Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Sunday, August 5, 2012

‹‹እኛ ስራችንን ጨርሰናል፤ ከዚህ በኋላ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት ህዝቡ ነው!!››

በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ: ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ባለፉት ሁለት እትሞች ፍትህ ገበያ ላይ አልዋላችም፣ አንዱ ታትሞ ሲታገድ አንዱ ሳይታተም ነው የታገደው፤ ስትል እንደነበረው የማይታወቅ ቡድን እየከለከለህ ነው? በትክክል የከለከለህ አካል አይታወቅም ብዬ ነው፡፡ በመጀመሪያ የሆነው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሀምሌ 13 ቀን ለምትወጣው ጋዜጣችን ሀምሌ 12 ቀን ለህትመት ስንሄድ ሳንሱር አድርጎ ‹‹አላትምም›› በማለቱ አርብ ዕለት አልወጣችም፡፡

ለምን እንዳላተሙም ሄደን ስንጠይቃቸው የስራ ኃላፊዎቹ የመጀመሪያ ገፅ ላይ ያሉትን ‹‹እነዚህ እነዚህን ዜናዎች ቀይሩ›› አሉን፤ ይህ ሳንሱር መሆኑንና መስሪያ ቤቱ ጽሑፍ ተቀብሎ ከማተም ውጪ የፍርድ ቤት ስራ ሊሰራ እንደማይችል፣ ‹‹ይሄ ያስከስሳል አያስከስምም፣ ይህ ወንጀል ነው አይደለም›› የሚል ስልጣንም እንደሌለው አስረድተን የማተም ግዴታ እንዳለበት ስንነግራቸው ‹‹ተነጋግረን እንወስን›› ብለው ለከሰአት በኋላ ቀጠሮ ሰጥተው አሰናበቱን፡፡ ያው ብርሃንና ሰላምን እንዲህ ሲል በጎን ከሚመራው አካል መመሪያ ለመቀበል እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ከሰዓት በኋላ 8፡30 ስንሄድ ‹‹ይውጣ!›› እያሉ ይማገቱ የነበረበትን ሁኔታ ትተው ጋዜጣዋ እንዲታተም ተፈቀዷል አሉንና ታተመች፡፡


ከማተሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ ጨርሰን ስንወጣ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታውና ጋዜጣው ከታተመች በኋላ ያገዱት አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ እዚያው ቁጭ ብለው እየጠበቁ ነበር፡፡ ስለዚህ ጋዜጣዋ ታትማ ከመውጣቷ በፊት ነው ሳንሱር ተደርጋ የተጋደችው ማለት እንችላለን፡፡በምን ማረጋገጥ ይቻላል ? የሚገርመውና ለሳንሱር መቸኮላቸውን የምታውቀው ማገድ የነበረባቸው ጋዜጣዋ ጋዜጣ ሆና ከታተመች በኋላ ሀምሌ 14 መሆን ሲገባው፣ የእግድ ደብዳቤ የወጣው ገና ከመታተሟ ቀድሞ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡ ያልታተመውን ፅሁፍ መመርመር እንደማይችሉ ህገ - መንግስቱ ደንግጓል፡፡

 ሆኖም ቀድመው ካዩ እና እንዲወጣ ካልፈለጉ ህትመቱን የፈቀዱት ‹‹ቀድመን አላየንም›› የሚለውን ሀሳብ ስለጉዳዩ ለማናውቀው ሰዎች ለማሳየት ነው ? ወይስ ዞሮ ዞሮ ማገዳቸው ላይቀር አንተን ለማክሰር ነው ? ማክሰር የሚለውን በሁለተኛ ደረጃ ነው የማየው፤ በርግጥ እንዲህ አይነቱ እቅድ እንዳላቸው አውቃለሁ፤ በእለቱ ግን ቅድመ ምርመራ/ሳንሱር አደረጋችሁ እንዳይባሉ ነው፤ እግዱ የተላለፈው ግን ነገ ሊወጣ ዛሬ ነው፡፡ ጋዜጣው በቀኑ ‹‹ፕሌት የለም›› በሚል ተልካሻ ምክንያት ሳይታተም ቀርቶ ስለነበረ የሚወጣው ሀምሌ 14 ቀን እንደመሆኑ እግዱም መፃፍ የነበረበት ሐምሌ 14 እንጂ ሀምሌ 13 አልነበረም፡፡ እነሱ ግን ያገዱት ሳይታተም ሀምሌ 13 ቀን ነው፡፡

 ስለዚህም ሁለት ነገር ግልፅ ማድረግ እፍልጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ከደርግ ውድቀት ጋር አብሮ የወደቀው ሳንሱር ተመልሶ መምጣቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ታግዷል›› የሚል ደብዳቤ እየደረሰው ጋዜጣዋን ያተምው ብርሃንና ሰለማም ማተሚያ ቤት ኪሳራውን መውሰድ ግዴታው እንደሆነ ማለቴ ነው፡፡ከዚያስ? ከዚያማ መንግስት ‹‹ለብሄራዊ ደህንነቴ ያሰጋኛል›› ካለ ጉዳዩን ፍርድ
ቤት ስለሚፈታው በሚል የቀጣዩ ሳምንት ስራችንን ወደ መስራቱ ነበር የሄድነው፡፡ ስራውንም አጠናቀን ሐሙስ 5፡00 ሰዓት ላይ በድጋሚ 30,000 /ሰላሳ ሺህ/ኮፒ ለማሳተም ክፍያ ለመፈፀም ስንሄድ ገንዘብ ተቀባዮቹ ‹‹ፍትህን እንዳትቀበሉ ተብለናል›› አሉ፡፡ 

በዚህ ጊዜ ወደ ኃላፊዎቹ ሄደን ስንጠይቃቸው ‹‹በማናጅመንት ደረጃ ወስነናልና አናትምም›› አሉን፡፡ ይህ አግባብ ያለመሆኑን ነገርናቸው፣ ማተሚያ ቤቱ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ መጠን ለማናቸውም ህጋዊ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ግዴታው እንጂ የማማረጥ መብት እንደሌለው አስረግጠን ነገርናቸው፡፡ ይሄን ጊዜ በጎን በኩል ከፍትህ ሚኒስትር ‹‹እንዳታትሙ›› የሚል ትዕዛዝ እንደደረሳቸው ነገሩን፣ እኛም ፍትህ ሚሚስቴር ሄደን ሚኒስትር ዲኤታውን አቶ ብርሃኑ ፀጋዬን አነጋገርናቸው፤ እርሳቸውም ‹‹ለነሱ የጻፍነው ደብዳቤ የሚያሳየው የሀምሌ 14ቱን እትም ብቻ ነው፡፡
 
ድጋሚም ሆነ በጎን አላዘዝንም፣ ታዘናል ካሉ ማን እንዳዘዛቸው ይናገሩ›› አሉን፡፡ ሁኔታው ሁሉ ተራ የቃላት ጨዋታ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ይህንኑ ለማተሚያ ቤቱ እንዲነግሩልን ብንጠይቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡በመቀጠል ምን እርምጃ ወሰዳችሁ? በማግስቱ የአቃቤያነ ህግ አለቃ አቶ ሚካኤል ተክሉን አገኘናቸው፡፡ እርሳቸው ግን ጠንከር ብለው ‹‹ከዚህ ቀደም ካንተ ጋር ማዕከላዊ ሁሉ ተገናኝተናል፤ እስከ ዛሬም ያለከው መንግስት ምሕረት አድርጎልህ ነው፣ አሁን ግን ምህረት አያደርግልህም፣ ወንጀል እየሰራህ እንደሆነ ማወቅ አለብህ›› አሉኝ፡፡ ሸገር ራዲዮ ላይም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ‹‹ፍትህ ጋዜጣ ወንጀል ትሰራ እንደነበር ስንከታተል ነበር›› ያሉትን ስንደምረው እንግዲህ ይህ ተቋም የተለመደውን እኩይ ስራውን በፍትህ ላይ ለመስራት እያሴረ እንደሆነ አመላካች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በአጠቃላይ ኢህአዴግ ፍትህን ከህትመት ውጭ ለማድረግ ሁለት አይነት ጨዋታ ተጫውቷል፡፡ምክንያቱም መጀመሪያ የሀምሌ 14ቱን ሲያግድ የእግድ ደብዳቤ አዘጋጅቶ ህግን የተከተለ ለማስመሰል ሞክሯል፡፡ የአሁኑን ሲዘጋ ደግሞ ተቋማትን ነው የተጠቀመው፡፡ ብርሃንና ሰላምን በማጋፈጥ ማለቴ ነው፡፡ መቼም ህጋዊነትና ህገ ወጥነትን እየቀላቀሉ መጠቀም የስርዓቱ መገለጫ ባህሪ እንደሆነ 21 ዓመት ሙሉ ያየነው ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት እየያዘ የመጣው ሀይል ነው ጋዜጣዋን የከለከለው የሚል ‹‹Facebook›› ላይ ለጥፈሀል፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከልከል ደግሞ በነእስክንድርም አይተናል፤ያንተ ክልከላ የቱ ነው? ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የነ እስክንድር ነጋን ፣ የነ ዳዊት ከበደን፣ የነወሰንሰገድ ገ/ኪዳንን፣ የነዘካሪያስ አሳታሚን በአጠቃላይ 5 ጋዜጦችን ህግን ሽፋን በማድረግ ነው ያገዷቸው፤ ሌሎች ወደ ሃያ ሶስት የሚሆኑ ጋዜጦችን ደግሞ ለማተሚያ ቤቶች በሙሉ የማስፈራሪያ ደብዳቤ በመበተን ‹‹እንዳታትሙላቸው›› በማለት ነው እንዳይታተሙ ያደረጓቸው፤ እነ ‹መዝናኛ›ን የመሳሰሉ ጋዜጦች ከህትመት ውጭ የሆኑት በዚህ መልኩ ነው፡፡

 በተለመደው የኢህአዴግ ታክቲክ ነው፡፡ ዛሬም ያንን ነው ፍትህ ላይ የተገበሩት፡፡በእኔ እምነት ይህ እየሆነ ያለው የአቶ መለስን የጤና መታወክ ተከትሎ በተከሰተው የስልጣን ሽኩቻ የበላይ እየሆነ የመጣው ‹‹አክራሪ ሀይል›› ቡድን ለደጋፊዎቹ እንደ መጫወቻ ካርድ እንዲያገለግለው ፍትህን ለመታያ መስዋዕት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ወደ ህትመት እንድትመለስ ካልተፈቀደልህ የስርዓቱን የፍትህ ተቋማት በማመን፣ ተከራክሬ አሸንፌ ወደ ስራዬ እመለሳለሁ ብለህ ታስባለህ ? ብዙ ሰዎች በስርዓቱ ውስጥ ያለውን የፍትህ ስርዓት ተፈታትነው አሸንፈዋል፡፡ እኛም በዚያ መልኩ ተጉዘን የፍርድ ቤቱን ነጻነትና ገለልተኝነት አሊያም ተቃራኒውን በሚገባና በግልጽ ለዚህ ትውልድም ሆነ ለታሪክ ለአደባባይ እናበቃለን፡፡

በዚያስ ካልተሳካላችሁ የመጨረሻ አማራጫችሁ ምንድን ነው ? በዚህ ስራ መቼም ተጽእኖ እየፈጠራችሁ ነበርና እምቢ ብትባሉ ከፕሬስ ውጭ በምን ትሰማራለችሁ ? ከዚያ በፊት ለምሳሌ ፕሬስ
አሳታሚዎች ማህበር ተመስርቷል፤ሊቀ መንበሩ አቶ አማረ አረጋዊ ናቸው፡፡ ምክትል ሊቀ - መንበሩ አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ለነሱ ደብዳቤ ጽፈናል፤ ከዚህ በፊት ‹‹የህትመት ስታንዳርድ ውል›› ብሎ ካመጣው በተለየ ማተሚያ ቤቱ በተናጠል ማገድ ስለጀመረ በጻፍነው ደብዳቤ መሰረት በአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶና ጉዳዩ ተጣርቶ እርምጃ ይወስዳል ብለን እናምናለን፡፡አለም አቀፍ ተቋማት ፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት፣ …. በስርዓቱ ላይ ጫና ፈጥረው የኢህአዴግን የፕሬስ መጋፋቱን ድርጊት ይገድቡ ዘንድ እናሳውቃለን፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ አለም አቀፉ ድጋፍ ጥሩ ነው፡፡ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የደረሰውን በማውገዝ CPJ እና IPI ጠንካራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በማያወላዳ መልኩ በኢትዮጵያ ያለውን ነጻ ሚዲያ መግደል መሆኑን ነው ያተኮሩበት፡፡ በተረፈም ሀፊንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ፣ AFP፣ AP…የመሳሰሉ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን በመስጠት አጋርነት አሳይተዋል፡፡ 

በውጭ ሀገር ያሉ ሁሉም የኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎችም ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ የአሜሪካ ድምጽ
ራዲዮ፣ ጀርመን ድምፅ ራዲዮ፣ ሸገር ሬዲዮ፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጣም ጉዳዩን ለህዝብ ለማሳወቅ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ እኛም በዚህ መልኩ ስርዓቱ ላይ ጫና በማሳደር ከፍትህ ላይ እጁን ያነሳ ዘንድ እስከ መጨረሻው እንታገላለን፡፡ ለምን እንደ ጓደኞችህ አትሰደድም ? አንተ እንዲያውም ‹‹ጓደኞቼን መልሱልኝ›› እያልክ ትጽፋለህ፤በአካል ከሚደርስብህ ወከባ በተጨማሪ በአይጋ ፎረም፣ በአዲስ ዘመን፣ በክብ ጠረጴዛ ጫናዎች ነበሩ፤ ከዚያም ውጭ አዲስ ነገሮች ከሀገር ሲሰደዱ እንደምታስታውሰው መንግስት በሽብርተኝነት ሊከሰን በማሰቡና ክሱ ደግሞ እስከ እድሜ ልክ እስራት ስለሚሄድ ያንን ለመቀበል ዝግጁ አልነበረንም ነው ያሉት፣ እናንተ ግን ጋዜጣዋ ተከልክላም ሀገር ውስጥ ናችሁ፡፡ ስደትን እንደ አማራጭ ያልወስድከው ለምንድን ነው ?

ፍትህን እንደምትከታተል አውቃለሁ፡፡ ካየሀቸው ጽሁፎቼ መካከል ‹‹ጓደኞቼን መልሱልኝ›› የሚለው
አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ጓደኞቼ ወደውና ፈቅደው እንደማይሰደዱ አውቃለሁ፡፡ከመሰደዳቸው በፊት አብዛኛዎቹ ‹‹ይህ አገር የማነው?›› እያሉም ይፅፉ ነበር፣ እኔ ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ‹‹ሀገሩማ የኔ ነው›› ብዬ ጽፌያለሁ፤ ይህንን ያልኩበት ምክንያት ለመብት ነጠቃና ለጭቆና መፍትሄው ስደት ሳይሆን ማንኛውንም መስዕዋት ከፍለህ መብትህን ማስከበር በመሆኑ ነው፡፡ ለእንዲህ አይነቱ ምሳሌ ደጋግሜ እንደምናገረው እኛ አርአያ ማድረግ ያለብን ጠ/ሚ/ር መለስን ነው፡፡ አቶ መለስ የደርግ አገዛዝ አፈና
ሲበረታባቸው ‹‹ይህ አገር የማን ነው› ብለው አልጠየቁምም አልተሰደዱምም፡፡ያደረጉት ምንድን ነው? ብለን ከጠየቅን የምናገኘው መልስ የተነጠቁትን መብት በትግል አስመለሱ የሚል ይሆናል፡፡

 እኛም በማንኛውም ሰላማዊ መልኩ መብታችንን መልሰን ለማግኘት እንሞክራለን እንጂ እስርን እና የመሳሰሉት ነገርን በመፍራት በመሰደድ ለሚመጣውም ሆነ ለአሁኑ ትውልድ መጥፎ ምሳሌ አንሆንም፡፡ ደጋግመን እንዳልነው ‹‹ጉዟችን እስከቀራኒዮ ድረስ ነው››፡፡ ስለዚም ቀራኒዮ መች ደረስን? እናም ወደ ቀራኒዮ የሚጓዝ ስደትን መፍትሄ አያደርግም፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያኖችም መብታቸው በተነጠቀ ቁጥር ውስጥ ውሱን ከሚንሾካሾኩ፣ ወይም ከሚሰደዱ አሊያም በብእር ስም በየማህበራዊ ድር- ገፆች ከሚፅፉ መብታቸውን መልሰው ለማግኘት እንዲነሱ አበረታታለሁኝ፡፡እኔ እንደ ወዳጅ ጋዜጣዋ ለዚህ ስርዓት ዴሞክራሲያዊነት ምስክር ከምትሆን፣ ተቺ እስከሆነች ማለቴ ነው፣ እንኳንም ተዘጋች ብል ትስማማለህ ? አልስማማም፡፡ ለምን መሰለህ የማልስማማው? ለፍትህ ህትመት ፈቀደ አልፈቀደ ስርአቱ ኢ - ዴሞክራሲያዊና አምባገነን እንደሆነ ምንም አያከራክርም፡፡
 
በተቃራኒው የፍትህ መኖር ድምጽ አልባ ለሆኑ ወገኖች እንዲሁም ይህን አስከፊ ስርዓት ለመቀየር በሚደረገው ሰላማዊ ትግል ላይ ድርሻ አላት፡፡ ተዘግታ ስርአቱን ከምታሳጣ ይልቅ ድምፅ አልባ ለሆኑት ድምጽ መሆኗ፣ የፍርሃትን ቆፈን ገፋ በረከቶችን ወደ ሰላማዊ ትግል ማውጣቷ የተሻለ ጠቃሚ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ተመስገን ፍትህን ተቋማዊ (institutional ) አላደረጋትም ይባላል? ለምሳሌ አብዛኛው ሰው ያንተ ጽሁፍ አንባቢ ነው፣አንተ ባትፅፍ ሰው አይወድም፡፡ 

የውጭ ጽሁፎች ላይ ጥገኛ የሆነ ጋዜጣ ነው ይባላል፡፡ ዛሬም ማስተዋል ህትመትና ማስታወቂያ ስራ ድርጅት ነው የሚለው፤አዲስ ነገሮች ከመስፍን ነጋሽ አሳታሚ ወደ አዲስ ነገር ተቋም አሳታሚ ለማምጣት ጊዜ አልፈጀባቸውም፤ምን አስባችሁ ነበር እናንተ ? ፍትህ ተቋማዊ ነው፣ ፍትህ ሲጀመር በ‹‹ተመስገ አሳታሚ›› ነበር የምትታተመው፣ ከየካቲት 25 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የፕሬስ ህግን ተከትሎ ወደ <plc> ዞሯል፡፡ ‹‹ማስተዋል›› የሰው ስም ቢሆንም የአሳታሚ ተቋሙ ስም ነው፡፡ አዲስ ነገርም ከአዋጁ በፊት እንዳልከው ‹‹በመስፍን አሳታሚ ድርጅት›› ስር ነበረች፡፡ ከአዋጁ በኋላ ደግሞ አዲስ ነገር አሳታሚ በሚል ተቀይሮአል፡፡ ሁለተኛ የውጭ ጽሁፍ ላይ ጥገኛ አይደለንም፡፡

አምደኛ ያልሆኑ ሰዎች ሰፊ ቦታ ይይዙ ነበር ማለቴ ነው፡ቋሚ የድርጅቱ አምደኞች ናቸው ባብዛኛው የሚሸፍኑት፡፡ ለውጭ ጽሁፍ የምንሰጠው ገፅ 12 ላይ ‹‹ነጻ አስተያየት›› አለ፣ ገፅ 4 ላይም ‹‹ነፃ አስተያየት›› አለ፤ ከሁለቱ ውጭ ለውጭ ሰዎች መች ቦታ አለን? ያንተ መረጃ የተሳሳተ ነው ማለት ነው፡፡ አክቲቪስት ነህ እንዴ ተመስገን? በጣም ለመተቸት አትፈራም፣ ሰዎችን የማስከተል ባህሪም አለህ፣ ‹‹ለዚህ ብዬ ነው እንዲህ የምላችሁ፣ በዚህ በኩል እመኑኝ፣ እንደዚህ ብታደርግ እንዲህ ይሆናል
የምልህ ለዚያ ነው….›› ትላለህ፤እና አቅደህ ነው አክቲቪስት ለመሆን ወይስ ባጋጣሚ ነው ? - አዝማሚያው ሊኖር ይችላል - ይህ ለምን የሆነ መሰለህ - የኢትዮጵያ ሚዲያን ታውቃለህ - በተመቻቸ መሬት ላይ አይደለም የምትሰራው፣ ለምሳሌ ዛሬ ፍትህ ታገደች፣ እስከ ዛሬ ከ140 ክሶች በላይ ተከስሻለሁ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ጠርተው ደብድበውኛል፣ በቪዲዮ ቀርፀውኛል፣ ‹‹ከዚህ በኋላ…›› በሚል ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውኛል፣ ይህን እስከዛሬ ለሚዲያ አልተናገርኩም፣ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ የደህንነት ጫናዎች ይደረጉብኛል፣ በዚህ ውስጥ ሆነህ በምዕራባውያን ሀገራት እንዳሉት ጋዜጣዎች ‹‹ጋዜጠኛ›› ብቻ ሆነን ልንቀር አልቻልንም፣ ህዝብ ይህን በደል ያውቅ ዘንድ ግፊት ማድረግ ነበረብኝ፣ ህግ እንዲከበር፣ ይህን እንዲታገል ጽሁፎቼን በዚህ መልኩ እቃኝ ነበር፡፡ 

በአጠቃላይ ‹‹Activist›› ነኝ ባልልም እስከዛሬ ፍትህ ስታደርግ የነበረው ግን ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ሁለቱም ጎን ለጎን እየሄዱም ይመስለኛል፡፡ጋዜጣዋ ከመተቸት ባለፈ መፍትሄ ጠቋሚ ነበረች ?- ሙሉ በሙሉ መፍትሄ ሰጪ አዝማሚያ የያዘች ነበረች ብሎ ለመናገር ድፍረቱ የለኝም፡፡በተወሰነ ደረጃ፣ በጋዜጣዋ አቅም ልክ የመፍትሄ ሀሳቦችን የምታቀርብበት ብዙ ጊዜት ነበሩ፡፡ በትችቱ ልክ መፍትሄ ትሰጥ ነበር ብዬ ግን አልናገርም፡፡ ሆኖም ችግሩን አጉልቶ ማሳወቅ ለመፍትሄው መቃረብ ነው፣ ብዙ ጊዜ ፍትህ ችግሮችን በማሳየት ከግማሽ መንገድ በላይ ትጓዝ ስለነበር መፍትሄ ጠቋሚ ነች ልንላት እንችላለን፡፡ፍትህ በኢትዮጵያ ፕሬስ ምን አበርክቶ ነበራት ? ድህረ 97 የነበረውን ቆፈን መግረፍ ነበር አላማችን፣ ያንን በትክክል እያሳካን ነበር፡፡ 

ሌላው ጋዜጠኝንት ‹‹በሰምና ወርቅ›› እንደማይቀርብ ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ጥሩ መልዕክት ያስተላለፍን ይመስለኛል፡፡ ቆፊኑን ገፈናል ስትል ግን፣ እውነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዝም ጭጭ ብለው የነበሩት ምሁራን ፍትህ ላይ በመጻፍ ድምጽ ማሰማት ጀምረው ነበር፣ ስርአቱ ይህንን መነቃቃትና የቆፈኑ መገፈፍ ያስፈራው አይምስልህ -እናንተን ለማገድ ያበቃው ማለቴ ነው፤- ልክ ነህ - ኢህአዴግ በአሁኑ ሰዓት የአፍሪካ ትልቁ አምባገነን ለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም፤ከሙባረክ ውድቀት በኋላ ቦታውን የተረከበው ኢህአዴግ ነውና፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ሚዲያዎችን የስልጣኑ ስጋት አድርጎ ነው የሚያያቸው፡፡

