ኢሳት ዜና:- ነሀሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ከትላንት በስተያ ዕለት በፌዴራል ከፍተኛው
ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16 ወንጀል ችሎት የዋስትና መብቱ ተገፎ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከላከል
የተፈረደበት የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፌዴራል ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የታሰረበት ዞን
/ቀጠና/ እና ክፍል አልታወቀም፤ ሊጎበኙት የመጡ ሰዎች ሁሉ እንዳያገኙት ተከልክለዋል፡፡
ጋዜጠኛ
ተመስገንን ለመጠየቅ መጥተው አለ የተባለበት ቦታ ባለመገኘቱ እና የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ሊያቀርቡላቸው
ባለመቻላቸው የተማረሩት የሙያ አጋሮቹ የማረሚያ ቤትን ምክትል ኃላፊን ሄደው ቢያነጋግሩም ኃላፊው “ የፍትህ ጋዜጣ
ተመስገን ደሳለኝን ነው፣ በሉ እርሱን መቼም ልታገኙት አትችሉም፣ ይህ የበላይ አካል ውሳኔ ነው፤ ዝም ብላችሁ
ምግቡን ብቻ ጥላችሁለት ሂዱ፣ እኛ እናደርሳለን” ብለዋል፡፡
ለቤተሰቦቹም አንድ ሰው ወክለው በየቀኑ
ምግቡን እያመጣ ለፖሊስ እየሰጠ ብቻ እንዲሄድ የገለጹት ምክትል ኃላፊው እኛ ኃላፊነታችን በዚህ ቅጥር ጊቢ ውስጥ
የሚገኝ ታራሚን ደህንነት መጠበቅ እንጂ ማን በቤተሰቦቹ ይጠየቅ፣ ማን አይጠየቅ የሚለውንና የት ቦታ መታሰር
እንዳለበት የሚወስነው የበላይ አካል ነው ብለዋል፡፡
በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ያቀረብኩት
የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ክስ ዋስትና አያሳጣም ያለው የፌዴራል ዐቃቤ ህግ አቶ ቴዎድሮስ
ባህሩ፣ ነገር ግን ያቀረብኩት ክስ ተደራራቢ በመሆኑ ዋስትና ይነፈግልኝ በማለት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ
በችሎቱ ዳኛ በመጽደቁ ትላንት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት መኪና ከፍርድ ቤት ቢወጣም የት
እንደተወሰደ እንደማያውቁ የሙያ አጋሮቹ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡
ከዛሬ ጠዋት 2፡30 ሰዓት ጀምሮ በቃሊቲ
ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ ምግብ፣ ቅያሬ ልብስ እና ፒጃማ ይዘው የመጡ ቤተሰቦቹ፣ የሥራ
ባልደረቦቹ፣ የሙያ አጋሮቹ፣ ጓደኞቹ እና አድናቂዎቹ እስከ ቀኑ 6፡00 ሠዓት ድረስ የማረሚያ ቤቱ የሥራ አመራርን
መርህ እና ትዕዛዝ ተከትለው ዞን አንድ፣ ዞን ሦስት እና ዞን አራት የማረሚያ ቤቱ ቀጠናዎች ቢጠይቁና ቢያስጠይቁም
ሊያቀርቡላቸው እንዳልቻሉ ለዘጋቢያችን አሳውቀዋል፡፡
ነገር ግን ዘጋቢያችን ወደ ዜና ምንጮቹ ስልክ ደውሎ
ከኮምፒውተር ላይ ባለው ምዝገባ እንዳረጋገጠው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዋሲሁን ሥም የሚገኘው ከባድ ወንጀለኞች
በሚታሰሩበት ዞን አንድ ውስጥ ሲሆን በዚህ ዞን ውስጥ ከአራት መቶ በላይ ፍርደኞች ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ገና በጊዜ
ቀጠሮ ላይ የሚገኝ እና ፍርደኛ ባለመሆኑ ወደ አንድ ሺህ አምስት መቶ እሥረኞች ወደ ሚገኙበት ዞን ሦስት
ሊያሻግሩት ይችላሉ ብሏል፡፡
ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቤተሰቦቹ የመጣለትን ምግብ የማረሚያ ቤቱ ፖሊስ የተቀበለ ሲሆን ከሥራ ባልደረቦቹ፣ ከሙያ አጋሮቹ እና ከአድናቂዎቹ የመጡለት የፍጆታ እቃዎች ተመላሽ ተደርገዋል፡፡
No comments:
Post a Comment