Welcome!

"If you are neutral 0n the situations of injustice, You have choosen the side of oppressors." -Desmond tutu

Tuesday, May 22, 2012

ተቀናቃኝ ቡድኖችና ፖለቲካ

BY ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
ተመስገን ደሳለኝ በተቀናቃኝ ቡድኖች ላይ አዲስ የመነጋገሪያ ርእስ ከፍቶአል (ግንቦት 3፣ 2004)፤ ጉዳዩ በጣም አንገብጋቢና በጣም ወቅታዊ ነው፤ እንደተለመደው አንብበን ችላ የምንለው ጉዳይ አይደለም፤ ሁላችንም በተቻለን መጠን እውነትን ይዘን ያለ ይሉኝታና ያለፍርሃት በራሳችን ላይ እንዝመትና እውነትን ይዘን እንነሣ።

በ1997 መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኢዴሊና ቀስተ ደመና የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ሆነው ቅንጅትን ፈጠሩ፤ ነገር ግን የመኢአድን ከአቶ ኃይሉ ሻውል፣ ኢዴፓን ከአቶ ልደቱ ህልውና ለመለየት በፍፁም የማይቻል ሆነ፤ ስለዚህም የቅንጅትን ህልውና ፈተና ውስጥ ከተቱትና ተበታተነ፤ እስካሁን ድረስ ህልውናውን ከሕዝብ ህልውና ጋር አስተሳስሮ የቆየ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ በገዢው ወንበር ላይ በጠመንጃ ኃይል ከወጡ በኋላ ጉልበትና ሀብት ሁሉም በጄ ሁሉም በደጄ ብለው ኢሰፓና ወያኔ/ኢሕአዴግ ሎሌዎቻቸውን ሰብስበው ፓርቲ ቢሉ ዋጋ እንደሌለው አይተናል፤ ደርግ በጉልበት ስልጣን በመያዙና ስልጣንን ጉልበት ብቻ በማድረጉ እንደተጠላ ተፍረክርኮ አይዞህ የሚለው ሳያገኝ ወድቆ ተበታተነ፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ እንደገና በጉልበት ኢሰፓን ተካ፤ ሥልጣንን ጉልበት ብቻ አድርጎም እየገዛ ነው፤ በኢሰፓ ዘመን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስምም በተግባርም አልነበሩም፤ በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም ተፈልፍለው በተግባር ተለጉመው በመኖና ባለመኖር መሀከል እያጣጣሩ አሉ፤ ያውም ምርጫ ቦርድ መልካም ፈቃዱ ሲሆን!

ለይስሙላ የተቋቋሙት ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜ ትንሽ የተፈቀደላቸውን ያህል አባላት አስመርጠው በብሔራዊ ምክር ቤት (ፓርላማ) ያስቀምጣሉ፤ የተከበሩት አባላትም ቤትና ደመወዝ ያገኛሉ፤ የመጨረሻው ዓላማቸውም ይኸው ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም ተሰይመው፣ ህልውናቸውን በአንድ ወይ በሁለት ሰዎች ስም ያስከብራሉ።

በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመን አንድ የተለመደ አጉል ፈሊጥ አለ፤ በሆነ ባልሆነው ወያኔ/ኢሕአዴግን መውቀር ያስመሰግናል፤ በአንጻሩ በተቀናቃኝ ቡድኖች ወይ በመሪዎቻቸው ላይ ትችት ማቅረብ እንደክህደትና ከኢትዮጵያዊነት መስመር እንደመውጣት ይታያል፤ ይህ በተደጋጋሚ የታየ ነው፤ በቅንጅት መሪዎች መሀከል የነበረውን የስልጣን ሽኩቻ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ስናገር በመጀመሪያ የራዲዮው ጠያቂ የነበረችው አነጋገሬን አልወደደችውም፤ የግል ስሜትዋን ለመግለጽ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደገና ደውላ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ ጠየቀችኝ፤ ወሬው ከተላለፈ በኋላም ብዙ ሰዎች እየደወሉ ለብቻቸው ብታነጋግራቸውና ብትመክራቸው ይሻል ነበር በማለት የወቀሳ ትችት አቀረቡልኝ፤ እነዚህ ሰዎች የማከብራቸውና ሀሳባቸውን የማልንቅባቸው ናቸው፤ ለሁሉም የመለስሁላቸው እነሱ ለእኔ የሰነዘሩትን ምክር አንደኛ እኛ ሳናስብበትና ተግባራዊ ሳናደርገው ቀረን ብለው መገመታቸው የሚያሳዝን መሆኑን ነበር፤ ሁለተኛ ሁለትና ሶስት ወራት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በተዋናውያኑ በራሳቸው እውነቱ ገሀድ እንደሚወጣ ነግሬአቸው ነበር፤ እኔ የሥልጣን ጥሙን ሽኩቻ በማንሣቴ ለጠብ በር የከፈትሁ የመሰላቸው ሰዎች በቅንጅት ውስጥ የነበረውን ትግል የማያውቁ ናቸው፣ ገና ቀደም ብዬ ሌላው ሁሉ ካቃተኝ በኋላ የስልጣን ሽኩቻው ቅንጅትን እየጎዳው እንደሆነ ስለተረዳሁ ለቅንጅት ሊቀ መንበር ለኃይሉ ሻውል ደብዳቤ ጽፌ ከምክር ቤት መሰናበቴን አሳወቅሁ፤ ከቅንጅት ምክር ቤት ስወጣ በይፋ በአደባባይ ሳልናገር መቅረቴ ስሕተት ነው፤ መናገር ነበረብኝ፤ ግን ያው በኋላ ከብዙ ሰዎች የሰማሁት ወቀሳ በእኔም ውስጥ ስለነበረ ይሉኝታ ይዞኝ ተሳሳትሁ፤ ከቃሊቲ ከወጣን በኋላ በህንድ አገር ሀኪም ቤት ማጅራቴን በመጋዝ ለመተርተር ስዘጋጅ ድንገት ሳልነቃ ብቀር እውነት ተዳፍኖ እንዳይቀር በማለት ምስክርነቴን ሰጠሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ የነበርሁበትን ሁኔታ በትንሹም ቢሆን ለመገመት ከተቻለ ለእውነት በእውነት ከመመስከር ሌላ ዓላማ እንደማይኖረኝ ለመረዳት እንዴት እንዳስቸገረ እስከዛሬ አልገባኝም፤ ጥርጣሬያችንና አለመተማመናችን ድንበር የለውም ማለት ነው።

ከዚያ በኋላ ብዙ መጽሐፎች ተጽፈዋል፤ ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ሥላሴ፣ ልደቱ አያሌው፣ ደበበ እሸቱ፣ አንተነህ ሙሉጌታ (የመጽሐፉን ርእስ አበላሽቶት ብዙ ሰዎች አላነበቡትም እንጂ በጣም ጥሩ መጽሐፍ) መስፍን ወልደማርያምም ጽፈዋል፤ አሁን ደግሞ ሲሳይ አጌና (ከውጭ እንደጋዜጠኛ ይሁን ወይስ የውስጥ መስሎ አላውቅም፤ ነገር ግን በራድዮ ሲናገር እንደሰማሁት ብርሃኑ ነጋን ከእውነቱ ሊያርቀው በጣም ሲሞክር እውነቱን ይደፈጥጣል)፤ ለማናቸውም ታዛቢዎች ተናገሩት አልተናገሩት በኃይሉ ሻውል፣ በብርሃኑና በልደቱ መሀከል የነበረውን ግልጽ የሆነ ሥርዓት ያጣ ፉክክር ማንም ሊክደው ወይም ሊያድበሰብሰውና ሊያልፈው አይችልም፤ ለምን ቅንጅት ፈራረሰ? አንዳንዶቻችን ክብራችንን አንጥፈን ለማስታረቅ ሞክረናል፤ አንድ ምሳሌ ለመስጠት በቀጠሮ ሄደን አቶ ገብረጻድቅ፣ አቶ ይልማ ይፍሩና እኔ ከአቶ ኃይሉ ሻውል አጥር ውጭ ለእኩል ሰዓት ያህል መኪና ውስጥ ቆይተን ሳይሆንልን ተመልሰናል፤ በኋላም አሜሪካ ሆኖ በነጭ ወረቀት ከሕግ ውጭ የሆነ የሹም-ሽር ሲያደርግ ሀሳቡን ለማስለወጥ አሜሪካ ስልክ ደውዬ ለማነጋገር ብሞክር እኔንም ባላንጣው አደረገኝ፤ ተፎካካሪዎቹን ለማቀራረብ፣ ለማስታረቅና ወደአብሮ መሰለፍ ለማምጣት በተደረገው ጥረት የተሳተፉትን ሁሉ ተፎካካሪዎቹ በጥላቻ ይመለከቱአቸው ጀመሩ።

በልደቱ የተጀመረው የቅንጅት መገነጣጠል፣ በብርሃኑ ነጋና በኃይሉ ሻውል ቀጥሎ ብርቱካን የምትመራው አንድነት ብቻውን ቀረ፤ በአንድነትም ውስጥ ገና ከመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ ብርቱካን በመመረጥዋ ቅር ያላቸው አባሎች አኩርፈው ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ ብርቱካን ስትታሰር ኤንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በጉጉት ሲጠብቀው የነበረውን ወንበር አገኘና የአምባገነንነት አገዛዙን በግምባር ቀደምትነት ከዶር. ኃይሉ አርአያና ከአቶ ዓሥራት ጣሴ ጋር ጀመረ፤ ሁሉም ቢያንስ ከሁለት ሺህ ብር በላይ የወር ደመወዝ ያገኙ ነበር፤ እንዲሁም የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ሁሉ በጥሩ ደመወዝ ተሰንገው የተያዙ ነበሩ፤ እነዚህ ናቸው ሎሌዎች አይደለንም የሚሉት፤ ከበስተጀርባቸውም የብሔራዊ ምክር ቤት ገብተው ሌሎቹ ቃሊቲ በነበሩበት ጊዜ ደመወዝ ሲበሉ የነበሩ ናቸው፤ ያንን የደመወዝ ወንበር እንደያዙ ለመቀጠል የተመኙ የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የምክር ቤት አባላት ነበሩ፤ ግዛቸው እነዚህን ሁሉ ሎሌዎች አሰልፎ ስሙ ወደምግባሩ መራውና የማይበገር አንባ-ገነን ሆነ፤ ከመጀመሪያዎቹ አወዛጋቢ ጉዳዮች መሀከል አባላት በጽሕፈት ቤቱ አዳራሽ ያለፈቃድ እንዳይሰበሰቡ፣ ግዛቸው፣ ኃይሉ አርአያና ዓሥራት ባልፈቀዱት ጉዳይ መወያየት መከልከሉን፣ በነፃነት አባልነታቸውን ለመወጣት የሚፈልጉትንና ከሎሌነት ያፈነገጡትን ሰዎች ለማስወንጀል ማስፈራራት ነበሩ፤ ከውጭም ድጋፍ ነበራቸው፤ የቅንጅት የድጋፍ ኮሚቴ በአሜሪካ ሊቀመንበር ነኝ የሚል አክሎግ ልመንህ የሚባል የማስፈራሪያ ደብዳቤ ጽፎልን እኔ መልስ ሰጥቸውአለሁ፤ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊው አቶ ዓሥራት ጣሴ አንደኛ አንዲት ጸሐፊ የነበረች የአንድነት አባልን ያለማስጠንቀቂያና ካሣ፣ ሁለተኛ አንዲት የጽዳት ሠራተኛን እንዲሁም ያለምንም ማስጠንቀቂያና ካሣ ከሥራ ማስወጣቱ ናቸው፤ በነዚህ ምክንያቶች አንድነት ለሁለት ተከፈለ፤ ግዛቸው መርጠው ወንበሩ ላይ ያስቀመጡትን ሰዎች አባርሮ በዶር. ነጋሶ ጊዳዳ፣ በአቶ ስዬ አብርሃና በአቶ ገብሩ ዓሥራት ድጋፍ መሰላሉን ሊወጣ ተመኘ፤ መሰላሉ ወደቀ።

ዛሬ ቅንጅትን ሰባብረው ግልገል የሥልጣን ፈረሶችን የፈጠሩት ሁሉ በሦስት ምክንያቶች ኮስሰዋል፤ አንደኛ ሰውን መግዣ ገንዘብ እያነሰ ነው፤ ሁለተኛ አባሎችም የተሻለ ንቃትና ትምህርት እያገኙ ሎሌነትን እምቢ እያሉ ነው፤ ሦስተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲሶቹን መኳንንት የኤንጂነር ግዛቸውን፣ የዶር. ኃይሉ አርአያንና የአቶ ዓሥራት ጣሴን ‹‹በታላላቅ›› ሰዎች ጥላ ስር ሆነው ለመሽሎክ ያቀዱት አልተሳካላቸውም፤ መማር የሚችሉት ሊማሩ ሄዱ፤ የማይችሉት ቀሩ።

No comments:

Post a Comment