 ከዚህ ፍርሃት የመነጨ ነው ፍትህ ላይም የተወሰደው እርምጃ፡፡- ምን ታጎድሉብናላችሁ? በተለይ አርብ አርብ ፣- ይህን አንተ ነህ የምትፈርደው፡፡ ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጋዜጣ በ7 ሰው ይነበባል የሚል ጥናት አለ፡፡ ይህንን ደግሞ በ30 ሺህ ብትመታው ሁለት ሞቶ አስር ሺህ ሰው አርብ አያነብም ማለት ነው፡፡መዝጋታችሁ እውነት ከሆነ የፍርሃቱ ድባብ ተመልሶ አይመጣም ትላለህ? ሌሎች የሚተቹት ገባ ወጣ በማለት ስለሚመስለኝ ነው፣ ፍርሃት አይመለስም፣ ለምን መሰለህ ፣ አሁን ጎበዝ ወጣት ጸሀፊዎች እየመጡ ነው፣ ለምሳሌ አንዱ አንተ ነህ፣ በርካታ አዳዲስ ጸሀፊዎች እየመጡ ስለሆነ ስርዓቱን ይገረስሱታል፡፡ እናምኢህአዴግ በማን አለብኝነት ፍትህን ቢያፍንም ሺህ የፍትህ መንፈስ ያለባቸው ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የኔና ያንተ ትውልድ ወደ ፍርሃት
አይመለስም፡፡

እናንተ ከታገዳችሁ የአይጋ ፎረም የአዲስ ዘመን እና የክብ ጠረጴዛ ስራ ምን የሚሆን ይመስልሀል ?
- አዲስ ዘመን ገፅ ሶስት ባዶውን ይወጣል - ስለ ፍትህ በሚጽፍበት ቦታ ላይ ማለቴ ነው፡፡ የአይጋ ፎረምም ዕጣ ፈንታ ሌላ ኢህአዴግን የሚያስጨንቅ እስኪነሳ የተለየ አይሆንም፣ ሰራቸው እኛ ነበረን፣ የኢህአዴግ ካድሬዎችንና ሌሎች የዋህ ኢትዮጵያውያንን በስነ ልቦና ማዘጋጀት ነበር፣ እከሌ የሚባለው ሚዲያ ከግንቦት ሰባት ጋር፣ እከሌ ከአርበኞች ግንባር፣ እከሌ ደግሞ ከአልሸባብ ጋር…እያሉ ተደጋጋሚ ጽሁፎችን በመጻፍ መንግስት ለሚወስድብህ እርምጃ ፍትሃዊነት ያዘጋጁሃል፡፡ በቀጣዩ ነጥሮ በሚወጣ ድርጅት ወይም ሚዲያ ላይ ፊታቸውን ያዞራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ አልሸባብ አስራ አራት ሺህ ዶላር መልስልኝ ባለው መሰረት መልሶ ነው የተዘጋው ሊል ይችል ይሆን መንግስት ? - ይህን ማለት አይችልም፤ በዚህ ጉዳይ ድሮ አሸናፊው መንግስት ነበር፣ አዲስ ነገርና አውራምባን ሲዘጉ ከስረው ነው አሉን፡፡ እኛ ግን እነኚህን ደረጃዎች አልፈናል፣ ባለፈው የታገተብን ከመቶ ሺህ ብር በላይ እዚያ ተይዞ ተመሳሳይ ቁጥር ለማዘዝ ማተሚያ ቤት ሄድን ነበር፤ ስለዚህ በኪሳራ ነው ሊል አይችልም፡፡

 እንዲያውም አልፎ ተርፎ መንግስት ነጥብ የጣለበት ታክቲክ ነው፣ ይህ አይነቱ የስርዓቱ የአፈጀ፣ ያለፈበት ማጥቂያ ስልት የአደባባይ ገመና የሆነም ይመስለኛል፤ልጆች፣ ትዳር፣ ህይወት እንዴት ነው ? [ረዥም ሳቅ ነበረው]፤ የሚገርም ነው፣ ትዳር የለኝም፤ ጓደኛም የለኝም፤ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፤ በፊት ከቤተሰቦቼ ጋር እኖር ነበር፤ ከሁለት አመት ወዲህ ግን ቤተሰቦቼ ከተለያዩ የስርዓቱ ባህሪና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አደገኛነት ተነስተው ከዚህ ስራ እንድርቅ ጫና ስላደረጉብኝ ብቻዬን መኖር ጀመርኩ፤ ከስምንት ወራት ወዲህ ደግሞ በደረሰብን የደህንነት ጫና እኔና ሁለቱ ምክትል አዘጋጆቼ እኔ የተከራየሁባት ቤት ውስጥ አብረን መኖር ጀምረናል፤ ደጋግመን እንደጻፍነው የቺን ቤት ወዳጆቻችን ‹‹አሲምባ›› የሚል ስም አውጥተውላታል፡፡ አሲምባ ደርግ ከፍተኛ ብትር ያሳረፈባቸው ‹‹የ ያ ትውልድ›› ወጣቶች የመሸጉባት ትግራይ ውስጥ የምትገኝ ተራራ ናት፡፡

በአጠቃላይ ጋዜጣችሁ ለምን ታገደች ማለት ነው ? እኔ እስካሁን የማውቀው ግልጽ ነገር የለም፣ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃነ ሀይሉ ‹‹ብሎምበርግ›› ለተባለ የውጭ ሚዲያ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤናና በሙስሊሙ ተቃውሞ ላይ የጻፈው ነገር አለ›› የሚል ሆኖ አግኝተነዋል፣ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤና እኛ የተለየ ነገር አልያዝንም፣ የተለያዩ ወገን መረጃዎችን እና የአቶ በረከትን መግለጫ ነው የዘገብነው፤ስለሙስሊሞች ተቃውሞ የተነሳ እንደሆነ ደግሞ መንግስት በሙስሊሙ ላይ የወሰደባቸውን እርምጃ ባገኘነው መረጃ በማጋለጣችን ቅሬታ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፣ ሚኒስትሩ እንዳሉት ያ ዘገባ ለብሔራዊ ደህንነት ያሰጋል የሚል ነው፤መቼም ሀይማኖታዊ ተግባሩን እያከናወነ ያለን ምዕመን መስጂድ ውስጥ ገብተው መደብደባቸውን መዘገብ እንዴትም ቢለጠጥ ለአገር ስጋት ነው ብዬ አላስብም፣ በግሌ እስልምና እምነትም ሆነ ሙስሊሞች ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው ብዬ ለሰከንድም ቢሆን አላስብም፡፡ እነሱ ያሉት’ኮ ‹‹መጅለስ ይውረድ ነው›› መለስ ይውረድ አላሉም፣ የሀይማኖታዊ ነጻነት ጥያቄ ነው፡፡ መለስ ይውረድ ቢሉም ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው ብዬ አላስብም፡፡ 

በአጠቃላይ ጋዜጣው ከዚህ በኋላ ለህትመት ብትበቃም በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለውን እንዲህ አይነት አፈናዎችንም ሆነ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ከመዘገብ ወደ ኋላ አንልም፡፡ እሱ አለፈ - ቀጣዩስ ለምን አልታተመም ? - እነሱ ናቸው የሚያውቁት ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ ለሚገባው አካል ምን መልዕክት አለህ ? - እኛ ስራችንን ጨርሰናል፤ ከዚህ በኋላ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት ህዝቡ ነው፣ የቻልነውን ተቋቁመን ሰርተናል፣ ጉዳዩ አሁን የፍትህ ባልደረቦች ጉዳይ አይደለም፡፡ 

ጉዳዩ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ቀጣዩ ምን ይመስልሀል ? - የአቃቤ ህግ ጥቁምታ እንደሚያሳየው መጀመሪያ ፍትህን ዘግተው አንባቢያንን እና ለፕሬስ ተቆርቋሪ የሆኑትን በሙሉ ያለማምዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አንድ ምክንያት ፈጥረው ወይም ከአንዱ አሸባሪ ድርጅት ጋር ፈርጀው እጃቸውን ይጭኑብናል፡፡ ያስሩሃል ማለት ነው፡፡ ይህ የተለመደ አሰራራቸው ነው፡፡ እኛ ግን ለሀገራችን እና ለህዝባችን ሁሉንም ለመቀበል እስከ ቀራኒዮ አደባባይ እንጓዛለን!

No comments:

Post a Comment