ማውገዝ የሚጠበቅባቸው የሀይማኖት አባቶች ሁኔታ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲሆንብኝና የአምላክ አገልጋይነታቸውን ርግፍ አርገው ትተው ለቄሳር መገበራቸውን ሲገባኝ ተገረምኩ፤ ከዚያም ፃፍኩ፡፡ በዚህ አይነት ጉዞዬ ‹ከልማታዊነት› ጎዳና በእጅጉ የራቁ ጽሁፎች ማዘጋጀቴን በሰፊው ተያያዝኩት፡፡ ጽሁፎቹም በቼንጅ መጽሄት፣ በአዲስ ፕሬስ፣ በአውራአምባ ታይምስ በመጨረሻም በፍትህ ጋዜጣ ላይ ተስተናገዱ፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ልፋቴ በማንም ላይ ክፉ ከማሰብ የመነጨ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከሆነለት ራሱን አርሞ ሀገሬን በቅጡ እንዲመራ ካልሆነለት ደግሞ ስልጣኑን ለሕዝብ እንዲያስረክብ በማሳሰብ የሚጠበቅብኝን ሀገራዊና ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ስል በፈፀምኩት ውለታ የማይረሳው መንግስታችን ለዚህ መልካም ተግባሬ ‹የሽብርተኝነት› ማዕረግ አቀዳጀኝ፡፡ የቃሊቲን የክብር ስፍራም አልነፈገኝም፡፡ ‹ደክሞሃል እረፍ› እያልኩ ስጽፍ የነበረው በቅንነት መሆኑን ተረድቶ እሱም በተራው በቅንነት የ14 ዓመታት እረፍት አዞልኛል፡፡ ታዲያ ልማታዊ መንግስታችን እንደዚህ አጥብቆ ምስጋናውን በተግባር እንዲገልጽልኝ ምክኒያት ከሆኑ ጽሁፎቼ መሀከል የተወሰኑትን ብጋብዛችሁ ምን ይላችኋል?” ስትል ርዕዮት “የኢህአዴግን ቀይ እስክሪብቶ” መጽሐፏን ጀባ ብላናለች፡፡
የርዕዮት ትንታግ ብዕር ዛሬም እውነትን ይናገራል፡፡ በአሳሪዎች እጅ ወድቄአለሁ ብላ ህሊናዋን አላሰረችም፡፡ የዓለም አቀፉ የሴት ጋዜጠኞች ፋውንዴሽን 2012 ተሸላሚዋ ርዕዮት ዓለሙ ዛሬም እውነትን ትመሰክራለች፡፡ ብዕሯ የሚጐረብጣቸው “ሽብርተኛ” ብለው ቢፈርጇትም እሷ ግን ፈርጀዋታል፡፡ አሁንም እውነት ከመፃፍ ወደኋላ አላለችም፡፡ የአገራችንን እውነተኛውን ገጽታ ባለው መልኩ መቀበል የቻሉት ግን አድንቀዋታል፡፡
የአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የሆነው የህገመንግስት አንቀጽ በተግባር ተሽሮ ኃላፊነትን ሊወጣ ባልቻለ ምርጫ ቦርድ ኢህአዴግ የሐሰት ምርጫ እያደረገ “አሸነፍኩ” እያለ በመራጩ ህዝብ ላይ ሲያላግጥ “ራሱን አውራ ፓርቲ ነኝ” እያለ በህዝብ ሲቀልድ እውነተኛ ብዕር ያስፈልግ ነበረና ፃፈች፡፡ ርዕዮት እንደምትነግረን በዚህ የተናደዱት አሳሪዎቿ ጉድጓድ ሲቆፍሩላት ቆዩ፤የሴቶች መብትና እኩልነት ለመድረክና ጐዳና ማድመቂያ መዋሉን፤ እንዲያውም የሥርዓቱ ዋና ዋና ተዋናይ የሆኑ፤ “17 ዓመት ታግለን የገባን ነን” የሚሉ፤ሳይቀሩ ሥልጣንና ገንዘብ ሲያገኙ አብረዋቸው ታግለው የገቡ ሚስቶቻቸውን እየፈቱ “የእኔ ቆንጆ” እያሉ በሚያቆለምጧቸው ዘመናዊ ሴቶች ሲቀየሯቸው “ለምን?” በማለት ተቸቻቸው፡፡ አኮረፉና ወጥመድ አዘጋጁላት፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ ነፃነት ከቀን ወደ ቀን እየተዳፈነ አይን ያወጣ የአፈና ሥርዓት ሲዘረጋ ርዕዮት ፃፈች፡፡ ርዕዮትን ከፕሬስ መነጠል ፈለጉና አሴሩባት፡፡ ክቡርና ታላቅ የሆነው የዜግነት ክብር ተዋርዶና ተሽሮ ሥራ ማግኛ የኢህአዴግ ተራ የአባልነት ደብተር ሲሆን እንደሌላው ዝም ብላ ከመቀበል “ልክ አይደለም” ካለች በኋላ ሥራ በዜግነት በሥራና በሞያ በእውቀት ውድድር ተደርጐ መሆን አለበት ብላ ፃፈች፡፡ ይህን ማለት ወንጀል ሆነና ዶለቱባት፤የሃይማኖት አባቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ታላቅ ክብር አውርደው ለሥርዓቱ አጐብዳጅና ተላላኪ ሲሆኑ የቴሌቪዥን ማድመቂያና የማይመጥናቸው ሥራ ሲሠሩ በማየቷ ርዕዮት ፃፈችባቸው፤ድሮውንም ከመስመሩ የወጡ ነበሩና “እንዴት በህፃናት እንሰደባለን? እንዴት በልጅ ስንሰደብ መንግስት ዝም ብሎ ይመለከታል” ብለው ባለሥልጣናት ዘንድ ሄደው አለቀሱ፡፡ “አይዟችሁ ወህኒ እንወረውርላችኋለን” ተብሎ ቃል ተገባላቸው፡፡
ዱለታውም ሴራውም ተቀናጀና ታሰረች፡፡ ርዕዮት “ሽብርተኛ” ተባለችና ተከሰሰች፤ተፈረደባት፡፡ በርዕዮት ላይ የፈረዱ ዳኞች በእርግጠኝነት ህጉን ተረጐምን ብለው ፈርደዋል፡፡ ዐቃቢ ህጐችም የህግ የበላይነት ለማስከበር ብለን ጥፋተኛን ለህግ አቅርበናል ብለው እንደሚሉ አንጠራጠርም፡፡ፖሊስም ተጠርጣሪ አግኝተን ለህግ እንዲቀርብ ሰርተናል ሊሉን ይችላሉ፡፡ ጠ/ፍ/ቤት ያለውን ብሏል፡፡ ሁሉንም ለታሪክ እንተወው!! ርዕዮት ዛሬ የ5 ዓመት ጽኑ እስረኛ ተብላ ቃሊቲ ትገኛለች፡፡ርዕዮት “ዛሬም የታሰርኩበትን ፁሁፎቼን አንብቡልኝ” ብላ በመጽሐፍ መልክ ጠርዛ አቅርባልናለች፡፡
የቃሊቲ ብዕሯም ምን እንደሚል ከላይ አንብበነዋል፡፡ ዓለም የሸለማት እኛ ብዙም የማናውቃት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ዛሬና ትላንት ምን እንደፃፈች “የኢህአዴግን ቀይ እስክሪብቶ” መጽሐፍ ገዝቶ ማንበቡ የበለጠ እንድናውቃት ይረዳናል፡፡
No comments:
Post a Comment