ኢሳት ዜና:- ነሀሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ ከፍተኛ የህዝብ
የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ገዢው ፓርቲ ህዝብን ለማሳመን ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸውን
ካድሬዎች ወደ ገጠር መላኩ ታውቓል።
የብአዴን ካድሬዎች በአማራ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ህዝቡን እንዲያረጋጉ እንዲሁም የህዝቡን ስሜት እንዲያጠኑና ወደ ማእከል ሪፖርት እንዲያደርጉ ተልከዋል። ካድሬዎቹ ህዝቡን ለማሳመን ምን ማለት እንዳለባቸው በትክክል እንደማያውቁ፣ ይልቁንም ራሳቸው ካድሬዎቹ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
ከታማኝ የብአዴን ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ለክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንኳ አልተገለጠም። ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ መለስ ከመጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በፊት ሥራ ይጀምራሉ ሲሉ አቶ በረከት ስምዖን ተናግረዋል ።
ቀደም
ሲል በሰጧቸው መግለጫዎች አቶ መለስ በቅርቡ ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ ከማለት አልፈው፤ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ
ያልፈለጉት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትሩ፤ለመጀመሪያ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥራ መመለሻ ጊዜ
ተናግረዋል።
የመንግስት ቃል አቀባዩ አቶ በረከት ስምዖን ይህን የተናገሩት፤ ጽህፈት ቤቱ በአውስትራሊያ ከሚገኘው ኤስ.ቢ.ኤስ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህክምናቸውን ጨርሰው በአሁኑ ሰዓት በእረፍት ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ በረከት፤”በቅርቡ እረፍታቸውን በመጨረስ ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
“በቅርቡ
ሲሉ መቼ ማለትዎ ነው? ከመጪው የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በፊት አገር ቤት ይገኛሉ?በየዓመቱስ እንደሚያደርጉት
የመልካም አዲስ ዓመት መግለጫ ያስተላልፋሉ ብለው በእርግጠኝነት ሊነግሩን ይችላሉ?” በማለት ከራዲዮው
ለቀረበላቸው ጥያቄ፦”እጅግ በጣም እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ”ነው ያሉት አቶ በረከት። “እንደውም ይህ ነገር ፤ ከአዲስ ዓመት በፊት ባለው ጊዜ ይሆናል”ሲሉም ተደምጠዋል።
ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ፦”አቶ መለስ ወደ ሥራቸው መቼ ይመለሳሉ?” ብለው አቶ በረከትን ከሳምንት በፊት ሲጠይቋቸው፦”ቀኑን በትክክል መናገር አይቻልም” ነበር ያሉት።
በዚህ
ቃለምልልስ ግን አቶ መለስ ባለፉት ዓመታት ያስጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ዳር ለማድረስ በፍጥነት ወደ ሥራ ገበታ
የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ያብራሩት ቃል አቀባዩ፤ ከአዲስ ዓመት በፊት ወደ ቢሯቸው በመግባት ሥራቸውን
እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
አቶ መለስ ከአደባባይ ከጠፉ ወደ ሁለት ወራት እየተጠጋቸው ነው። ከህዝባዊ
ወያነ ሀርነት ትግራይ(ህወሀት) መስራቾች አንዱ የሆኑት እና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የሰላምና የልማት
ፕሬዚዳንት ተብለው በሟቹ ዶክተር ክንፈ አብርሀ ምትክ የተመደቡት አቶ ስብሀት ነጋ፤ ቀደም ሲል ከአሜሪካ ድምጽ
ራዲዮ የአማርኛው ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ፦አቶ መለስ ከአስር ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራቸው
እንደሚመለሱ መናገራቸው ይታወሳል።
አቶ ስብሀት ቃለ -ምልልሱን ከሰጡ ሦስተኛ ሳምንታት እየተቆጠሩ
ቢሆንም፤አቶ መለስ ወደ ሥራቸው ሊመለሱ ቀርቶ በትክክል ስለሚገኙበት ሁኔታ እና ስላሉበት ቦታ ህዝቡ ግልጽና ተጨባጭ
መረጃ ሳያገኝ ቆይቷል። ነገሩ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ነው አቶ በረከት ለኤስ ቢ ኤስ ራዲዮ፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጪው አዲስ ዓመት በፊት ቢሯቸው ውስጥ ገብተው ሥራቸውን ማከናወን እንደሚጀምሩ የተናገሩት።
‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብራሰልስ ሴንት ሉክ ሆስፒታል ተኝተው በነበሩበት ጊዜ ከጠየቋቸው የመንግስት ባለስልጣናት መካከል አንደኛው አቶ በረከት እንደነበሩም በቃለ-ምልልሱ ተጠቁሟል።
“በሽታቸው
ምን ዐይነት ነው? ቅለትና ክብደቱ እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ለአቶ መለስ ከሐኪማቸው የተነገረ እና እርስዎ
