ኢሳት ዜና:- (Aug. 28) የአብዴፓ ፕሬዚዳንት ተደብድበዋል፤ የአንድነት ፓርቲ አባላትም እየታሰሩ ነው። በቂሊንጦ
እስር ቤት፡የሚገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፦“መለስ
መሞታቸው በቴሌቪዥን በተነገረበት ጊዜ ሌሎቹ ሲያለቅሱ፤ አንተ ስቀሀል” ተብለው ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው
ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
አቶ ዘሪሁን ከደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ብዛት ፊታቸው አባብጦና መንቀሳቀስ አቅቷቸው ሲያነክሱ መታየታቸውን ነው ፍኖተ-ነፃነት ቤተሰቦቻቸውን ጠቅሶ የዘገበው። ለምን ይህ ዘግናኝ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ሲጠይቁ፦ “ገና እንገለዋለን!” መባላቸውንም ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። ቤተሰቦቻቸው ጠይቀዋቸው ከተመለሱ በሁዋላ አቶ ዘሪሁን በሰንሰለት ታስረው እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ከቂሊንጦ እስር ቤት የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ከአቶ መለስ ሞት ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል ደራሼ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ የአንድነት ፓርቲ አባላት እየታሰሩ መሆናቸውን የየወረዳዎቹ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ ገልጸዋል። ሰብሳቢዎቹ እንደገለጹት ኢህአዴጎች የአንድነት አባላትን ያሰሩት ፤ ‹‹አቶ መለስ በመሞታቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ ኢህአዴግን በማውገዝና በመቃወም ይንቀሳቀሳል የሚል ስጋት ስለተፈጠረባቸው ነው፡፡
እንደ
አመራሮቹ አባባል የአካባቢዎቹ ሹመኞች ፦”ህዝብን ለፈለጉት አላማ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ችግር ሊፈጥሩብን
ይችላሉ” ብለው የሚያስቧቸውን፣ በየአካባቢው በህዝብ ተደማጭነት ያላቸውን እና በወቅቱ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ
እያደረጉ የሚገኙት የአንድነት አባላትን እያደኑ በፈጠራ ወንጀል እያሰሩ ይገኛሉ፡፡
የደራሼ ወረዳ
የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ዳፊኮ ታዬ፦ ‹‹ የአካባቢው የኢህአዴግ ካድሬዎችና ደህንነቶች ተሰባስበው፦’
በህዝብ መካከል መለስ ታሟል፤ መለስ ሞቷል’ እያሉ የሚያወሩትን እየተከታተሉ ለማሰር ማቀዳቸውን መረጃ ደረሰን፡፡
እኛም በበኩላችን ለአባሎቻችንና ለደጋፊዎቻችን ይህንኑ አስታወቅን፡፡ በመረጃ ባልተደገፈ ወሬ ላይም እዳይሳተፉ
አደረግን፡፡ ይሁንና የአቶ መለስ ሞት ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ ታደለ ተመስጌን፣ ግርማ ዓለሙ፣ ገናናው፣
ገነትና ስጦታው ግርማ የተባሉ የፓርቲው አባላት፦ ‹‹መለስ ሞቷል ብላችኋል›› ተብለው ታሰሩ”ብለዋል።
የአቶ
መለስ ሞት በመንግስት ከተገለፀ በኋላ ደግሞ ክሱን፦” ለአመጽ ቀስቅሳችኋል” በሚል ቀየሩት ያሉት ሰብሳቢው
የታሰሩት አባሎቻቸው በሙሉ ፓርቲያቸው በቅርቡ በወረዳው ባከናወነው ህዝባዊ ስብሰባ ግንባር ቀደም አስተባባሪዎች
የነበሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን የቡሌሆራ ወረዳ አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው በቀለ እንዳሉት ደግሞ፤ ‹አቶ ታሚ ምትኩና አቶ ባናታ በሌላ የተባሉ የፓርቲው አባላት ባለፈው ነሐሴ 12 ቀን ፦” መለስ ሞቷል እያላችሁ ህዝብን ለማነሳሳት ሞክራችኋል›› ተብለው ታስረዋል።
አቶ
ጌታቸው አያይዘውም፦ ‹‹የወረዳው ፖሊስ ከሞያው ተልእኮና ስነ ምግባር በመውጣት የአካባቢውን የኢህአዴግ
ኃላፊዎች ፍላጎት ለማርካት ሲል በካድሬ እና በደህንነት እየተመራ የህግ ጥሰት እየፈፀመ ነው፡፡ የሰብአዊ መብትን
እየገሰሰ ነው፡፡ የሚቀርብለትን የፈጠራ ክስ እየተቀበለ የጥላቻና የብቀላ ስራ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ሰውን
በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ እንደወንጀለኛ እየቆጠረ ያስራል፡፡ አቤቱታችንን አይሰማም፡፡ ህገ መንግስታዊ መብታችንን
ተጠቅመን ህጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረጋችን፤ የግል መብታቸውንና ክብራቸውን እንደደፈርን በመቁጠር በአባላቶቻችን
ላይ ጥቃት እየፈፀሙብን ነው” ሲሉ አማረዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የቡሌሆራ ወረዳ ፖሊስ ፦ ‹‹ታሰሩ ስለሚባሉት ግለሰቦች ምንም የማውቀው ነገር የለም”ብሏል። ፖሊስ ይህን ይበል እንጂ እስረኞቹ በዚያው ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች አረጋግጠዋል።
ፍትህ
ጋዜጣ አቶ መለስ ስለመሞታቸው የተገኘን መረጃ በማጠናቀር ለህትመት ለማብቃት በመዘጋጀቷ ሳቢያ እንድትቃጠል እና
ህትመቷ እንዲታገድ መወሰኑ፤ ይህንኑም ተከትሎ ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብቱን ተገስሶ ለግፍ
እስር መዳረጉ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment