ከአቶ መለስ ሞት ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልላዊ መንግስት ደራሼ ወረዳና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ የአንድነት ፓርቲ አባላት እየታሰሩ መሆናቸውን የወረዳው የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ በተለይ ለፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ አስታወቁ፡፡ የወረዳው ሰብሳቢ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት ‹‹አቶ መለስ በመሞታቸው ህዝብ ኢህአዴግን በማውገዝና በመቃወም ይንቀሳቀሳል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል፡፡
ህዝብ ለዚህ አላማ እንዳይንቀሳቀስ በየአካባቢው በህዝብ ተደማጭነት ያላቸውና በወቅቱ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን በማደን የፈጠራ ወንጀል በመፈብረክ እየታሰሩ ናቸው፡፡ ›› ይላሉ፡፡ የደራሼ ወረዳ አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዳፊኮ ታዬ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት ‹‹ የአካባቢው የኢህአዴግ ካድሬዎችና ደህንነቶች ተሰባስበው በህዝብ መካከል መለስ ታሟል መለስ ሞቷል እያሉ የሚያወሩትን እየተከታተሉ ለማሰር ማቀዳቸውን መረጃ ደረሰን፡፡
እኛም በበኩላችን ለአባሎቻችንና ለደጋፊዎቻችን ይህንኑ አስታወቅን፡፡ በመረጃ ባልተደገፈ ወሬ ላይ እዳይሳተፉ አደረግን፡፡ የአቶ መለስ ሞት ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ ታደለ ተመስጌን፣ ግርማ ዓለሙ፣ ገናናው፣ ገነትና ስጦታው ግርማ የተባሉ የፓርቲው አባላት ‹‹መለስ ሞቷል ብላችኋል›› ተብለው ታሰሩ፡፡ መሞታቸው በመንግስት ከተገለፀ በኋላ ክሱን ቀይረው ህዝብን ለአመጽ ቀስቅሳችኋል በሚል ቀየሩት፡፡ እነዚህ አባሎቻችን ፓርቲው በቅርቡ በወረዳችን ባከናወነው ህዝባዊ ስብሰባ ግንባር ቀደም አስተባባሪዎች የነበሩ ናቸው፡፡›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ….
በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ቡሌሆራ ወረዳ ሀገረማርም ከተማ የወረደው አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት ‹‹ነሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም መለስ ሞቷል እያላችሁ ህዝብን ለማነሳሳት ሞክራችኋላ›› ተብለው አቶ ታሚ ምትኩና አቶ ባናታ በሌላ የተባሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት ፖሊስ አሳሮብናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ‹‹የወረዳው ፖሊስ ከሞያው ተልእኮና ስነ ምግባር በመውጣት የአካባቢውን የኢህኤግን ኃላፊዎች ፍላጎት ለማርካት ሲል በካድሬ እና በደህንነት እየተመራ የህግ ጥሰት እየፈፀመ ነው፡፡
የሰብአዊ መብትን ይደፍራል፡፡ የሚቀርብለትን የፈጠራ ክስ እየተቀበለ የጥላቻና የብቀላ ስራ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ሰውን በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ እንደወንጀለኛ እየቆጠረ ያሰራል፡፡ አቤቱታችንን አይሰሙም፡፡ ህገ መንግስታዊ መብታችንን ተተቅመን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረጋችን የግል መብታቸውንና ክብራቸውን እንደደፈርን በመቁጠር በአባላቶቻችን ላይ ጥቃት እየፈፀሙብን ነው ሲሉ አማረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የቡሌሆራ ወረዳ ፖሊስ ስልክ ደውለን ዋና ሳጅን አካሉ መገርሳ እንደገለፁት ‹‹ታሰሩ ስለሚባሉት ግለሰቦች ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡
እንደዚህ አይነት ሰዎች በእኛ ጣቢያ አልታሰሩም፡፡ ስማቸውም በመዝገብ ላይ የለም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከአስረኞቹ ቤተሰቦች እንደተነገረን እስረኞቹ ወደ ህትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ እዚያው ፖሊስ ጣቢያ መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡
No comments:
Post a Comment