የሚያውቁት ነገር ይኖራል?” በማለት ለቀረበላቸው ተከታይ ጥያቄ፦ በሰለጠነው ዓለም እንደሚደረገው ሁሉ ይህ ጉዳይ
በሐኪሙ እና በታማሚው መካከል ብቻ ያለ ጉዳይ እንደሆነ አቶ በረከት ተናግረዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኙ ከሆነ፤ እንደ መንግስት ቃል አቀባይነትዎ ምስላቸውን በፎቶ ወይም በቪዲዮ አስደግፎ
ማሳየቱን ያልወደዱበት ምክንያት ምንድነው?ይህ ብልህ እርምጃ ነው ብለው ያስባሉ? ከዚህ ጋር በተያያዘስ ሥራዬን
በአግባቡ እየተወጣሁ ነው ብለው ያምናሉ? “የሚል ጥያቄም ከራዲዮው -ለአቶ በረከት ቀርቦላቸው ነበር።
ለጥያቄው፦“የኛ ሥራ የሚታወቅ ነው” በማለት ነው አቶ በረከት ምላሽ መስጠት የጀመሩት፦ አቶ በረከት በቃለ-ምልልሱ መንግስታቸው በህዝብ ተዓማኒ እንደሆነ መግለፃቸው፤ ብዙዎችን ፈገግ አሰኝቷል።
መንግስትን
አጠንክሮ በመተቸቱ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ይሰራበት
በነበረው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ፦” ውሸታሙ እረኛ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሁፍ ፤ መንግስት መገለጫው ውሸት
ከመሆኑ ብዛት ፤ህዝብ መንግስትን ማመን ያቆመበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ መግለጹ ይታወሳል።
የግንቦት
ሰባት ለፍትህ ለነፃነት እና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀ-መንበር የሆኑት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው በአንድ ወቅት
ስለ ኢህአዴግ እና ስለሚያስተዳድራቸው ሚዲያዎች ውሸት ከመጠን ማለፍ ሲናገሩ፦ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የተወለደ
ልጅ ፤በመንግስት ሚዲያዎች እውነት ሳይሰማ 20 ዓመት ሞላው ማለት ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
በዚህ
ቃለ-ምልልስ ራዲዮው፤ -የአቶ መለስን የጤና መታወክ ተከትሎ ከተፈጠረው ውዥንብር ጋር በማያያዝ አቶ በረከትን
-“ሥራዬን በአግባቡ እየተወጣሁ ነው ይላሉን?” በማለት የሰነዘረው ጥያቄ፤ ሚኒስትሩን ሳይቆረቁራቸው እንዳልቀረ
ተገምቷል። አቶ በረከት፦”ሰዎች እየጠበቁኝ ስለሆነ ከዚህ በላይ ላናግራችሁ አልችልም”በማለት በስልክ የሰጡትን ይህን ቃለ-ምልልስ ያቆሙት፤ ከዚህ ጥያቄ በሁዋላ ነው።
አይጋ
ፎረም የተሰኘው የኢህአዴግ ድረ-ገጽ በተመሳሳይ ከሳምንታት በፊት በለጠፈው ጽሁፍ ፦”ዓለም በአቶ መለስ ጤና ዙሪያ
የተፈጠረበትን ብዥታ ለማጥራት የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴርን መግለጫ እየጠበቀ ባለበት ጊዜ፤ አንጋፋውና ልምድ ያካበቱት
የህወሀቱ መስራች አቶ ስብሀት ሁሉንም ግልጽ አድርገውታል”በማለት አቶ በረከትንና የሚመሩት መስሪያ ቤት
በመንቀራፈፍ መውቀሱ እና አቶ ስብሀትን ማወደሱ አይዘነጋም።
ሪፖርተር ጋዜጣ በበኩሉ በቀጣዩ ቀን
ማለትም እ.አ፣አ በጁላይ 25-2012 ረቡዕ እትሙ፦“ሳሩን አየህ እና በሬውን ሳታይ እንዳይተረትብን “በሚል
ርዕስ ባወጣው ርዕሰ አንቀጽ ፦ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እየተፈጠሩ ላሉ ውዥንብሮች እና ተቃውሞዎች፤
የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትን አሠራር ተጠያቂ የሚያደርግ አቋም አንጸባርቋል።
በኢህአዴግና ደጋፊ ሚዲያዎች
ላይ የአቶ መለስን መታመም ተከትሎ አቶ በረከትን እና የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ጥያቄዎችና
ፅሁፎች በተከታታይ መንጸባረቃቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መሰወር ተከትሎ በገዥው መንደር አለ የሚባለውን የ እርስ
በርስ መሻኮት አመላካች ነው ይላሉ -ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች። ምንም አቶ በረከት በሰጡት
ቃለ-ምልልስ – “እኛ ኢህአዴጎችን የዚህ ዓይነት ነገር ሲያልፍ አይነካንም” ሲሉ ቢደመጡም።
ሌላው አነጋጋሪ ነገር በርካታ የመንግስትና የድርጅት ሚዲያዎችን በስራቸው የሚያስተዳድሩት አቶ በረከት ይህን ቃለ-ምልልስ እንዴት ለኤስ.ቢ.ኤስ ራዲዮ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኑ? የሚለው ጉዳይ ነው። አንዳንዶች ይህን ያደረጉት፤ ውጪአገር በሚገኙ ሚዲያዎች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ነው በማለት ይናገራሉ።
ኤስ.ቢ.ኤስ ቀደም ሲልም የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያምን ቃለ-መጠይቅ ማድረጉ አይዘነጋም። ከሁለት
ወር በፊት በሬጋን ህንፃ በተደረገው የቡድን 20 አገሮች ስብሰባ ላይ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ተቃውሞ ከሰነዘረባቸው
በሁዋላ አቶ መለስ በአደባባይ የታዩት በሜክሶኮ የተደረገውን ቀጣይ ስብሰባ ለመካፈል ወደዚያው ባቀኑበት ጊዜ
ሲሆን ፤ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ጋር ሲጨባበጡ በሚያሳየው በዚሁ ቪዲዮ ላይ ሰውነታቸው ከመጠን በላይ ቀንሶ መታየታቸው
ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment