Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Thursday, August 9, 2012

የርዕዮት ዓለሙ መጽሐፍ ከአዟሪዎች ላይ እየተነጠቀ ነው

- ጋዜጠኛዋ በስር ፍርድ ቤት የተወሰነባት የ14 ዓመት እስር እና የ33ሺህ
ቅጣት ወደ 5 ዓመት እስራት ዝቅ ተደርጓል
- መፅሐፏ ባለፈው ቅዳሜ ተመርቋል

ባለፈው ቅዳሜ ለነምርቃት የበቃው የርዕዮት አለሙ መፅሀፍ ከአዟሪዎች እጅ በፖሊሶች እየተነጠቀ መሆኑን በተለያዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተሰማሩ መፅሀፍ አዟሪዎች ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ፡፡

በተለይ በላናቻና በቦሌ አካባቢ የመፅሀፍ የሚሸጡ ግለሰቦች እንደተናገሩት ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ፖሊሶች የርዕዮትን መፅሀፍ ለይተው በመንጠቅ አባረዋቸዋል፡፡ በ “ሽብርተኝነት” ተከሳ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ ከተባለች በኋላ 14 ዓመት እስራትና 33 ሺህ ብር ቅጣት የተፈረደባት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ በጠየቀቺው ይግባኝ ጥፋተኛ በተባለችበት 1ኛና 3ኛ ክስ ጥፋተኛ ልትባል የሚያስችል ማስረጃ ባለመቅረቡ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ይግባኙን የሰማው ጠ/ፍ/ቤት ወሰነ፡፡ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ በሽብርተኝነት በመሳተፍ እና አመራር በመሰጠት የሚያሰኝ ማስረጃ አለመቅረቡን ጠቅሶ አንድ ሰው አንቀጽ ተጠቅሶ ስለተከሰሰ ብቻ መቀጣት የለበትም በማለት ሁለቱን ክሶች ውድቅ አድርጐታል፡፡ 


ሁለተኛው ክስ ከሽብርተኛ ጋር በማንኛውም መንገድ መሥራት በሚለው መሠረት “ኢትዮጵያን ሪቪው” ለተባለ ድህረ ገጽ ዜና ሰርታና ፎቶ ግራፍ አንስታ በመላኳ 5 ዓመት እስራት ተፈርዶባታል፡፡
ከፍርድ ውሳኔው በኋላ አስተያየት የጠየቅናቸው የርዕዮት ዓለሙ ጠበቃ ሞላ ዘገየ በሰጡን አስተያየት “ደንበኛዬ በነፃ ትለቀቃለች የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ አሁን ግን ከዚህ በፊት ጥፋተኛ የተባለችባቸው ክሶች ተሽረዋል፡፡ በአንድ ክስ ጥፋተኛ ተብላለች፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብን እንነጋገራለን” ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ርዕዮት ዓለሙ የፃፈችው “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” የተሰኘ መጽሐፍ ባለፈው ቅዳሜ በራስ አምባ ሆቴል ፤ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተመርቋል፡፡ በምረቃው ዕለት ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ወላጅ አባቷ ጠበቃ ዓለሙ ጎቤቦ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በመጨረሻም የመጽሐፉን ዝግጅት ምረቃ አስተባባሪ ለነበሩት የኮሚቴ አባላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ ቅድሚያ የተናገሩት ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም የወቅቱን የፍትህ ሥርዓት “በድቅድቅ ጨለማ” መስለው አቅርበውታል፡፡ ፕ/ር መስፍን እንዳሉት “ዛሬ የታሰረቺው ርዕዮት ብቻ ሳትሆን የታሰረው የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ነው፡፡ አገራችን የተአምር አገር ናት፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ፍንጣቂ ብርሃን አለ፡፡ 14 ዓመት እስራትና 33 ሺ ብር ቅጣት የፈረዱ ዳኞች ባሉበት ሥርዓት 5 ዓመት የሚፈርድ ዳኛ መገኘቱ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ፍንጣቂ ብርሃን መኖሩን የሚያሳይ ተስፋ ነው” ብለዋል፡፡ 

በመቀጠል ንግግራቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ርዕዮትን ያወቋት በአንድ ወቅት የአዲስ ፕሬስ ጋዜጠኛ ሆና ስትሰራ ዩኒቨርስቲ ልታነጋግራቸው መጥታ እንደነበር ገልፀው አስተዋይነቷን አስምረውበታል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ ለተማሪዎች ሌክቸር እንዳላደርግ ተደርጌ ደሞዝ ብቻ እየበላሁ እንድቀመጥ ተደርጌአለሁ፡፡” ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “ሐሳብን በነፃነት ማንሸራሸር አስቸጋሪ መሆኑንን” ገልፀዋል፡፡

“የዚች ቆራጥና ጀግና ልጅ አባት በመሆኔ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል” ያሉት ወላጅ አባት ጠበቃ ዓለሙ ጎቤቦ “ርዕዮት የመጀመሪያ ልጃችን ናት” ካሉ በኋላ በቤት ስሟ “ሉሉ ባህርይዋም በተለያየ መልኩ የእኔን ይመስላል” ብለዋል፡፡ ዛሬ መሐላችን ባትኖርም መጽሐፏ ሲመረቅ ቤተሰቦቿ ደስ ብሎናል፡፡ መጽሐፏ የልጅ ልጄ ነው፡፡ እኔም የዚህ መጽሐፍ አያት ሆኜአለሁ፡፡ የመጽሐፉም መታሰቢያ ለታዋቂው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባና የጦር ጀት አብራሪ ለነበረው ኰሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ እንዲሆንላት በማድረጓ ደስ ብሎኛል፡፡ ልጄን የምመስላት በሻማ ነው፡፡ ከመታሰሯ በፊት ዛቻ፣ ስድብ መዋረድ ተፈጽሞባታል፡፡ ሁለት ወር ከ15 ቀን በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ስትታስር አልተለቀቀችም፡፡ ነገ ነፃ ሆና በተለያዩ መድረኳች ሐሳቧን በነፃነት እንደምትገልጽ አልጠራጠርም” ብለዋል፡፡

በመጨረሻ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ነጋሶ “ርዕዮት ስለ ሃይማኖት አባቶች የፃፈችውን ሳነብ 97 ዓ.ም ትዝ አለኝ፡፡ በዚያን ዓመት ያሁሉ ሰው ሲጨፈጨፍ የሃይማኖት አባቶች ዝም ብለዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊው አቡነ ጴጥሮስ በሂትለር ዘመን በጀርመን ውስጥ የሂትለር ፋሺስታዊ ሥርዓት ተቃውሞ የሞተ የሃይማኖት አባትም አለ፡፡ እኔ የኢህአዴግ አባል ስለነበርኩ በኢህአዴግ ቋንቋ አካፋን አካፋ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡

በአሁን ወቅት የሃይማኖት አባቶች አገራቸውንና ህዝባቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ረስተዋል፡፡ ርዕዮት በይግባኝ የተፈረደባትን ተከራክራ አስቀንሳለች፡፡ እስከ መጨረሻው ተከራክራ ነፃ ትወጣለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ርዕዮት ዓለሙ በ2004 ዓ.ም ጐልታ የወጣች ወጣት ጋዜጠኛ ናት፡፡ በ2005 ዓ.ም ሌላ ጀግና ወጣት እንደምናገኝ ተስፋ አለኝ ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም የተለያዩ አገራዊና ወቅታዊ ግጥሞች እና ወጐች ቀርበዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐምሌ 28 ቀን 2004 ዓ.ም በራስ አምባ ሆቴል ተመርቆ ገበያ ላይ የዋለው “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” የተሰኛ መጽሐፍም በአሁኑ ሰዓት ካዙዋሪዎች ላይ እየተነጠቀ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment