Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Wednesday, August 8, 2012

አቶ ጁነዲን ከሥልጣናቸው ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ እነ ሚሚ ስብሀቱ ጠየቁ

ኢሳት ዜና:- ነሀሴ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን  ከሃላፊነታቸው ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ እነሚሚ ስብሀቱ  መንግስትን አሣሰቡ።

“ዛሚ ኤፍ.ኤም “ ተብሎ በሚጠራው  የነሚሚ ስብሀቱ ራዲዮ ጣቢያ በየሳምንቱ አርብ  በሚተላለፈው የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ የተሰኘ ፕሮግራም ላይ መደበኛ ተወያይ የሆኑት የኢቲቪዎቹ መሰረት አታላይ እና ሳሙኤል ፍቅሬ፣ የኢትዮጵያ ፈርስት ድረ-ገጽ አዘጋጅ  ቤን ፣የቀድሞ የኢነጋማ ጸሀፊ የነበረውና  ከማህበሩ ተለያቶ  ወደ መንግስት የገባው  ወንድወሰን ከበደ ባለፈው አርብ ባደረጉት ውይይት መንግስት  የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩን ከሃላፊነታቸው አንስቶ በህግ እንዲጠቃቸው አሣስበዋል።


ባለቤታቸው ከሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ 50 ሺህ ብር እና  የሀይማኖት መፃህፍት ይዘው ሲወጡ በፖሊስ ተይዘው የታሰሩባቸው አቶ ጁነዲን ቅዳሜ በወጣው ኢትዮ ቻነል ጋዜጣ ላይ፦” ባለቤቴ ያለ ትክክለኛ ማስረጃ ታስራብኛለች!” በማለት አቤቱታ ማሰማታቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ፦“እንደ ሚኒስትርነቴ  ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ የፃፍኩት ነው” ባሉት በዚህ  ጽሁፋቸው ፤ ባለቤታቸው  ከሳዑዲ ዐረቢያ ኤምባሲ ገንዘብና መጽሀፍ ይዘው ሲወጡ መያዛቸውን አምነው፤ ሆኖም ገንዘቡና መጽሀፉ እንደተባለው  አክራሪዎችን ለመርዳት ሳይሆን  እናቷቸው ባስተላለፉላቸው ኑዛዜ መሰረት መስጊድ ለማሰራት የሚውል እንደነበር በስፋት ማብራራታቸው ይታወሳል።

የዛሚ ኤፍ ኤም  ራዲዮ ተወያዮች ሚኒስትሩ  ሊሻሩ ብቻ ሳይሆን በህግም ሊጠየቁ ይገባል ያሉት፤ ያንን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ ነው። “ሰውዬው  አንድ ትልቅ  የመንግስት ባለስልጣን ሆነው ሳለ፤ ለሀይማኖት ተቋማት የሚውል መስጊድ  ላሠራ እየተንቀሳቀስኩ  ነው ሲሉ እዛ ላይ ወድቀዋል” ያለው  የኢቲቪው ጋዜጠኛና የብአዴኑ አባል መሰረት አታላይ ፦” ሰውዬው በዚህ ብቻ  ከስልጣናቸው ሊወርዱ ይገባል” ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮ-ፈርስቱ ቤን በበኩሉ ፦ከኤምባሲ በቀጥታ በእጅ የሚሰጥ ገንዘብ፤  መንግስት የማያውቀውና ለምን እንደሚውል የማይታወቅ መሆኑን በማብራራት ፦ “አቶ ጁነዲን ተጠያቂነት የሌለበትን ገንዘብ በመቀበላቸው  ሊጠየቁ ይገባል”ብሏል። “አቶ ጁነዲን ከኔ አካባቢ ነው የተመረጡት”በማለት አስተያዬት መስጠት የጀመረው  ደግሞ ሳሙኤል ፍቅሬ ነው።

“እውነት ለመናገር አቶ ጁነዲንን በጽንፈኝነት አላውቃቸውም” ያለው ሳሙኤል፤ “ሆኖም አቶ ጁነዲንን  የመረጣቸው ሙስሊሙም፤ ክርስቲያኑም እንጂ የአንድ የእምነት ተከታይ ህዝብ አይደለም።ይህ በሆነበት ሁኔታ ልክ  የአንድ እምነት ተከታይ ህዝብ እንደመረጣቸው  መንግስታዊ ሀላፊነታቸውን ትተው ወደዚህ ተግባር መግባታቸው አሳዛኝ ነው” ብሏል።

“እኔም  በዚያ አካባቢ የዚህ ዓይነት ነገር  አደርጋለሁ። ለመስጊድ ሥራ  አዋጥቼ አውቃለሁ።ያን የማደርገው  ግን ሳሙኤል ሆኜ ነው “ሲልም አክሏል። ይሁንና  ሁሉንም ህዝብ አገለግላለሁ ብሎ የሚያስበው የኢቲቪው ጋዜጠኛ ሳሙኤል  ራሱን ሆኖ  ያን ማድረግ እንደሚችል በተናገረበት መድረክ፤ አቶ ጁነዲን ራሳቸውን ሆነው የግል እምነታቸውን  ለማራመድ የማይችሉበትን ምክንያት አላብራራም።

አወያዩዋ  ሚሚ ስብሀቱ  ፦“በኢትዮጵያ እየታዬ ካለው የአክራሪነት ስጋት  ጋር ተያይዞ ችግሮች እየታዩ ያሉት በሳዑዲ ኤምባሲ ነው” ብላለች። ሚሚ አክላም፦አቶ ጁነዲን ለመስጊድ ሥራ ነው ይበሉ አለያም ሌላ ምክንያት ያስቀምጡ፤ ሚስታቸው ከሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና የቁርዓን መፃህፍት ይዛ መውጣቷን እስካሙኑ ድረስ ሊጠየቁ ይገባል በማለት፤ የሚኒስትር ጁነዲንን  ጉዳይ በኢትዮጵያ እየታዬ ካለው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ጋር አያይዛዋለች።

ተወያዮቹ አቶ ጁነዲንን በሙስና  ሊያስጠይቅ ይገባል በማለት  ያነሱት ሌላው ነጥብ ደግሞ፤ ለግል ጉዳያቸው መንግስት የመደበላቸውን  መኪና መጠቀማቸውን ነው። ውይይቱን የተከታተሉ አንዳንድ ወገኖች በሰጡት አስተያዬት፤ የጋዜጠኞቹ የአነጋገር ድምጸት እና  ሚኒስትሩን  ለመውቀስ ያሳዩት ድፍረት፤ አቶ ጁነዲን በቅርብ መታሰራቸው አይቀርም የሚል ግምት የሚያሳድር ነው ብለዋል።

“በእርግጥ የመንግስትን መኪና ለግል ጉዳይ መጠቀም  ሙስና  ነው”ያሉት እነዚህ ወገኖች ፤”ይሁንና ከ 12 ቢሊዮን ዶላር በላይ  በእርዳታ የመጣ ገንዘብ በመንግስት ሹመኞች እና በነጋዴ ሸሪኮቻቸው አማካይነት ወደ ውጪ እንደሸሸ በሚነገርባትና- በየዕለቱ   እጅግ በርካታ ሙስናዎች በሚፈጸሙባት  አገር፤ አንድን ሚኒስትር ፦መንግስት የመደበለትን መኪና ለግሉ በመጠቀሙ ይጠየቅ ማለት፤ በሚኒስትሩ ላይ የተነጣጠረውን አደጋ  የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ ዳዊት ከበደ ቀደም ሲል ባቀረበው ጽሁፍ ፤ኢትዮጵያ ውስጥ  ሰዎች ከመታሰራቸው በፊት በነ ሚሚ ስብሀቱ የክብ ጠረጴዛ ፕሮግራም ፦” መታሰር አለባቸው” የሚል ውሳኔ እንደሚተላለፍባቸው፤ በጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ እና በአንዷለም አራጌ ላይ የሆነውን ዋቢ በማድረግ መግለጹ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment